በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 120

ፍሬ የሚያፈራ ቅርንጫፍና የኢየሱስ ወዳጅ መሆን

ፍሬ የሚያፈራ ቅርንጫፍና የኢየሱስ ወዳጅ መሆን

ዮሐንስ 15:1-27

  • እውነተኛው የወይን ተክልና ቅርንጫፎቹ

  • በኢየሱስ ፍቅር መኖር የሚቻልበት መንገድ

ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ልብ ለልብ ውይይት በማድረግ አበረታቷቸዋል። አሁን እኩለ ሌሊት ሳያልፍ አይቀርም። ኢየሱስ ለሥራ የሚያነሳሳ ምሳሌ ተናገረ።

ምሳሌውን ሲጀምር “እኔ እውነተኛው የወይን ተክል ነኝ፤ አትክልተኛው ደግሞ አባቴ ነው” አለ። (ዮሐንስ 15:1) ምሳሌው ከበርካታ ዘመናት በፊት ስለ እስራኤል ብሔር ከተነገረው ሐሳብ ጋር የሚመሳሰል ነው፤ የእስራኤል ብሔር፣ የይሖዋ የወይን ተክል ተብሎ ተጠርቷል። (ኤርምያስ 2:21፤ ሆሴዕ 10:1, 2) ይሁን እንጂ ይሖዋ ይህን ብሔር ሊተወው ነው። (ማቴዎስ 23:37, 38) በመሆኑም ኢየሱስ የተናገረው ነገር አዲስ ሐሳብ ነው። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው የወይን ተክል ኢየሱስ ነው፤ ይሖዋ በ29 ዓ.ም. ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ ከቀባው ጊዜ አንስቶ ሲንከባከበው ቆይቷል። ሆኖም ኢየሱስ የወይኑ ተክል የሚያመለክተው እሱን ብቻ አለመሆኑን ሲገልጽ እንዲህ አለ፦

“በእኔ ላይ ያለውን፣ ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ [አባቴ] ቆርጦ ይጥለዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ደግሞ ይበልጥ እንዲያፈራ ያጠራዋል። . . . ቅርንጫፉ ከወይኑ ተክል ጋር ተጣብቆ ካልኖረ በራሱ ፍሬ ማፍራት አይችልም፤ እናንተም ከእኔ ጋር ያላችሁን አንድነት ጠብቃችሁ ካልኖራችሁ ፍሬ ልታፈሩ አትችሉም። እኔ የወይኑ ተክል ነኝ፤ እናንተ ደግሞ ቅርንጫፎቹ ናችሁ።”—ዮሐንስ 15:2-5

ኢየሱስ ከሄደ በኋላ ረዳት የሚሆነውን መንፈስ ቅዱስ እንደሚልክላቸው ለታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ቃል ገብቷል። ከ51 ቀናት በኋላ ሐዋርያቱና ሌሎች ደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስ በወረደባቸው ጊዜ የወይኑ ተክል ቅርንጫፎች ሆነዋል። “ቅርንጫፎቹ” በሙሉ ከኢየሱስ ጋር ያላቸውን አንድነት ጠብቀው መኖር አለባቸው። ይህን የሚያደርጉበት ዓላማ ምንድን ነው?

ኢየሱስ “ማንኛውም ሰው ከእኔ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ከኖረና እኔም ከእሱ ጋር አንድ ሆኜ ከኖርኩ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤ እናንተ ከእኔ ተለይታችሁ ምንም ነገር ልታደርጉ አትችሉምና” በማለት አብራራ። እነዚህ “ቅርንጫፎች” ማለትም የእሱ ታማኝ ተከታዮች የእሱን ባሕርያት በመምሰል፣ ለሌሎች ስለ አምላክ መንግሥት በቅንዓት በማወጅና ተጨማሪ ሰዎች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ በመርዳት ብዙ ፍሬ ያፈራሉ። አንድ ሰው ከኢየሱስ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ባይኖርና ፍሬ ባያፈራስ? ኢየሱስ ‘አንድ ሰው ከእኔ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ካልኖረ ይጣላል’ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ “ከእኔ ጋር ያላችሁን አንድነት ከጠበቃችሁና ቃሌ በልባችሁ ከኖረ የምትፈልጉትን ማንኛውንም ነገር ብትጠይቁ ይፈጸምላችኋል” በማለት ተናገረ።—ዮሐንስ 15:5-7

አሁን ደግሞ ኢየሱስ ቀደም ሲል ሁለት ጊዜ የጠቀሰውን ርዕሰ ጉዳይ ይኸውም ትእዛዛቱን መጠበቅን አስመልክቶ ተናገረ። (ዮሐንስ 14:15, 21) ደቀ መዛሙርቱ ይህን ማድረጋቸውን ማሳየት የሚችሉበትን ግሩም መንገድ ሲገልጽ “እኔ የአብን ትእዛዛት ጠብቄ በፍቅሩ እንደምኖር እናንተም ትእዛዛቴን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ” አላቸው። ይሁንና ይሖዋ አምላክንና ልጁን መውደድ ብቻውን በቂ አይደለም። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ትእዛዜ ይህ ነው፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም። የማዛችሁን ነገር የምትፈጽሙ ከሆነ ወዳጆቼ ናችሁ።”—ዮሐንስ 15:10-14

ኢየሱስ በእሱ ለሚያምኑ ሁሉ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ይህን ፍቅሩን ያሳያል። የእሱ ምሳሌ፣ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን የሚጠይቀውን ይህ ዓይነቱን ፍቅር ተከታዮቹም አንዳቸው ለሌላው እንዲያሳዩ ሊያነሳሳቸው ይገባል። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” አለ፤ በእርግጥም ኢየሱስ ቀደም ሲል እንደተናገረው ይህ ፍቅር ተለይተው እንዲታወቁ ያደርጋል።—ዮሐንስ 13:35

ሐዋርያቱ፣ ኢየሱስ “ወዳጆች” ብሎ እንደጠራቸው ልብ ሊሉ ይገባል። ይህን ያለበትን ምክንያት ሲገልጽ “ከአባቴ የሰማሁትን ነገር ሁሉ ስላሳወቅኳችሁ ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ” አለ። የኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች መሆንና አባቱ የነገረውን ማወቅ እንዴት ያለ ውድ መብት ነው! ተከታዮቹ ይህን ዝምድና እንደያዙ ለመቀጠል ምንጊዜም ‘ፍሬ ማፍራት’ ይኖርባቸዋል። ይህን የሚያደርጉ ከሆነ ‘አብ በስሜ  የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል’ በማለት ኢየሱስ ተናገረ።—ዮሐንስ 15:15, 16

በእነዚህ “ቅርንጫፎች” ማለትም በደቀ መዛሙርቱ መካከል ያለው ፍቅር ወደፊት የሚመጣውን ነገር በጽናት ለመወጣት ይረዳቸዋል። ኢየሱስ፣ ዓለም እንደሚጠላቸው ያስጠነቀቃቸው ቢሆንም እንደሚከተለው በማለት አጽናናቸው፦ “ዓለም ቢጠላችሁ፣ እናንተን ከመጥላቱ በፊት እኔን እንደጠላኝ ታውቃላችሁ። የዓለም ክፍል ብትሆኑ ኖሮ ዓለም የራሱ የሆነውን በወደደ ነበር። አሁን ግን . . . የዓለም ክፍል ስላልሆናችሁ ከዚህ የተነሳ ዓለም ይጠላችኋል።”—ዮሐንስ 15:18, 19

ኢየሱስ ዓለም እነሱን የሚጠላበትን ምክንያት ይበልጥ ሲያብራራ “የላከኝን ስለማያውቁት በስሜ ምክንያት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ያደርጉባችኋል” አለ። ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት እሱን የሚጠሉት ሰዎች እንዲፈረድባቸው እንደሚያደርጉ ሲገልጽ እንዲህ በማለት ተናገረ፦ “ሌላ ማንም ያላደረገውን ነገር በመካከላቸው ባላደርግ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን እኔን አይተዋል እንዲሁም እኔንም ሆነ አባቴን ጠልተዋል።” ለነገሩ ጥላቻቸው ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል።—ዮሐንስ 15:21, 24, 25፤ መዝሙር 35:19፤ 69:4

ቀጥሎም ኢየሱስ ረዳት የሆነውን መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው በድጋሚ ቃል ገባ። ተከታዮቹ በሙሉ ይህን ኃይል ማግኘት ይችላሉ፤ እንዲሁም ይህ ኃይል ፍሬ እንዲያፈሩ ይኸውም ‘ምሥክር እንዲሆኑ’ ይረዳቸዋል።—ዮሐንስ 15:27