በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 113

ትጉ ስለ መሆን የተሰጠ ትምህርት—ታላንቱ

ትጉ ስለ መሆን የተሰጠ ትምህርት—ታላንቱ

ማቴዎስ 25:14-30

  • ኢየሱስ የታላንቱን ምሳሌ ተናገረ

ኢየሱስ ከአራት ሐዋርያቱ ጋር በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ነው፤ እዚያው እያሉ ሌላ ምሳሌ ነገራቸው። ከጥቂት ቀናት በፊት በኢያሪኮ እያለ፣ መንግሥቱ የሚመጣው ወደፊት እንደሆነ ለማመልከት የምናኑን ምሳሌ ተናግሮ ነበር። አሁን የተናገረው ምሳሌ ከምናኑ ምሳሌ ጋር የሚያመሳስለው ብዙ ነገር አለ። ይህ ምሳሌ፣ ስለ መገኘቱና ስለ ሥርዓቱ መደምደሚያ ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠው መልስ ክፍል ነው። ደቀ መዛሙርቱ በአደራ የሰጣቸውን ሥራ በትጋት ማከናወን እንዳለባቸው ያጎላል።

ኢየሱስ ምሳሌውን ሲጀምር እንዲህ አለ፦ “መንግሥተ ሰማያት ባሪያዎቹን ጠርቶ ንብረቱን ለእነሱ በአደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ከተነሳ ሰው ጋር ይመሳሰላል።” (ማቴዎስ 25:14) ቀደም ሲል ኢየሱስ፣ ራሱን “ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተረክቦ ለመመለስ” ወደ ሌላ አገር ከተጓዘ ሰው ጋር ስላመሳሰለ ሐዋርያቱ አሁን በሚናገረው ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው “ሰው” እሱ እንደሆነ በቀላሉ ማስተዋል ይችላሉ።—ሉቃስ 19:12

በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሰው ወደ ሌላ አገር ከመጓዙ በፊት ውድ ንብረቱን ለባሪያዎቹ በአደራ ሰጣቸው። ኢየሱስ ለሦስት ዓመት ተኩል ባከናወነው አገልግሎት ላይ ትኩረት ያደረገው የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክ ላይ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱንም ለዚህ ሥራ አሠልጥኗቸዋል። እንዲሠሩ ያሠለጠናቸውን ሥራ እንደሚያከናውኑ በመተማመን አሁን ትቷቸው ሊሄድ ነው።—ማቴዎስ 10:7፤ ሉቃስ 10:1, 8, 9፤ ከዮሐንስ 4:38 እና 14:12 ጋር አወዳድር።

በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሰው ንብረቱን ያከፋፈለው እንዴት ነው? ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው፣ ለአንዱ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሄደ።” (ማቴዎስ 25:15) እነዚህ ባሪያዎች በአደራ የተሰጣቸውን ንብረት ምን ያደርጉታል? ጌታቸው ትርፍ እንዲያገኝ ሲሉ የተሰጣቸውን ታላንት ተጠቅመው በትጋት ይሠሩ ይሆን? ኢየሱስ ሐዋርያቱን እንዲህ አላቸው፦

“አምስት ታላንት የተቀበለው ሰው ወዲያው ሄዶ ነገደበትና ሌላ አምስት ታላንት አተረፈ። በተመሳሳይም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ ታላንት ብቻ የተቀበለው ባሪያ ግን ሄዶ መሬት ቆፈረና ጌታው የሰጠውን ገንዘብ ቀበረ።” (ማቴዎስ 25:16-18) ታዲያ ጌታቸው ሲመለስ ምን ያደርጋል?

ኢየሱስ በመቀጠል “ከረጅም ጊዜ በኋላ የእነዚያ ባሪያዎች ጌታ መጥቶ ሒሳቡን ከባሪያዎቹ ጋር ተሳሰበ” አለ። (ማቴዎስ 25:19) የመጀመሪያዎቹ ሁለት ባሪያዎች ‘እንደ ችሎታቸው’ ይኸውም አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ሠርተዋል። ሁለቱም ባሪያዎች በአደራ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ትጉ፣ ታታሪና ውጤታማ ሆነዋል። አምስት ታላንትም ሆነ ሁለት ታላንት የተሰጠው ባሪያ የተቀበለውን እጥፍ አድርጓል። (በወቅቱ አንድ ሠራተኛ አንድ ታላንት ለማግኘት 19 ዓመት ገደማ መሥራት ነበረበት።) ጌታው እያንዳንዱን ባሪያ እንደሚከተለው በማለት አመሰገነ፦ “ጎበዝ፣ አንተ ጥሩና ታማኝ ባሪያ! በጥቂት ነገሮች ታማኝ ሆነህ ተገኝተሃል። ስለዚህ በብዙ ነገሮች ላይ እሾምሃለሁ። ወደ ጌታህ ደስታ ግባ።”—ማቴዎስ 25:21

አንድ ታላንት የተቀበለው ባሪያ ሁኔታ ግን የተለየ ነው።  ይህ ባሪያ እንዲህ አለ፦ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ያልዘራኸውን የምታጭድ፣ ያልደከምክበትንም እህል የምትሰበስብ ኃይለኛ ሰው መሆንህን አውቃለሁ። ስለዚህ ፈራሁ፤ ሄጄም ታላንትህን መሬት ውስጥ ቀበርኩት። ገንዘብህ ይኸውልህ።” (ማቴዎስ 25:24, 25) ይህ ባሪያ፣ ታላንቱን ገንዘብ ለዋጮች ጋ በማስቀመጥ ጌታው የተወሰነ ትርፍ እንዲያገኝ እንኳ አላደረገም። በእርግጥም የጌታውን ጥቅም የሚነካ ነገር ፈጽሟል።

ጌታው ይህን ግለሰብ “ክፉና ሰነፍ ባሪያ” ብሎ መጥራቱ የተገባ ነው። ያለው ንብረት ከእሱ ተወሰደና በትጋት ለመሥራት ፈቃደኛ ለሆነው ባሪያ ተሰጠ። ጌታው የሚመራበትን ደንብ ሲገልጽ “ላለው ሁሉ ይጨመርለታል፤ ደግሞም ይትረፈረፍለታል። የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል” አለ።—ማቴዎስ 25:26, 29

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህን ምሳሌ ጨምሮ ሊያስቡበት የሚገባ ብዙ ነገር አለ። ኢየሱስ በአደራ የሰጣቸው ነገር ይኸውም ደቀ መዛሙርት የማድረግ ውድ መብት ከፍ ተደርጎ ሊታይ እንደሚገባ መገንዘብ ይችላሉ። ደግሞም ይህን ኃላፊነት በትጋት እንዲወጡ ይጠብቅባቸዋል። ኢየሱስ፣ የሰጣቸውን የስብከት ሥራ ሁሉም በእኩል መጠን ማከናወን እንዳለባቸው አያስብም። በምሳሌው ላይ እንደተገለጸው “እያንዳንዱ እንደ ችሎታው” ይኸውም አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርበታል። ያም ቢሆን አንድ ባሪያ “ሰነፍ” ቢሆንና የጌታውን ንብረት ለማብዛት የተቻለውን ያህል ባይጥር ኢየሱስ በእሱ ፈጽሞ ደስ አይሰኝም።

ሐዋርያቱ “ላለው ሁሉ ይጨመርለታል” የሚለውን ማረጋገጫ ሲሰሙ ምንኛ ተደስተው ይሆን!