በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 26

“ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል”

“ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል”

ማቴዎስ 9:1-8 ማርቆስ 2:1-12 ሉቃስ 5:17-26

  • ኢየሱስ፣ ሽባ የሆነውን ሰው ኃጢአት ይቅር በማለት ፈወሰው

በዚህ ወቅት የኢየሱስ ዝና በስፋት ተሰራጭቷል። ብዙ ሰዎች፣ ሲያስተምር ለመስማትና ተአምራት ሲፈጽም ለማየት ሲሉ ርቀው ከሚገኙ አካባቢዎች እንኳ እሱ ወዳለበት ቦታ እየጎረፉ ነው። ከጥቂት ቀናት በኋላ ኢየሱስ የእንቅስቃሴው ማዕከል ወደሆነችው ወደ ቅፍርናሆም ተመለሰ። ኢየሱስ መመለሱን የሚገልጸው ወሬ በገሊላ ባሕር አቅራቢያ በምትገኘው በዚህች ከተማ ወዲያውኑ ተዳረሰ። በዚህም ምክንያት ብዙዎች እሱ ወዳለበት ቤት መጡ። ከእነዚህም መካከል ከመላዋ ገሊላ እንዲሁም ኢየሩሳሌምን ጨምሮ ከይሁዳ የመጡ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ይገኙበታል።

“ቤቱ ሞልቶ ደጅ ላይ እንኳ ቦታ እስኪታጣ ድረስ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ እሱም የአምላክን ቃል ይነግራቸው ጀመር።” (ማርቆስ 2:2) አሁን፣ በጣም አስደናቂ ለሆነ አንድ ክንውን መድረኩ ተመቻችቷል። በዚህ ወቅት የተፈጸመው ክንውን ኢየሱስ ለሰብዓዊ መከራ መንስኤ የሆነውን ነገር የማስወገድና በሽታን የመፈወስ ኃይል እንዳለው ለመገንዘብ ያስችለናል።

ኢየሱስ በቤቱ ውስጥ የተሰበሰቡትን ብዙ ሰዎች እያስተማረ እያለ አራት ሰዎች ሽባ የሆነ አንድ ሰው በቃሬዛ ይዘው መጡ። ኢየሱስ ጓደኛቸውን እንዲፈውስላቸው ፈልገዋል። ሆኖም ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ሽባውን “ወደ ኢየሱስ ማቅረብ” አልቻሉም። (ማርቆስ 2:4) እንዴት የሚያበሳጭ ነው! ሰዎቹ ግን ጠፍጣፋ ወደሆነው ጣሪያ ወጡና ነደሉት። ከዚያም ሽባውን ሰው ቃሬዛው ላይ እንደተኛ በቀዳዳው በኩል ወደታች አወረዱት።

ኢየሱስ ንግግሩን ስላቋረጡት ተናደደ? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ በእምነታቸው በጣም ተገረመ፤ ሽባውን ሰውም “ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል” አለው። (ማቴዎስ 9:2) ይሁንና ኢየሱስ ኃጢአትን ይቅር ሊል ይችላል? ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይህን ማድረግ እንደሚችል አልተሰማቸውም፤ በመሆኑም “ይህ ሰው እንዲህ ብሎ የሚናገረው ለምንድን ነው? አምላክን እየተዳፈረ እኮ ነው። ከአንዱ ከአምላክ በቀር ኃጢአትን ማን ይቅር ሊል ይችላል?” ብለው አሰቡ።—ማርቆስ 2:7

ኢየሱስም ሐሳባቸውን ስላወቀ እንዲህ አላቸው፦ “በልባችሁ እንዲህ እያላችሁ የምታስቡት ለምንድን ነው? ሽባውን ‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሏል’ ከማለትና ‘ተነሳና ቃሬዛህን ተሸክመህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል?” (ማርቆስ 2:8, 9) በእርግጥም ኢየሱስ ወደፊት የሚያቀርበውን መሥዋዕት መሠረት በማድረግ የሰውየውን ኃጢአት ይቅር ማለት ይችላል።

ከዚያም ኢየሱስ፣ የሚተቹትን ሰዎች ጨምሮ በዚያ ለተሰበሰበው ሕዝብ ሁሉ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው አሳያቸው። ወደ ሽባው ዞር አለና “ተነስ፣ ቃሬዛህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” ብሎ አዘዘው። ሰውየውም በዚያ ያሉት ሁሉ እያዩ ወዲያውኑ ተነሳና ቃሬዛውን ተሸክሞ ሄደ። ሰዎቹ በጣም ተገረሙ! “‘እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይተን አናውቅም’ በማለት አምላክን አከበሩ።”—ማርቆስ 2:11, 12

ኢየሱስ ኃጢአትን ከበሽታ ጋር አያይዞ መጥቀሱ እንዲሁም የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት ከአካላዊ ጤንነት ጋር የተያያዘ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የመጀመሪያው ወላጃችን አዳም ኃጢአት እንደሠራና ሁላችንም የኃጢአት ውጤት የሆኑትን በሽታንና ሞትን እንደወረስን ይገልጻል። ሆኖም በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ኢየሱስ አምላክን የሚወዱና የሚያገለግሉ ሰዎችን ሁሉ ኃጢአት ይቅር ይላል። ከዚያም በሽታ ለዘላለም ይወገዳል።—ሮም 5:12, 18, 19