በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 84

ደቀ መዝሙር መሆን ምን ያህል ከባድ ኃላፊነት ነው?

ደቀ መዝሙር መሆን ምን ያህል ከባድ ኃላፊነት ነው?

ሉቃስ 14:25-35

  • ደቀ መዝሙር መሆን የሚያስከፍለው መሥዋዕት

ኢየሱስ ከፈሪሳውያን መሪዎች በአንዱ ቤት በተጋበዘበት ወቅት ጠቃሚ ትምህርቶችን አስተምሯል። ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርገውን ጉዞ ሲቀጥል ብዙ ሕዝብ አብሮት ይጓዝ ጀመር። ሆኖም ሰዎቹ የሚከተሉት ለምንድን ነው? እነዚህ ሰዎች፣ የኢየሱስ እውነተኛ ተከታይ መሆን የሚጠይቅባቸው ነገር ምንም ይሁን ምን በእርግጥ ተከታዮቹ መሆን ይፈልጋሉ?

እየተጓዙ ሳሉ ኢየሱስ አንዳንዶችን ሊያስደነግጥ የሚችል ነገር ተናገረ፦ “ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ አባቱን፣ እናቱን፣ ሚስቱን፣ ልጆቹን፣ ወንድሞቹንና እህቶቹን ሌላው ቀርቶ የገዛ ራሱን ሕይወት እንኳ የማይጠላ ከሆነ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።” (ሉቃስ 14:26) ኢየሱስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነው?

ኢየሱስ ተከታዮቹ የሚሆኑ ሁሉ፣ ቤተሰባቸውን ቃል በቃል መጥላት እንዳለባቸው መናገሩ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለቤተሰቦቻቸው ያላቸው ፍቅር ለእሱ ካላቸው ፍቅር ያነሰ መሆን እንዳለበት መግለጹ ነው፤ በሌላ አባባል ኢየሱስ ስለ ራት ግብዣ በተናገረው ምሳሌ ላይ እንደጠቀሰውና የቀረበለትን ትልቅ ግብዣ ገና ማግባቱ በመሆኑ ሳይቀበል እንደቀረው ሰው መሆን የለባቸውም። (ሉቃስ 14:20) የአይሁዳውያን ቅድመ አያት የሆነው ያዕቆብ ሊያን ‘ይጠላ’ ራሔልን ግን ይወድ እንደነበር ተገልጿል፤ እንዲህ ሲባል ለሊያ ያለው ፍቅር ለራሔል ካለው ፍቅር ያነሰ ነው ማለት ነው።—ዘፍጥረት 29:31 ግርጌ

ኢየሱስ፣ አንድ ደቀ መዝሙር “የገዛ ራሱን ሕይወት” ወይም ነፍስ እንኳ መጥላት እንዳለበት መናገሩን ልብ በል። ኢየሱስ ይህን ሲል አንድ እውነተኛ ደቀ መዝሙር ከራሱ ሕይወት እንኳ አስበልጦ ኢየሱስን ሊወደው እንደሚገባ ሌላው ቀርቶ አስፈላጊ ከሆነ ሕይወቱን ለመስጠት ጭምር ፈቃደኛ መሆን እንዳለበት መግለጹ ነው። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ከባድ ኃላፊነት ያስከትላል። እንደ ቀላል ታይቶ በሚገባ ሳይታሰብበት የሚጀመር ነገር አይደለም።

የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የሆነ ሰው መከራና ስደት ሊደርስበት ይችላል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “የራሱን የመከራ እንጨት ተሸክሞ የማይከተለኝ ሁሉ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም” ብሏል። (ሉቃስ 14:27) በእርግጥም እውነተኛ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ልክ እንደ ጌታው የነቀፋ ሸክምን ለመሸከም ፈቃደኛ መሆን አለበት። ኢየሱስ በጠላቶቹ እጅ እንደሚገደልም ጭምር ተናግሯል።

ስለዚህ ከኢየሱስ ጋር እየተጓዙ ያሉት ሰዎች፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን የሚያስከትለውን ኃላፊነት በጥሞና ሊያስቡበት ይገባል። ኢየሱስ ይህን ሐቅ ለማጉላት አንድ ምሳሌ ተጠቀመ። “ለምሳሌ ከእናንተ መካከል፣ ግንብ ለመገንባት ፈልጎ ለመጨረስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዳለው ለማወቅ በመጀመሪያ ተቀምጦ ወጪውን የማያሰላ ማን ነው?” አለ። አክሎም ‘እንዲህ ካላደረገ ግን መሠረቱን ከጣለ በኋላ ፍጻሜ ላይ ማድረስ ሊያቅተው ይችላል’ በማለት ተናገረ። (ሉቃስ 14:28, 29) እንግዲያው ከኢየሱስ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዙ ያሉት ሰዎች፣ ደቀ መዛሙርቱ ከመሆናቸው በፊት ኃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ ለመወጣት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለባቸው። ይህን ሐሳብ ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ሌላ ምሳሌ ተናገረ፦

“አንድ ንጉሥ ሌላን ንጉሥ ጦርነት ለመግጠም በሚነሳበት ጊዜ 20,000 ሠራዊት አስከትቶ የመጣበትን ንጉሥ በ10,000 ሠራዊት ሊቋቋመው ይችል እንደሆነ ለማወቅ  በቅድሚያ ተቀምጦ አይማከርም? መቋቋም የማይችል ከሆነ ሊገጥመው የሚመጣው ንጉሥ ገና ሩቅ ሳለ አምባሳደሮች ልኮ እርቅ ለመፍጠር ይደራደራል።” ኢየሱስ ነጥቡን ለማጉላት “እንደዚሁም ከእናንተ መካከል ያለውን ንብረት ሁሉ የማይሰናበት ፈጽሞ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም” አለ።—ሉቃስ 14:31-33

እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው አብረውት እየተጓዙ ላሉት ሰዎች ብቻ አይደለም። ስለ ክርስቶስ የተማሩ ሰዎች ሁሉ እዚህ ላይ የተናገረውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን አለባቸው። በሌላ አባባል የእሱ ደቀ መዛሙርት መሆን ከፈለጉ ያላቸውን ነገር ሁሉ ይኸውም ንብረታቸውንና ሕይወታቸውን ጭምር መሥዋዕት ለማድረግ ዝግጁ መሆን ይኖርባቸዋል። ይህ በጸሎት ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።

ቀጥሎ ደግሞ ኢየሱስ፣ በተራራው ስብከቱ ላይ ደቀ መዛሙርቱ “የምድር ጨው” እንደሆኑ በተናገረ ጊዜ ያነሳውን ጉዳይ መልሶ ጠቀሰ። (ማቴዎስ 5:13) ጨው አንድ ነገር እንዳይበላሽ እንደሚያደርግ ሁሉ ደቀ መዛሙርቱ የሚያሳድሩት በጎ ተጽዕኖም፣ ሰዎች በመንፈሳዊም ሆነ በሥነ ምግባራዊ ሁኔታ እንዳይበከሉ የሚከላከል መሆኑን መግለጹ ነበር። ኢየሱስ አገልግሎቱ እየተገባደደ ባለበት በዚህ ወቅት ደግሞ እንዲህ አለ፦ “ጨው ጥሩ ነገር እንደሆነ የታወቀ ነው። ሆኖም ጨው ራሱ የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ጨውነቱን በምን መመለስ ይቻላል?” (ሉቃስ 14:34) አድማጮቹ፣ ከአፈር ጋር በመቀላቀሉ ንጹሕ ያልሆነና እምብዛም የማይጠቅም ጨው እንዳለ ያውቃሉ።

ስለዚህ ለረጅም ጊዜ የእሱ ደቀ መዛሙርት ሆነው የቆዩ ሰዎች እንኳ አቋማቸውን ማላላት እንደሌለባቸው እያመለከተ ነው። አቋማቸውን ቢያላሉ፣ ጣዕሙን እንዳጣ ጨው ጥቅም አይኖራቸውም። በመሆኑም የዓለም መዘባበቻ ይሆናሉ። ከዚህም በላይ በአምላክ ፊት ብቃት የጎደላቸው፣ እንዲያውም በስሙ ላይ ነቀፋ የሚያመጡ ይሆናሉ። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዳያጋጥም መጠንቀቅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማጉላት ሲል “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” ብሏል።—ሉቃስ 14:35