በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 75

ኢየሱስ የደስታ ምንጭ ምን እንደሆነ ገለጸ

ኢየሱስ የደስታ ምንጭ ምን እንደሆነ ገለጸ

ሉቃስ 11:14-36

  • “በአምላክ ጣት” አጋንንትን አስወጣ

  • የእውነተኛ ደስታ ምንጭ

ኢየሱስ ስለ ጸሎት በድጋሚ አስተምሮ መጨረሱ ነው፤ ሆኖም በአገልግሎቱ ወቅት ከአንድ ጊዜ በላይ የተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ይህ ብቻ አይደለም። በገሊላ ተአምራት በፈጸመበት ጊዜ አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ ኃይል እንደሆነ የሚገልጽ የሐሰት ክስ ተሰንዝሮበት ነበር። አሁን ደግሞ በይሁዳ እንዲህ ያለ ክስ በድጋሚ ቀረበበት።

ኢየሱስ አንድን ሰው መናገር እንዳይችል አግዶት የነበረውን ጋኔን ሲያስወጣ ሕዝቡ በጣም ተደነቀ። አንዳንድ ተቺዎች ግን በዚህ አልተደሰቱም። ከዚህ ቀደም ያነሱትን የሐሰት ክስ በመድገም “አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል ነው” አሉ። (ሉቃስ 11:15) ሌሎቹ ደግሞ ስለ ኢየሱስ ማንነት የሚመሠክር ተጨማሪ ማስረጃ ስለፈለጉ ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት።

ኢየሱስ ሊፈትኑት እንዳሰቡ ስላወቀ በገሊላ ለነበሩት ተቺዎች የሰጠውን ዓይነት መልስ ሰጣቸው። እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ እንደሚጠፋ በመግለጽ “ሰይጣን እርስ በርሱ ከተከፋፈለ መንግሥቱ እንዴት ይቆማል?” ሲል ጠየቃቸው። ከዚያም ኢየሱስ “አጋንንትን የማስወጣው በአምላክ ጣት ከሆነ የአምላክ መንግሥት ሳታስቡት ደርሶባችኋል ማለት ነው” ብሎ በግልጽ ነገራቸው።—ሉቃስ 11:18-20

ኢየሱስ ስለ “አምላክ ጣት” መጥቀሱ አድማጮቹ ቀደም ባሉት ዘመናት በእስራኤል ታሪክ ውስጥ የተፈጸመውን ነገር እንዲያስታውሱ ሊያደርጋቸው ይገባል። በፈርዖን ቤተ መንግሥት ውስጥ ሙሴ ተአምር ሲፈጽም ያዩት ሰዎች “ይህ የአምላክ ጣት ነው!” ብለው ነበር። አሥርቱ ትእዛዛት በሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች ላይ የተጻፉትም “በአምላክ ጣት” ነው። (ዘፀአት 8:19፤ 31:18) በተመሳሳይም ኢየሱስ አጋንንትን የሚያስወጣውና ሕሙማንን የሚፈውሰው “በአምላክ ጣት” ማለትም በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም በሥራ ላይ ባለው የአምላክ ኃይል ነው። በእርግጥም ተቃዋሚዎቹ የአምላክ መንግሥት ሳያስቡት ደርሶባቸዋል፤ ምክንያቱም አምላክ የመረጠው የዚህ መንግሥት ንጉሥ ማለትም ኢየሱስ በመካከላቸው ሆኖ እነዚህን ሥራዎች እያከናወነ ነው።

በደንብ ታጥቆ ቤቱን የሚጠብቅን ብርቱ ሰው ከእሱ ይበልጥ ብርቱ የሆነ ሰው ሲያጠቃውና ሲያሸንፈው ኃይሉን እንደሚያሳይ ሁሉ ኢየሱስም አጋንንትን ማስወጣት መቻሉ በሰይጣን ላይ ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ኢየሱስ ርኩስ መንፈስ ስለወጣለት ሰው የተናገረውን ምሳሌም ደገመው። ሰውየው ባዶውን ቦታ በመልካም ነገሮች ካልሞላው ርኩሱ መንፈስ ከሌሎች ሰባት መናፍስት ጋር ሆኖ ይመለስበታል፤ ይህም የሰውየው ሁኔታ ከቀድሞው የከፋ እንዲሆን ያደርጋል። (ማቴዎስ 12:22, 25-29, 43-45) የእስራኤል ብሔር ሁኔታም እንዲሁ ነው።

የኢየሱስን ትምህርት የምታዳምጥ አንዲት ሴት በዚህ ጊዜ በአድናቆት ስሜት ተገፋፍታ “አንተን የተሸከመች ማህፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ደስተኞች ናቸው!” አለችው። አይሁዳውያን ሴቶች የነቢይ በተለይ ደግሞ የመሲሑ እናት መሆን ይፈልጋሉ። በመሆኑም ይህች ሴት፣ ማርያም እንዲህ ያለ መምህር እናት በመሆኗ በጣም ደስተኛ እንደምትሆን አስባ ይሆናል። ኢየሱስ ግን የእውነተኛ ደስታ ምንጭ ምን እንደሆነ በመግለጽ ሴትዮዋን አረማት፤ “ደስተኞችስ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው!” አላት። (ሉቃስ 11:27, 28) ኢየሱስ፣ ማርያም ልዩ ክብር ሊሰጣት እንደሚገባ ገልጾ አያውቅም። ወንድም ሆነ ሴት፣ ማንኛውም ሰው እውነተኛ ደስታ የሚያገኘው በሥጋዊ ዝምድና ወይም በሥራው ውጤት ሳይሆን ታማኝ የአምላክ አገልጋይ በመሆን ነው።

ኢየሱስ በገሊላ እንዳደረገው ሁሉ በይሁዳም ሰዎቹ ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው በመጠየቃቸው አውግዟቸዋል። “ከዮናስ ምልክት” በስተቀር ምንም ምልክት እንደማይሰጣቸው ተናገረ። ዮናስ ምልክት የሆነው፣ ለሦስት ቀናት በዓሣ ሆድ ውስጥ በመቆየቱ እንዲሁም የነነዌን ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ ባነሳሳቸው ድፍረት የተሞላበት ምሥክርነቱ ነው። “ነገር ግን ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ” በማለት ኢየሱስ ተናገረ። (ሉቃስ 11:29-32) ኢየሱስ፣ የሳባ ንግሥት በጥበቡ ተደንቃ ልትጎበኘው ከመጣችው ከሰለሞንም ይበልጣል።

ኢየሱስ አክሎም እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው መብራት ካበራ በኋላ በሰዋራ ቦታ አያስቀምጠውም ወይም እንቅብ አይደፋበትም፤ ከዚህ ይልቅ . . . በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል።”  (ሉቃስ 11:33) ይህን ሲል፣ ለእነዚህ ሰዎች መስበክና በእነሱ ፊት ተአምራት መፈጸም ብርሃንን እንደ መደበቅ መሆኑን መግለጹ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች ዓይናቸው በአንድ ነገር ላይ ያተኮረ ባለመሆኑ ኢየሱስ ያከናወናቸውን ነገሮች ዓላማ መገንዘብ አልቻሉም።

ኢየሱስ በዚያ ወቅት ከአንድ ሰው ላይ ጋኔን በማስወጣት ዱዳ የነበረው ሰው መናገር እንዲችል አድርጓል። ይህ ተአምር ሕዝቡ አምላክን እንዲያከብሩና ይሖዋ እያከናወነ ያለውን ነገር ለሌሎች እንዲናገሩ ሊያነሳሳቸው ይገባል። ኢየሱስ እንዲህ በማለት ተቺዎቹን ያስጠነቀቀው ለዚህ ነው፦ “በውስጥህ ያለው ብርሃን፣ ጨለማ እንዳይሆን ተጠንቀቅ። እንግዲህ መላ ሰውነትህ ምንም ጨለማ ሳይኖርበት ብሩህ ከሆነ፣ ልክ ብርሃን እንደሚፈነጥቅልህ መብራት ሁለንተናህ ብሩህ ይሆናል።”—ሉቃስ 11:35, 36