በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 64

ይቅር ባይ የመሆን አስፈላጊነት

ይቅር ባይ የመሆን አስፈላጊነት

ማቴዎስ 18:21-35

  • ሰባት ጊዜ ይቅር ማለት?

  • ይቅር ባይ ስላልሆነው ባሪያ የተነገረ ምሳሌ

ጴጥሮስ፣ በወንድሞች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር ሁለቱ ብቻ ሆነው እንዴት ሊፈቱት እንደሚችሉ ኢየሱስ የሰጠውን ምክር ሰምቷል። ይሁንና ጴጥሮስ፣ አንድ ሰው እንዲህ ያለ ጥረት ማድረግ ያለበት ምን ያህል ጊዜ እንደሆነ ማወቅ የፈለገ ይመስላል።

በመሆኑም ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ይቅር ልበለው?” በማለት ጠየቀ። አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች አንድ ሰው እስከ ሦስት ጊዜ ይቅር ማለት እንዳለበት ያስተምራሉ። ስለዚህ ጴጥሮስ “እስከ ሰባት ጊዜ” ይቅር ካለ በጣም ደግ እንደሆነ ተሰምቶት ይሆናል።—ማቴዎስ 18:21

ሆኖም አንድ ሰው ምን ያህል ጊዜ እንደበደለ መቁጠር፣ ኢየሱስ ከሰጠው ትምህርት ጋር ይቃረናል። በመሆኑም ኢየሱስ “እስከ 77 ጊዜ እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” በማለት ጴጥሮስን አረመው። (ማቴዎስ 18:22) በሌላ አባባል ምንጊዜም ይቅር ባይ መሆን እንዳለበት መናገሩ ነው። ጴጥሮስ ወንድሙን ምን ያህል ጊዜ ይቅር ማለት እንዳለበት ገደብ ሊያበጅ አይገባም።

ቀጥሎም ኢየሱስ፣ ጴጥሮስና ሌሎች ደቀ መዛሙርቱ ይቅር የማለት ግዴታ እንዳለባቸው ለማስገንዘብ አንድ ምሳሌ ነገራቸው። ምሳሌው፣ መሐሪ የሆነውን ጌታውን አርዓያ ስላልተከተለ አንድ ባሪያ የሚገልጽ ነው። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ንጉሥ ከባሪያዎቹ ጋር ሒሳብ መተሳሰብ ፈለገ። በዚህ ጊዜ ብዙ ዕዳ ያለበትን ይኸውም 10,000 ታላንት [60,000,000 ዲናር] የተበደረን አንድ ባሪያ ወደ እሱ አመጡ። ሰውየው ዕዳውን መክፈል የሚችልበት ምንም መንገድ የለውም። በመሆኑም ንጉሡ ይህ ባሪያ፣ ሚስቱ እንዲሁም ልጆቹ ተሸጠው ዕዳው እንዲከፈል አዘዘ። ባሪያው ይህን ሲሰማ ጌታው እግር ላይ ወድቆ “ጌታዬ ሆይ፣ እባክህ ታገሠኝ፤ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ” ሲል ለመነው።—ማቴዎስ 18:26

ንጉሡም አዘነለትና ባሪያው የነበረበትን ከፍተኛ ዕዳ በመሰረዝ ምሕረት አደረገለት። ይህ ባሪያ፣ ንጉሡ ምሕረት ካደረገለት በኋላ ወጥቶ ሲሄድ 100 ዲናር ከእሱ የተበደረ ሌላ ባሪያ አገኘ። ባሪያውን ያዘውና አንገቱን አንቆ “ያለብህን ዕዳ ክፈለኝ” አለው። ባልንጀራው የሆነው ባሪያም  እግሩ ላይ ወድቆ “ወንድሜ ሆይ፣ እባክህ ታገሠኝ፤ እከፍልሃለሁ” ብሎ ለመነው። (ማቴዎስ 18:28, 29) ይሁንና ዕዳውን ንጉሡ ይቅር ያለው ባሪያ የጌታውን አርዓያ አልተከተለም። እሱ ከነበረበት ዕዳ አንጻር በጣም ትንሽ ዕዳ ያለበትን ባሪያ፣ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ ወህኒ ቤት አሳሰረው።

ኢየሱስ በመቀጠል፣ ይህ ባሪያ የፈጸመውን ምሕረት የጎደለው ድርጊት የተመለከቱ ሌሎች ባሪያዎች ሁኔታውን ሄደው ለጌታቸው እንደነገሩት ገለጸ፤ ጌታቸውም ተቆጥቶ ባሪያውን አስጠራውና እንዲህ አለው፦ “አንተ ክፉ ባሪያ፣ ስለተማጸንከኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውኩልህ። ታዲያ እኔ ምሕረት እንዳደረግኩልህ ሁሉ አንተስ ባልንጀራህ ለሆነው ባሪያ ምሕረት ልታደርግለት አይገባም ነበር?” ንጉሡም ምሕረት ያላደረገውን ባሪያ፣ ያለበትን ዕዳ ሁሉ እስኪከፍል ድረስ ለወህኒ ቤት ጠባቂዎቹ አሳልፎ ሰጠው። ኢየሱስ “እናንተም እያንዳንዳችሁ ወንድማችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ በሰማይ ያለው አባቴ እንደዚሁ ያደርግባችኋል” በማለት ደመደመ።—ማቴዎስ 18:32-35

የይቅር ባይነትን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ የሚያደርግ እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ነው! አምላክ ከፍተኛ የሆነውን የኃጢአት ዕዳችንን ይቅር ብሎናል። አንድ ክርስቲያን ወንድማችን፣ ምንም ዓይነት በደል ቢፈጽምብን እኛ ካለብን ዕዳ ጋር ሲወዳደር አነስተኛ ነው። ከዚህም በላይ ይሖዋ፣ አንድ ጊዜ ሳይሆን በሺዎች ለሚቆጠሩ ጊዜያት ይቅር ብሎናል። ታዲያ እኛስ ብንበደልም እንኳ ወንድማችንን በተደጋጋሚ ጊዜያት ይቅር ልንለው አይገባም? ኢየሱስ በተራራው ስብከት ላይ እንዳስተማረው አምላክ “የበደሉንን ይቅር እንዳልን በደላችንን ይቅር” ይለናል።—ማቴዎስ 6:12