በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 96

ኢየሱስ ለአንድ ሀብታም አለቃ መልስ ሰጠ

ኢየሱስ ለአንድ ሀብታም አለቃ መልስ ሰጠ

ማቴዎስ 19:16-30 ማርቆስ 10:17-31 ሉቃስ 18:18-30

  • አንድ ሀብታም ሰው ስለ ዘላለም ሕይወት ጠየቀ

ኢየሱስ በፔሪያ አቋርጦ ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዘ ነው። አንድ ሀብታም ወጣት ወደ ኢየሱስ እየሮጠ መጥቶ በፊቱ ተንበረከከ። ሰውየው ‘ከአይሁዳውያን አለቆች አንዱ’ ተብሎ ተጠርቷል፤ ምናልባትም በአካባቢው የሚገኝ ምኩራብ አለቃ አሊያም የሳንሄድሪን ሸንጎ አባል ሊሆን ይችላል። ወጣቱ “ጥሩ መምህር ሆይ፣ የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” ሲል ጠየቀ።—ሉቃስ 8:41፤ 18:18፤ 24:20

ኢየሱስም “ለምን ጥሩ ብለህ ትጠራኛለህ? ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም” በማለት መለሰለት። ወጣቱ “ጥሩ” የሚለውን ቃል የተጠቀመበት እንደ ማዕረግ ስም አድርጎ ሳይሆን አይቀርም፤ ረቢዎች እንዲህ ያደርጋሉ። ኢየሱስ ጥሩ አስተማሪ ቢሆንም “ጥሩ” በሚለው የማዕረግ ስም መጠራት የሚችለው አምላክ ብቻ እንደሆነ ለሰውየው አሳወቀው።

ኢየሱስ “ሕይወት ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ዘወትር ትእዛዛቱን ጠብቅ” በማለት መከረው። በመሆኑም ወጣቱ “የትኞቹን?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስ ከአሥርቱ ትእዛዛት አምስቱን ይኸውም “አትግደል፣ አታመንዝር፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመሥክር፣ አባትህንና እናትህን አክብር” የሚሉትን ጠቀሰለት። አክሎም “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለውን ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ትእዛዝ ነገረው።—ማቴዎስ 19:17-19

ወጣቱ “እነዚህን ሁሉ ስጠብቅ ኖሬአለሁ፤ ታዲያ አሁን የሚጎድለኝ ነገር ምንድን ነው?” አለ። (ማቴዎስ 19:20) ይህን የጠየቀው፣ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ብቁ እንዲሆን የሚያስችለው አንድ ጥሩ ነገር ማድረግ እንዳለበት ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ፣ ሰውየው በቅንነት እንደጠየቀው ስለተገነዘበ “ወደደው።” (ማርቆስ 10:21) ይሁንና ይህ ወጣት፣ እንቅፋት የሚሆንበት አንድ ነገር አለ።

ወጣቱ ቁሳዊ ንብረቶቹን ስለሚወድ ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ “አንድ ነገር ይጎድልሃል፤ ሂድና ያለህን ነገር ሁሉ ሸጠህ ገንዘቡን ለድሆች ስጥ፤ በሰማይም ውድ ሀብት ታገኛለህ፤ ደግሞም መጥተህ ተከታዬ ሁን።” ሀብታሙ ሰው፣ ገንዘቡን መልሰው ሊሰጡት ለማይችሉት ለድሆች ማከፋፈልና የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን ይችላል። ወጣቱ፣  ኢየሱስ ያለውን ሲሰማ በጣም ቅር ተሰኝቶ ተነስቶ ሄደ፤ ኢየሱስ ይህን ሲመለከት ሳያዝን አልቀረም። ወጣቱ ሀብትን ይኸውም ያለውን “ብዙ ንብረት” መውደዱ እውነተኛውን ውድ ሀብት እንዳያይ አሳውሮታል። (ማርቆስ 10:21, 22) ኢየሱስ “ገንዘብ ላላቸው ሰዎች ወደ አምላክ መንግሥት መግባት ምንኛ አስቸጋሪ ነው!” አለ።—ሉቃስ 18:24

ደቀ መዛሙርቱ በዚህም ሆነ ኢየሱስ ቀጥሎ በተናገረው ነገር በጣም ተገረሙ፤ “ሀብታም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲሰሙ “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ ከተናገረው አንጻር፣ መዳን ሊደረስበት የማይችል ከባድ ነገር ነው? ኢየሱስ ትኩር ብሎ እያያቸው “በሰዎች ዘንድ የማይቻል፣ በአምላክ ዘንድ ይቻላል” በማለት መለሰ።—ሉቃስ 18:25-27

ጴጥሮስ፣ ከሀብታሙ ሰው የተለየ ምርጫ እንዳደረጉ በመጥቀስ “እነሆ፣ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ የምናገኘው ምን ይሆን?” አለው። ኢየሱስም ያደረጉት ትክክለኛ ምርጫ በስተመጨረሻ ምን እንደሚያስገኝ ሲገልጽ እንዲህ አለ፦ “ሁሉም ነገር አዲስ በሚሆንበት ጊዜ የሰው ልጅ፣ ክብራማ በሆነው ዙፋኑ ላይ ሲቀመጥ እኔን የተከተላችሁኝ እናንተ በ12 ዙፋኖች ላይ ተቀምጣችሁ በ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ።”—ማቴዎስ 19:27, 28

ኢየሱስ ይህን ሲል፣ ወደፊት በምድር ላይ ሁሉም ነገር አዲስ የሚሆንበትን ይኸውም በኤደን የአትክልት ስፍራ የነበረው ዓይነት ሁኔታ የሚሰፍንበትን ጊዜ ማመልከቱ ነው። ጴጥሮስና ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት፣ ገነት በሆነች ምድር ላይ ከኢየሱስ ጋር የመግዛት መብት ያገኛሉ፤ በእርግጥም ይህ ማንኛውንም ዓይነት መሥዋዕትነት ቢከፍሉለት የማያስቆጭ ሽልማት ነው!

ይሁን እንጂ ሽልማት የሚያገኙት ወደፊት ብቻ አይደለም። ደቀ መዛሙርቱ አሁንም ቢሆን የሚያገኙት ወሮታ አለ። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ለአምላክ መንግሥት ሲል ቤትን ወይም ሚስትን ወይም ወንድሞችን ወይም ወላጆችን ወይም ልጆችን የተወ ሁሉ፣ አሁን በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ፣ በሚመጣው ሥርዓት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛል።”—ሉቃስ 18:29, 30

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ወደ የትኛውም የዓለም ክፍል ቢሄዱ፣ ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር የሚኖራቸው ዝምድና ከሥጋ ቤተሰባቸው ጋር ካላቸው ይበልጥ የቀረበና ውድ ነው። የሚያሳዝነው ግን ወጣቱ ሀብታም አለቃ፣ ይህን በረከት ብቻ ሳይሆን በሰማይ ባለው የአምላክ መንግሥት ሕይወት የማግኘት አጋጣሚንም የሚያጣ ይመስላል።

ኢየሱስ “ሆኖም ፊተኞች የሆኑ ብዙዎች ኋለኞች፣ ኋለኞች የሆኑ ደግሞ ፊተኞች ይሆናሉ” ሲል አክሎ ተናገረ። (ማቴዎስ 19:30) ይህን ሲል ምን ማለቱ ነው?

ሀብታሙ አለቃ፣ ከአይሁዳውያን መሪዎች አንዱ በመሆኑ “ፊተኞች” ከተባሉት መካከል ነው። የአምላክን ሕግ ስለሚጠብቅ አካሄዱ ጥሩ ከመሆኑም ሌላ ከእሱ ብዙ ሊጠበቅ ይችላል። ሆኖም በሕይወቱ ውስጥ ከምንም በላይ ያስቀደመው ሀብትንና ንብረትን ነው። ከዚህ በተቃራኒ፣ ተራው ሕዝብ የኢየሱስ ትምህርት እውነት እንደሆነና ሕይወት እንደሚያስገኝ ተገንዝቧል። እነዚህ ሰዎች በምሳሌያዊ አነጋገር “ኋለኞች” የነበሩ ቢሆንም አሁን “ፊተኞች” እየሆኑ ነው። በሰማይ በዙፋኖች ላይ ተቀምጠው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ከኢየሱስ ጋር የመግዛት ተስፋ አላቸው።