በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 20

በቃና የፈጸመው ሁለተኛ ተአምር

በቃና የፈጸመው ሁለተኛ ተአምር

ማርቆስ 1:14, 15 ሉቃስ 4:14, 15 ዮሐንስ 4:43-54

  • ኢየሱስ “የአምላክ መንግሥት ቀርቧል” እያለ ሰበከ

  • አጠገቡ ያልነበረን አንድ ልጅ ፈወሰ

ኢየሱስ በሰማርያ ሁለት ቀን ካሳለፈ በኋላ ወዳደገበት አካባቢ ጉዞውን ቀጠለ። በይሁዳ ረዘም ላለ ጊዜ የስብከት ዘመቻ ሲያካሂድ ቆይቷል፤ ወደ ገሊላ የተመለሰው ግን ለእረፍት አይደለም። እንዲያውም ባደገበት አካባቢ አገልግሎቱን ይበልጥ በስፋት ማከናወን ጀመረ። በእርግጥ በዚያ ጥሩ አቀባበል እንደማያገኝ ጠብቆ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም “ነቢይ በገዛ አገሩ እንደማይከበር” እሱ ራሱ ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:44) ደቀ መዛሙርቱም ከእሱ ጋር ከመቆየት ይልቅ ወደየቤተሰቦቻቸው ተመልሰው የቀድሞ ሥራቸውን ማከናወን ቀጠሉ።

ለመሆኑ ኢየሱስ የሚሰብከው መልእክት ምንድን ነው? “የአምላክ መንግሥት ቀርቧል። ንስሐ ግቡ፤ በምሥራቹም እመኑ” የሚል ነው። (ማርቆስ 1:15) ምን ምላሽ አገኘ? በርካታ የገሊላ ሰዎች ኢየሱስን ተቀብለውታል፤ እንዲሁም አክብረውታል። ይህን ያደረጉት ግን በሚሰብከው መልእክት የተነሳ ብቻ አይደለም። አንዳንድ የገሊላ ሰዎች ከተወሰኑ ወራት በፊት በኢየሩሳሌም በተከበረው የፋሲካ በዓል ላይ ተገኝተው ስለነበር ኢየሱስ የፈጸማቸውን አስደናቂ ምልክቶች አይተዋል።—ዮሐንስ 2:23

ኢየሱስ በገሊላ ያከናወነውን ታላቅ አገልግሎት የጀመረው የት ነው? በአንድ ሠርግ ላይ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ በለወጠበት በቃና ሳይሆን አይቀርም። ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ቃና በመጣበት በዚህ ወቅት አንድ ልጅ በጠና ታምሞ ሊሞት እንደተቃረበ አወቀ። የልጁ አባት፣ ከጊዜ በኋላ የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ ያስቆረጠው የንጉሥ ሄሮድስ አንቲጳስ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን ነው። ባለሥልጣኑ፣ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ቃና መምጣቱን ሰማ። በመሆኑም ኢየሱስን ለማግኘት በቅፍርናሆም ከሚገኘው ቤቱ ተነስቶ ወደ ቃና መጣ። በሐዘን የተዋጠው ይህ ባለሥልጣን “ጌታዬ፣ ልጄ ከመሞቱ በፊት እባክህ በቶሎ ድረስ” በማለት ኢየሱስን ለመነው።—ዮሐንስ 4:49

ኢየሱስ የሰጠው መልስ ሰውየውን ሳያስገርመው አልቀረም፤ “ሂድ፤ ልጅህ ድኗል” አለው። (ዮሐንስ 4:50) የሄሮድስ ባለሥልጣንም የኢየሱስን ቃል ስላመነ ወደ ቤቱ ለመመለስ ጉዞውን ተያያዘው። መንገድ ላይ እያለ ከባሪያዎቹ ጋር ተገናኘ፤ ባሪያዎቹ የምሥራች ሊያበስሩት ቸኩለዋል። ልጁ በሕይወት እንዳለና ደህና እንደሆነ ነገሩት! ባለሥልጣኑም ምን እንደተፈጸመ በዝርዝር ማወቅ ስለፈለገ ‘የተሻለው ስንት ሰዓት ላይ ነው?’ ብሎ ጠየቃቸው።

እነሱም “ትናንት ሰባት ሰዓት ላይ ትኩሳቱ ለቀቀው” ብለው መለሱለት።—ዮሐንስ 4:52

ባለሥልጣኑም ልጁ የተሻለው ኢየሱስ “ልጅህ ድኗል” ባለው ሰዓት እንደሆነ ተገነዘበ። ከዚያም፣ ባሪያዎች ለመቅጠር የሚያስችል ሀብት ያለው ይህ ሰው ከመላው ቤተሰቡ ጋር የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሆነ።

ኢየሱስ፣ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ በመለወጥና እሱ ካለበት ቦታ 26 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሆን ርቀት ላይ የሚገኝን አንድ ልጅ በመፈወስ በቃና ሁለት ተአምራት ፈጽሟል። እርግጥ፣ ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት እነዚህ ብቻ አይደሉም። ሆኖም ይህን ልጅ መወፈሱ ወደ ገሊላ መመለሱን የሚያመለክት በመሆኑ ጎላ ያለ ትርጉም አለው። ኢየሱስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ነቢይ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፤ ይሁንና ይህ ነቢይ ‘በገዛ አገሩ ምን ያህል ይከበር ይሆን’?

ይህ ጥያቄ፣ ኢየሱስ ወዳደገባት ወደ ናዝሬት ሲሄድ መልስ ያገኛል። እዚያ ምን ያጋጥመው ይሆን?