በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 69

አባታቸው አብርሃም ነው ወይስ ዲያብሎስ?

አባታቸው አብርሃም ነው ወይስ ዲያብሎስ?

ዮሐንስ 8:37-59

  • አይሁዳውያን አባታቸው አብርሃም እንደሆነ ተናገሩ

  • አብርሃም ከመወለዱ በፊት ኢየሱስ ነበር

ኢየሱስ አሁንም ያለው ኢየሩሳሌም ነው፤ ወደዚህ የመጣው የዳስ በዓልን ለማክበር ሲሆን እዚያው እያለ አስፈላጊ የሆኑ እውነቶችን ማስተማሩን ቀጠለ። ኢየሩሳሌም ያሉ አንዳንድ አይሁዳውያን “እኛ የአብርሃም ዘር ነን፤ ለማንም ባሪያዎች ሆነን አናውቅም” ብለውታል። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “የአብርሃም ዘር እንደሆናችሁ አውቃለሁ። ሆኖም ቃሌ በእናንተ ውስጥ ሥር ስለማይሰድ ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። እኔ ከአባቴ ጋር ሳለሁ ያየሁትን ነገር እናገራለሁ፤ እናንተ ግን ከአባታችሁ የሰማችሁትን ነገር ታደርጋላችሁ።”—ዮሐንስ 8:33, 37, 38

ኢየሱስ መናገር የፈለገው ነገር ለመረዳት የሚከብድ አይደለም፦ የእሱ አባት ከእነሱ አባት የተለየ ነው። አይሁዳውያኑ ግን ኢየሱስ የተናገረው ስላልገባቸው በድጋሚ “አባታችን አብርሃም ነው” አሉት። (ዮሐንስ 8:39፤ ኢሳይያስ 41:8) የአብርሃም ዘሮች መሆናቸው ግልጽ ነው። በመሆኑም የአምላክ ወዳጅ የሆነው አብርሃም መንፈሳዊ አባታቸው እንደሆነ ተሰምቷቸዋል።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ “የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ ኖሮ አብርሃም የሠራውን ትሠሩ ነበር” በማለት የሚያስደነግጥ ምላሽ ሰጣቸው። በእርግጥ ልጅ የሆነ ሁሉ የአባቱን ምሳሌ ይከተላል። ኢየሱስ አክሎ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ግን ከአምላክ የሰማሁትን እውነት የነገርኳችሁን እኔን ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። አብርሃም እንዲህ አላደረገም።” ከዚያም “እናንተ እየሠራችሁ ያላችሁት የአባታችሁን ሥራ ነው” በማለት ግራ ሊያጋባቸው የሚችል ነገር ተናገረ።—ዮሐንስ 8:39-41

አይሁዳውያኑ ግን ኢየሱስ ስለ ማን እየተናገረ እንዳለ አሁንም አልገባቸውም። ሕጋዊ ልጆች መሆናቸውን ሲገልጹ “እኛስ በዝሙት የተወለድን አይደለንም፤ እኛ አንድ አባት አለን፤ እሱም አምላክ ነው” አሉ። ይሁንና አባታቸው በእርግጥ አምላክ ነው? ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “አምላክ አባታችሁ ቢሆን ኖሮ እኔ ወደዚህ የመጣሁት ከእሱ ዘንድ ስለሆነ በወደዳችሁኝ ነበር። እሱ ላከኝ እንጂ እኔ በራሴ ተነሳስቼ አልመጣሁም።” ከዚያም ኢየሱስ “እየተናገርኩት ያለው ነገር የማይገባችሁ ለምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ካቀረበላቸው በኋላ “ቃሌን መስማት ስለማትችሉ ነው” በማለት ራሱ መልሱን ሰጠ።—ዮሐንስ 8:41-43

ኢየሱስ፣ እሱን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆን ምን እንደሚያስከትል ለመግለጽ ሞክሯል። አሁን ግን በግልጽ “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት መፈጸም ትሻላችሁ” አላቸው። አባታቸው ምን ዓይነት ባሕርይ አለው? ኢየሱስ የአባታቸውን ማንነት በግልጽ ሲናገር “እሱ በራሱ መንገድ መሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ . . . በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም” ብሏል። አክሎም “ከአምላክ የሆነ የአምላክን ቃል ይሰማል። እናንተ ግን ከአምላክ ስላልሆናችሁ አትሰሙም” አላቸው።—ዮሐንስ 8:44, 47

አይሁዳውያኑ በዚህ ውግዘት ስለተናደዱ “‘አንተ ሳምራዊ ነህ፤ ደግሞም ጋኔን አድሮብሃል’ ማለታችን ትክክል አይደለም?” አሉት። ኢየሱስን “ሳምራዊ” ብለው የጠሩት ለእሱ ያላቸውን ንቀት ለመግለጽ ነው። ኢየሱስ ግን ስድባቸውን ችላ በማለት “እኔ አባቴን አከብራለሁ እንጂ ጋኔን የለብኝም፤ እናንተ ግን ታቃልሉኛላችሁ” አላቸው። ድርጊታቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤ ኢየሱስ “ማንም ሰው ቃሌን የሚጠብቅ ከሆነ ፈጽሞ ሞትን አያይም” በማለት ቀጥሎ የገባው ቃል ይህን ያሳያል። እርግጥ ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱም ሆነ እሱን የሚከተሉ ሌሎች ሰዎች ቃል በቃል ፈጽሞ አይሞቱም ማለቱ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዘላለማዊ ጥፋትን ወይም ትንሣኤ የሌለውን “ሁለተኛውን ሞት” እንደማያዩ መግለጹ ነው።—ዮሐንስ 8:48-51፤ ራእይ 21:8

አይሁዳውያኑ ግን ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ቃል በቃል በመረዳታቸው እንዲህ አሉ፦ “አሁን በእርግጥ ጋኔን እንዳለብህ ተረዳን። አብርሃም ሞቷል፤ ነቢያትም ሞተዋል፤ አንተ ግን ‘ማንም ሰው ቃሌን የሚጠብቅ ከሆነ ፈጽሞ ሞትን አይቀምስም’ ትላለህ። አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህ እንዴ? . . . ለመሆኑ አንተ ማን ነኝ ልትል ነው?”—ዮሐንስ 8:52, 53

ኢየሱስ፣ መሲሕ መሆኑን እየጠቆመ እንደሆነ ግልጽ ነው። ሆኖም ስለ ማንነቱ ለቀረበለት ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ እንዲህ አለ፦ “እኔ ራሴን የማከብር ከሆነ ክብሬ ከንቱ ነው። እኔን የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን ነው የምትሉት አባቴ ነው። ሆኖም እናንተ አላወቃችሁትም፤  እኔ ግን አውቀዋለሁ። አላውቀውም ብል እንደ እናንተ ውሸታም መሆኔ ነው።”—ዮሐንስ 8:54, 55

ኢየሱስ በመቀጠል ታማኙን ቅድመ አያታቸውን ድጋሚ ጠቀሰና “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን እንደሚያይ ተስፋ በማድረግ እጅግ ተደሰተ፤ አይቶትም ደስ ተሰኘ” አለ። አብርሃም፣ አምላክ የገባውን ቃል በማመን የመሲሑን መምጣት በጉጉት ይጠባበቅ ነበር። አይሁዳውያኑ ግን “አንተ ገና 50 ዓመት እንኳ ያልሞላህ፣ አብርሃምን አይቼዋለሁ ትላለህ?” በማለት የተናገረውን እንዳላመኑት ገለጹ። ኢየሱስም “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ ነበርኩ” በማለት መለሰ። ይህን ሲል ሰው ከመሆኑ በፊት ኃያል መንፈሳዊ አካል ሆኖ በሰማይ ይኖር የነበረበትን ጊዜ ማመልከቱ ነው።—ዮሐንስ 8:56-58

ኢየሱስ ከአብርሃም በፊት ይኖር እንደነበር መናገሩ አይሁዳውያንን በጣም ስላናደዳቸው ሊወግሩት ተነሱ። ሆኖም ኢየሱስ ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ከዚያ ሄደ።