ምዕራፍ 7
ኮከብ ቆጣሪዎች ወደ ኢየሱስ መጡ
-
ኮከብ ቆጣሪዎች አንድን “ኮከብ” ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም ከዚያም ወደ ኢየሱስ ሄዱ
የተወሰኑ ሰዎች ከምሥራቅ መጡ። እነዚህ ሰዎች የከዋክብትን አቀማመጥ በማጥናት፣ በሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚከሰቱ ነገሮች ያላቸውን ትርጉም እንደሚያውቁ የሚናገሩ ኮከብ ቆጣሪዎች ናቸው። (ኢሳይያስ 47:13) በምሥራቅ በሚገኘው አገራቸው ሳሉ የተመለከቱትን “ኮከብ” ተከትለው በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ተጉዘዋል፤ “ኮከቡ” የመራቸው ግን ወደ ቤተልሔም ሳይሆን ወደ ኢየሩሳሌም ነው።
ኮከብ ቆጣሪዎቹ ኢየሩሳሌም ሲደርሱ “የተወለደው የአይሁዳውያን ንጉሥ የሚገኘው የት ነው? በምሥራቅ ሳለን ኮከቡን በማየታችን ልንሰግድለት መጥተናል” በማለት ጠየቁ።—ማቴዎስ 2:1, 2
ኢየሩሳሌም ያለው ንጉሥ ሄሮድስ ይህን ሲሰማ በጣም ደነገጠ። ስለዚህ የካህናት አለቆችንና ሌሎች የሃይማኖት መሪዎችን ጠርቶ ክርስቶስ የሚወለደው የት እንደሆነ ጠየቃቸው። እነሱም ቅዱሳን መጻሕፍትን መሠረት በማድረግ “በቤተልሔም” እንደሆነ ነገሩት። (ማቴዎስ 2:5፤ ሚክያስ 5:2) በዚህ ጊዜ ሄሮድስ ኮከብ ቆጣሪዎቹን በድብቅ አስጠርቶ “ሄዳችሁ ሕፃኑን በደንብ ፈልጉ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔም ሄጄ እንድሰግድለት መጥታችሁ ንገሩኝ” አላቸው። (ማቴዎስ 2:8) ሆኖም ሄሮድስ ልጁን ለማግኘት የፈለገው ሊገድለው አስቦ ነው!
ኮከብ ቆጣሪዎቹ ከሄዱ በኋላ አንድ አስገራሚ ነገር ተፈጸመ። በምሥራቅ ሳሉ የተመለከቱት “ኮከብ” ከፊት ከፊታቸው ይሄድ ጀመር። ይህ “ኮከብ” እነሱን ለመምራት የተዘጋጀ እንጂ ተራ ኮከብ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ኮከብ ቆጣሪዎቹ፣ “ኮከቡ” ዮሴፍና ማርያም ከትንሽ ልጃቸው ጋር ከሚኖሩበት ቤት በላይ እስኪቆም ድረስ ተከተሉት።
ኮከብ ቆጣሪዎቹ ቤቱ ውስጥ ሲገቡ ማርያምን ከትንሹ ኢየሱስ ጋር አገኟት። በዚህ ጊዜ ኮከብ ቆጣሪዎቹ ለኢየሱስ ሰገዱለት። ከዚያም ወርቅ፣ ነጭ ዕጣንና ከርቤ በስጦታ አበረከቱለት። በኋላ ላይ ወደ ሄሮድስ ሊሄዱ ሲሉ አምላክ ይህን እንዳያደርጉ በሕልም አስጠነቀቃቸው። በመሆኑም በሌላ መንገድ አድርገው ወደ አገራቸው ተመለሱ።
ኮከብ ቆጣሪዎቹን ሲመራ የነበረውን “ኮከብ” ያዘጋጀው ማን ይመስልሃል? “ኮከቡ” በቤተልሔም ወደነበረው ወደ ኢየሱስ በቀጥታ እንዳልመራቸው አስታውስ። ከዚህ ይልቅ የመራቸው ከንጉሥ ሄሮድስ ጋር ወደተገናኙበት ወደ ኢየሩሳሌም ነው፤ ሄሮድስ ደግሞ ኢየሱስን መግደል ፈለገ። ደግሞም ኢየሱስ የት እንዳለ ኮከብ ቆጣሪዎቹ ለሄሮድስ እንዳይነግሩት አምላክ ጣልቃ ገብቶ ባያስጠነቅቃቸው ኖሮ ሄሮድስ ኢየሱስን ከመግደል አይመለስም። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ እንዲገደል የፈለገው የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን ነው፤ ይህን ዓላማውን ለማሳካትም በዚህ ዘዴ ተጠቅሟል።