በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ልጆቻችሁን አስተምሩ

ኢየሱስ ክርስቶስ—በአእምሯችን ልናስበው የሚገባው እንዴት ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ—በአእምሯችን ልናስበው የሚገባው እንዴት ነው?

በዓለም ዙሪያ በታኅሣሥ ወር ላይ ኢየሱስ አራስ ልጅ ሆኖ የሚያሳዩ ሥዕሎችን ወይም ቅርጻ ቅርጾችን ማየት የተለመደ ነው። በሥዕሎቹ ላይ ኢየሱስ ከብቶች የሚበሉት ድርቆሽ በሚቀመጥበት ገንዳ የሚመስል ግርግም ውስጥ ተኝቶ ይታያል። ይሁን እንጂ ኢየሱስን በአእምሯችን ልናስበው የሚገባው እንደ አራስ ልጅ አድርገን ብቻ ነው? * ከዚህ በበለጠ መንገድ እሱን ማስታወስ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። አንድ ቀን ሌሊት በቤተልሔም አቅራቢያ ሜዳ ላይ የነበሩ እረኞች ካጋጠማቸው ነገር ትምህርት ማግኘት እንችላለን።

አንድ መልአክ በድንገት ለእረኞቹ ተገለጠ። ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “በዛሬው ዕለት በዳዊት ከተማ አዳኝ ተወልዶላችኋል፤ እሱም ጌታ ክርስቶስ ነው።” በተጨማሪም መልአኩ ኢየሱስን “በመጠቅለያ ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ” እንደሚያገኙት ነገራቸው። ወዲያውኑም ሌሎች ብዙ መላእክት ተገለጡላቸውና ‘አምላክን ማመስገን’ ጀመሩ።

መላእክት አምላክን ሲያመሰግኑ ብትሰማ ኖሮ ምን ይሰማህ ነበር?— እረኞቹ በጣም ደስ አላቸው! “አሁኑኑ ወደ ቤተልሔም ሄደን . . . በዚያ የተፈጸመውን ነገር ማየት አለብን” ተባባሉ። እዚያ ሲደርሱ “ማርያምንና ዮሴፍን አገኙ፤ ሕፃኑም በግርግም ተኝቶ ነበር።”

ብዙም ሳይቆይ ሌሎችም ማርያምና ዮሴፍ ወዳሉበት ወደ ቤተልሔም መጡ። እረኞቹ የሆነውን ነገር ሲነግሯቸው ሁሉም ተደነቁ። አንተስ እነዚህን አስደናቂ ነገሮች በማወቅህ አልተደሰትክም?— አምላክን የምንወድ ሁሉ ደስ ይለናል። እስቲ አሁን ደግሞ የኢየሱስ መወለድ በጣም የሚያስደስተው ለምን እንደሆነ እንመልከት። ይህን ለማየት እንድንችል ማርያም ከማግባቷ በፊት ምን እንዳጋጠማት ማወቅ ይኖርብናል።

አንድ ቀን ገብርኤል የተባለ መልአክ ወደ ማርያም መጣ። ገብርኤል ለማርያም ልጅ እንደምትወልድና እሱም ‘ታላቅ እንደሚሆን፤ የልዑሉም ልጅ እንደሚባል’ ቃል ገባላት። በተጨማሪም “ንጉሥ ሆኖ ይገዛል፤ መንግሥቱም መጨረሻ የለውም” አላት።

ማርያም ከወንድ ጋር ግንኙነት አድርጋ ስለማታውቅ ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ማወቅ ፈልጋ ነበር። ስለዚህ ገብርኤል እንዲህ በማለት አስረዳት፦ “የልዑሉም ኃይል በአንቺ ላይ ያርፋል።  ስለሆነም የሚወለደው ልጅ ቅዱስ፣ የአምላክ ልጅ ይባላል።” የአምላክን ልጅ ከሰማይ ወስዶ ሕይወቱን በማርያም ማህፀን ውስጥ በማስገባት ልጅ ሆኖ እንዲወለድ ማድረግ በጣም አስገራሚ ተአምር ነው!

ሦስት “ጠቢባን” እና እረኞች ሕፃኑን ኢየሱስን ለማየት ሲመጡ የሚያሳዩ ሥዕሎችን ወይም ቅርጻ ቅርጾችን አይተህ ታውቃለህ?— በገና ወቅት እንዲህ ዓይነት ምስሎችን ማየት የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ የሚያስተላልፉት መልእክት ትክክል አይደለም። እነዚያ “ጠቢባን” ኮከብ ቆጣሪዎች ነበሩ፤ ይህ ደግሞ አምላክ የሚጠላው ሥራ ነው። ኮከብ ቆጣሪዎቹ ማርያም ወዳለችበት ቦታ ሲደርሱ የሆነውን ነገር እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩ” ይላል። ስለዚህ ኮከብ ቆጣሪዎቹ በመጡ ጊዜ ኢየሱስ በግርግም ውስጥ አልነበረም፤ ከዮሴፍና ከማርያም ጋር በቤት ውስጥ የሚኖር ሕፃን ልጅ ነበር!

ኮከብ ቆጣሪዎቹ ኢየሱስን ሊያገኙት የቻሉት እንዴት ነው?— የመጡት “ኮከቡ” እየመራቸው ነበር፤ ይሁንና ኮከቡ መጀመሪያ የመራቸው ወደ ቤተልሔም ሳይሆን በኢየሩሳሌም ወደነበረው ወደ ንጉሥ ሄሮድስ ነበር። ሄሮድስ ኢየሱስን አግኝቶ ለመግደል ይፈልግ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፦ ኮከብ ቆጣሪዎቹን ወደ ሄሮድስ የመራቸውን ኮከብ የሚመስለውን ነገር ያዘጋጀው ማን ይመስልሃል?— እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ሳይሆን የእሱ ተቃዋሚ ወይም ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው!

በዛሬው ጊዜ ሰይጣን የሚጥረው ሰዎች ኢየሱስ ሁልጊዜ ሕፃን ልጅ እንደሆነ ብቻ አድርገው እንዲያስቡ ነው። ይሁን እንጂ መልአኩ ገብርኤል ለማርያም “ንጉሥ ሆኖ ይገዛል፤ መንግሥቱም መጨረሻ የለውም” ብሏታል። አሁን ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ እየገዛ ነው፤ በቅርቡ ደግሞ የአምላክን ጠላቶች በሙሉ ይደመስሳል። ኢየሱስን በአእምሯችን ልናስበው የሚገባው እንዲህ አድርገን ነው፤ ይህንንም ለሌሎች መንገር ያስፈልገናል።

ከመጽሐፍ ቅዱስህ ላይ

^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።