በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 11

መጥምቁ ዮሐንስ መንገዱን አዘጋጀ

መጥምቁ ዮሐንስ መንገዱን አዘጋጀ

ማቴዎስ 3:1-12 ማርቆስ 1:1-8 ሉቃስ 3:1-18 ዮሐንስ 1:6-8, 15-28

  • ዮሐንስ መስበክና ማጥመቅ ጀመረ

  • ብዙዎች ተጠመቁ፤ ያልተጠመቁም አሉ

ኢየሱስ በ12 ዓመቱ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ካሉት መምህራን ጋር ከተወያየ 17 ዓመታት ገደማ አልፈዋል። ወቅቱ 29 ዓ.ም. የጸደይ ወራት ነው። ብዙ ሰዎች፣ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምዕራብ ባለው ክልል በሙሉ እየሰበከ ስላለውና የኢየሱስ ዘመድ ስለሆነው ስለ ዮሐንስ እያወሩ ነው።

የዮሐንስ አለባበስም ሆነ ንግግር የሰዎችን ትኩረት የሚስብ ነው። ልብሱ ከግመል ፀጉር የተሠራ ሲሆን ወገቡም ላይ የቆዳ ቀበቶ ይታጠቃል። የሚመገበው ደግሞ አንበጣና የዱር ማር ነው። መልእክቱስ? “መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ንስሐ ግቡ” የሚል ነው።—ማቴዎስ 3:2

የዮሐንስ መልእክት የአድማጮቹን ስሜት የሚቀሰቅስ ነው። ብዙዎቹ ንስሐ መግባት ማለትም አስተሳሰባቸውንና አካሄዳቸውን በመለወጥ የቀድሞ ሕይወታቸውን እርግፍ አድርገው መተው እንዳለባቸው ተገነዘቡ። “በኢየሩሳሌምና በመላዋ ይሁዳ እንዲሁም በዮርዳኖስ ዙሪያ ባለው ክልል ሁሉ የሚኖሩ ሰዎች” ወደ ዮሐንስ እየመጡ ነው። (ማቴዎስ 3:5) ወደ ዮሐንስ ከመጡት ሰዎች ብዙዎቹ ንስሐ ገብተዋል። እሱም በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ እያጠለቀ አጠመቃቸው። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው?

የዮሐንስ ጥምቀት፣ ሰዎቹ የአምላክን የቃል ኪዳን ሕግ በመተላለፍ ለፈጸሙት ኃጢአት ከልብ ንስሐ መግባታቸውን የሚያሳይ ምልክት ወይም ማረጋገጫ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 19:4) ለመጠመቅ ብቁ የሆኑት ግን ሁሉም አይደሉም። የሃይማኖት መሪዎች የሆኑ አንዳንድ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ እሱ ሲመጡ ዮሐንስ “የእፉኝት ልጆች” በማለት አውግዟቸዋል። አክሎም እንዲህ አላቸው፦ “ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አፍሩ። ‘እኛ እኮ አባታችን አብርሃም ነው’ ብላችሁ አታስቡ። አምላክ ለአብርሃም ከእነዚህ ድንጋዮች ልጆች ሊያስነሳለት እንደሚችል ልነግራችሁ እወዳለሁ። መጥረቢያው ዛፎቹ ሥር ተቀምጧል። ስለዚህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ተቆርጦ እሳት ውስጥ ይጣላል።”—ማቴዎስ 3:7-10

ዮሐንስ የብዙዎችን ትኩረት በመሳቡ፣ የሚያውጀው መልእክት ኃይለኛ በመሆኑ እንዲሁም በርካቶችን በማጥመቁ ካህናትና ሌዋውያን “አንተ ማን ነህ?” ብለው እንዲጠይቁት ወደ እሱ ተላኩ።

ዮሐንስ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም” በማለት በግልጽ ተናገረ።

“ታዲያ ማን ነህ? ኤልያስ ነህ?” ሲሉ ጠየቁት።

እሱም መልሶ “አይደለሁም” አለ።

“ነቢዩ ነህ?” አሉት፤ ይህን ሲሉ እንደሚመጣ ሙሴ የተናገረለትን ታላቅ ነቢይ መጥቀሳቸው ነው።—ዘዳግም 18:15, 18

“አይደለሁም!” ሲል ዮሐንስ መለሰ።

በዚህ ጊዜ “ለላኩን ሰዎች መልስ መስጠት እንድንችል ታዲያ አንተ ማን ነህ? ስለ ራስህስ ምን ትላለህ?” በማለት አጥብቀው ጠየቁት። ዮሐንስም “ነቢዩ ኢሳይያስ እንደተናገረው ‘የይሖዋን መንገድ አቅኑ’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኸው ሰው እኔ ነኝ” አላቸው።—ዮሐንስ 1:19-23

ሰዎቹ “ታዲያ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንክ ለምን ታጠምቃለህ?” ሲሉ ጠየቁት። ዮሐንስም የሚከተለውን ትልቅ ትርጉም ያለው መልስ ሰጣቸው፦ “እኔ በውኃ አጠምቃለሁ። እናንተ የማታውቁት ግን በመካከላችሁ ቆሟል፤ እሱም ከኋላዬ ይመጣል፤ እኔ የጫማውን ማሰሪያ እንኳ ለመፍታት አልበቃም።”—ዮሐንስ 1:25-27

ሕዝቡ፣ ንጉሥ የሚሆነውንና አስቀድሞ የተነገረለትን መሲሕ ለመቀበል የሚያስችል ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ እንዲኖራቸው በማድረግ መንገዱን እያዘጋጀ መሆኑን ዮሐንስ ገልጿል። ዮሐንስ ስለ መሲሑ ሲናገር “ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይበረታል፤ እኔ ጫማውን ለማውለቅ እንኳ ብቁ አይደለሁም” ብሏል። (ማቴዎስ 3:11) እንዲያውም “ከእኔ ኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለነበረ ከእኔ ይበልጣል” ሲል ተናግሯል።—ዮሐንስ 1:15

በእርግጥም ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ንስሐ ግቡ” ብሎ መናገሩ ተገቢ ነው። (ማቴዎስ 3:2) የዮሐንስ መልእክት፣ ይሖዋ የሾመው ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን ሊጀምር መሆኑን ለሕዝቡ የሚጠቁም ነው።