በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 108

ኢየሱስን ለማጥመድ የተጠነሰሰው ሴራ ከሸፈ

ኢየሱስን ለማጥመድ የተጠነሰሰው ሴራ ከሸፈ

ማቴዎስ 22:15-40 ማርቆስ 12:13-34 ሉቃስ 20:20-40

  • የቄሳር የሆነውን ለቄሳር

  • ትንሣኤ ያገኙ ሰዎች ያገባሉ?

  • ከሁሉ የሚበልጡት ትእዛዛት

የኢየሱስ ጠላቶች የሆኑት የሃይማኖት መሪዎች ተበሳጭተዋል። ኢየሱስ ክፋታቸውን የሚያጋልጡ ምሳሌዎች ተናግሮ መጨረሱ ነው። በዚህ ጊዜ ፈሪሳውያን እሱን ለማጥመድ ሴራ ጠነሰሱ። እሱን ለሮም አገረ ገዢ አሳልፈው ለመስጠት የሚያስችላቸው ነገር እንዲናገር ለማድረግ የሞከሩ ሲሆን ለደቀ መዝሙሮቻቸው ገንዘብ በመክፈል እሱን እንዲያጠምዱ ላኳቸው።—ሉቃስ 6:7

እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፦ “መምህር፣ አንተ ትክክለኛውን ነገር እንደምትናገርና እንደምታስተምር እንዲሁም እንደማታዳላ፣ ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን፦ ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባናል ወይስ አይገባንም?” (ሉቃስ 20:21, 22) ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች ግብዞችና ተንኮለኞች መሆናቸውን ስለሚያውቅ በሽንገላቸው አልተታለለም። ‘ግብር መክፈል ተገቢ አይደለም’ ብሎ ቢመልስ ‘በሮም መንግሥት ላይ ዓመፅ አነሳስተሃል’ ተብሎ ሊወነጀል ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ‘ግብር መክፈል ተገቢ ነው’ ቢል በሮም ቀንበር ሥር በመውደቃቸው የተማረሩት አይሁዳውያን በተሳሳተ መንገድ ሊረዱትና በእሱ ላይ ሊነሱ ይችላሉ። ታዲያ ኢየሱስ ምን ብሎ ይመልስ ይሆን?

“እናንተ ግብዞች፣ ለምን ትፈትኑኛላችሁ? እስቲ ለግብር የሚከፈለውን ሳንቲም አሳዩኝ” አላቸው። እነሱም አንድ ዲናር አመጡለት። ኢየሱስ “ይህ ምስልና የተቀረጸው ጽሑፍ የማን ነው?” አላቸው። እነሱም “የቄሳር” አሉ። በዚህ ጊዜ “እንግዲያው የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” በማለት ጥበብ የተንጸባረቀበት መመሪያ ሰጣቸው።—ማቴዎስ 22:18-21

ሰዎቹ ኢየሱስ በሰጠው መልስ ተደነቁ። ማስተዋል ለታከለበት  ንግግሩ ምላሽ መስጠት ስላልቻሉ ትተውት ሄዱ። ይሁንና ቀኑ ገና አላበቃም፤ ሰዎቹም እሱን ለማጥመድ መሞከራቸውን አላቆሙም። ፈሪሳውያን ያደረጉት ጥረት አልተሳካም፤ ከዚያም ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ወደ ኢየሱስ መጡ።

በትንሣኤ የማያምኑት ሰዱቃውያን፣ ከትንሣኤና ከዋርሳ ጋብቻ ጋር በተያያዘ ጥያቄ አነሱ፦ “መምህር፣ ሙሴ ‘አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ወንድሙ የሟቹን ሚስት ማግባትና ለወንድሙ ዘር መተካት አለበት’ ብሏል። በእኛ ዘንድ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ። የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ በመሞቱ ወንድሙ የሟቹን ሚስት አገባ። ሁለተኛውም ሆነ ሦስተኛው እስከ ሰባተኛው ድረስ ልጅ ሳይወልዱ ሞቱ። በመጨረሻም ሴትየዋ ሞተች። እንግዲህ ሁሉም ስላገቧት በትንሣኤ ከሰባቱ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?”—ማቴዎስ 22:24-28

ኢየሱስ፣ ሰዱቃውያን የሚያምኑባቸውን የሙሴን መጻሕፍት በመጥቀስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተ የምትሳሳቱት ቅዱሳን መጻሕፍትንም ሆነ የአምላክን ኃይል ባለማወቃችሁ አይደለም? ከሞት በሚነሱበት ጊዜ ወንዶችም አያገቡም ሴቶችም አይዳሩም፤ ከዚህ ይልቅ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ። ስለ ሙታን መነሳት ግን በሙሴ መጽሐፍ፣ ስለ ቁጥቋጦው በሚገልጸው ታሪክ ላይ አምላክ ሙሴን ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ እንዳለው አላነበባችሁም? እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም። እናንተ እጅግ ተሳስታችኋል።” (ማርቆስ 12:24-27፤ ዘፀአት 3:1-6) ሕዝቡ በኢየሱስ መልስ በጣም ተደነቁ።

ኢየሱስ ፈሪሳውያንንም ሆነ ሰዱቃውያንን ዝም አሰኝቷቸዋል፤ በመሆኑም ተቃዋሚዎቹ የሆኑት እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች እንደገና ሊፈትኑት ግንባር ፈጥረው ወደ እሱ መጡ። አንድ ጸሐፊ “መምህር፣ ከሕጉ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው።—ማቴዎስ 22:36

ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የመጀመሪያው ይህ ነው፦ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ይሖዋ አምላካችን አንድ ይሖዋ ነው፤ አንተም አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ።’ ሁለተኛው ደግሞ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚል ነው። ከእነዚህ የሚበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለም።”—ማርቆስ 12:29-31

ጸሐፊው የኢየሱስን መልስ ሲሰማ እንዲህ አለው፦ “መምህር፣ የተናገርከው እውነት ነው፤ ‘እሱ አንድ ነው፤ ከእሱ ሌላ አምላክ የለም’፤ እሱን በሙሉ ልብ፣ በሙሉ አእምሮና በሙሉ ኃይል መውደድ እንዲሁም ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ፣ ሙሉ በሙሉ ከሚቃጠል መባና ከመሥዋዕት ሁሉ እጅግ ይበልጣል።” ኢየሱስ፣ ጸሐፊው በማስተዋል እንደመለሰ ሲመለከት “አንተ ከአምላክ መንግሥት የራቅክ አይደለህም” አለው።—ማርቆስ 12:32-34

ኢየሱስ ለሦስት ቀናት (ኒሳን 9, 10 እና 11) በቤተ መቅደሱ ሲያስተምር ቆይቷል። እንደዚህ ጸሐፊ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ደስ እያላቸው አዳምጠውታል። የሃይማኖት መሪዎቹ ግን እንዲህ አልተሰማቸውም፤ እነሱ ‘ከዚህ በኋላ ሊጠይቁት አልደፈሩም።’