በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 71

ፈሪሳውያን ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው በጥያቄ አፋጠጡት

ፈሪሳውያን ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው በጥያቄ አፋጠጡት

ዮሐንስ 9:19-41

  • ፈሪሳውያን ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው በጥያቄ አፋጠጡት

  • የሃይማኖት መሪዎቹ “ዕውሮች” ናቸው

ፈሪሳውያኑ፣ ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው ኢየሱስ እንደፈወሰው ማመን ስላልቻሉ ወላጆቹን ጠሩ። ወላጆቹ ‘ከምኩራብ ሊባረሩ’ እንደሚችሉ አውቀዋል። (ዮሐንስ 9:22) ቤተሰቡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከሌሎች አይሁዳውያን ጋር መቆራረጡ ከማኅበራዊ ጉዳዮችም ሆነ ከኢኮኖሚ አንጻር ከባድ ችግር ያስከትላል።

ፈሪሳውያኑ ሁለት ጥያቄዎች አቀረቡላቸው፦ “ዓይነ ስውር ሆኖ ተወልዷል የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነው? ታዲያ አሁን እንዴት ሊያይ ቻለ?” ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ይህ ልጃችን እንደሆነና ዓይነ ስውር ሆኖ እንደተወለደ እናውቃለን። አሁን ግን እንዴት ሊያይ እንደቻለ የምናውቀው ነገር የለም፤ ዓይኖቹን ማን እንዳበራለትም አናውቅም።” ልጁ የተፈጸመውን ነገር ለወላጆቹ ነግሯቸው ሊሆን ቢችልም ወላጆቹ ዘዴኛ በመሆን “እሱን ጠይቁት፤ ሙሉ ሰው ነው። ስለ ራሱ መናገር ያለበት እሱ ነው” አሉ።—ዮሐንስ 9:19-21

ስለዚህ ፈሪሳውያኑ ሰውየውን እንደገና ጠሩትና ኢየሱስን ለመወንጀል የሚያበቃ ማስረጃ እንዳላቸው በመግለጽ ሊያስፈራሩት ሞከሩ። “እውነቱን በመናገር ለአምላክ ክብር ስጥ፤ እኛ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እናውቃለን” አሉት። ዓይነ ስውር የነበረው ሰው ግን “ኃጢአተኛ ይሁን አይሁን የማውቀው ነገር የለም” በማለት የሰነዘሩት ክስ እሱን እንደማይመለከተው ገለጸ። ከዚያም “እኔ የማውቀው ዓይነ ስውር እንደነበርኩና አሁን ግን ማየት እንደቻልኩ ነው” አለ።—ዮሐንስ 9:24, 25

ፈሪሳውያኑ ግን በዚህ ስላልረኩ “ምንድን ነው ያደረገልህ? ዓይንህን ያበራልህስ እንዴት ነው?” አሉት። ሰውየውም በድፍረት “ነገርኳችሁ እኮ፤ እናንተ ግን አትሰሙም። እንደገና መስማት የፈለጋችሁት ለምንድን ነው? እናንተም የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን ፈለጋችሁ እንዴ?” ሲል መለሰላቸው። ፈሪሳውያኑ በንዴት እንዲህ አሉት፦ “የዚያ ሰው ደቀ መዝሙር አንተ ነህ፤ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን። አምላክ ሙሴን እንዳነጋገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከየት እንደመጣ አናውቅም።”—ዮሐንስ 9:26-29

ሰውየውም በዚህ መደነቁን በሚገልጽ መንገድ “ከየት እንደመጣ አለማወቃችሁ በጣም የሚያስገርም ነገር ነው፤ ያም ሆነ ይህ ዓይኖቼን አብርቶልኛል” አላቸው። ከዚያም አምላክ የሚሰማቸውንና የሚቀበላቸውን ሰዎች በተመለከተ የሚከተለውን አሳማኝ ሐሳብ አቀረበ፦ “አምላክ ኃጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን፤ ፈሪሃ አምላክ ያለውንና ፈቃዱን የሚያደርገውን ሁሉ ግን ይሰማዋል። ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዓይኖች የከፈተ አለ ሲባል ከጥንት ዘመን ጀምሮ ተሰምቶ አይታወቅም።” በመጨረሻም “ይህ ሰው ከአምላክ ባይሆን ኖሮ ምንም ነገር ሊያደርግ አይችልም ነበር” ሲል ደመደመ።—ዮሐንስ 9:30-33

ፈሪሳውያኑ ሰውየውን መርታት ስላልቻሉ “አንተ ሁለመናህ በኃጢአት ተበክሎ የተወለድክ! እኛን ልታስተምር ትፈልጋለህ?” ብለው ሰደቡት። ከዚያም አባረሩት።—ዮሐንስ 9:34

ኢየሱስ የተፈጠረውን ነገር ሰማ፤ ሰውየውን ባገኘው ጊዜም “በሰው ልጅ ላይ እምነት አለህ?” ብሎ ጠየቀው። ዓይኑ የበራለት ሰውም “ጌታዬ፣ አምንበት ዘንድ እሱ ማን ነው?” ሲል መለሰ። ኢየሱስ “አይተኸዋል፤ ደግሞም እያነጋገረህ ያለው እሱ ነው” በማለት በግልጽ ነገረው።—ዮሐንስ 9:35-37

ሰውየውም “ጌታ ሆይ፣ በእሱ አምናለሁ” አለ። እንዲሁም ለኢየሱስ በመስገድ በእሱ ላይ እምነት እንዳለውና እንደሚያከብረው አሳየ። ኢየሱስም “የማያዩ ማየት እንዲችሉ፣ የሚያዩም እንዲታወሩ፣ ለዚህ ፍርድ ወደዚህ ዓለም መጥቻለሁ” በማለት ትልቅ ትርጉም ያለው ሐሳብ ተናገረ።—ዮሐንስ 9:38, 39

በዚያ ያሉት ፈሪሳውያን ዓይነ ስውር እንዳልሆኑ ያውቃሉ። ሆኖም መንፈሳዊ መሪ የመሆን ኃላፊነታቸውን እንዴት እየተወጡ ነው? ፈሪሳውያኑ “እናንተም ዕውሮች ናችሁ እያልከን ነው?” የሚል የመከላከያ ሐሳብ አቀረቡ። ኢየሱስም “ዕውሮች ብትሆኑማ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባችሁ ነበር። አሁን ግን ‘እናያለን’ ትላላችሁ። ስለዚህ ኃጢአታችሁ እንዳለ ይኖራል” አላቸው። (ዮሐንስ 9:40, 41) እነዚህ ሰዎች በእስራኤል አስተማሪዎች ባይሆኑ ኖሮ ኢየሱስ፣ መሲሕ መሆኑን አለመቀበላቸው የሚያስገርም አይሆንም ነበር። ይሁንና ሕጉን እያወቁ እሱን መቃወማቸው ከባድ ኃጢአት ነው።