በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 109

ተቃዋሚዎቹን አወገዘ

ተቃዋሚዎቹን አወገዘ

ማቴዎስ 22:41–23:24 ማርቆስ 12:35-40 ሉቃስ 20:41-47

  • ክርስቶስ የማን ልጅ ነው?

  • ኢየሱስ የተቃዋሚዎቹን ግብዝነት አጋለጠ

የኢየሱስ ተቃዋሚ የሆኑት የሃይማኖት መሪዎች፣ እሱን ተቀባይነት ለማሳጣትም ሆነ እሱን በማጥመድ ለሮማውያን አሳልፈው ለመስጠት ያደረጉት ጥረት አልተሳካም። (ሉቃስ 20:20) ዕለቱ ኒሳን 11 ሲሆን ኢየሱስ አሁንም ያለው በቤተ መቅደሱ ነው፤ በዚህ ጊዜ በተራው ጥያቄዎችን በማንሳት እውነተኛ ማንነቱን እንዲያውቁ አደረገ። ቅድሚያውን በመውሰድ “ስለ መሲሑ ምን ትላላችሁ? የማን ልጅ ነው?” ሲል ጠየቃቸው። (ማቴዎስ 22:42) መሲሑ ወይም ክርስቶስ ከዳዊት የዘር ሐረግ እንደሚመጣ በሰፊው ይታወቃል። እነሱም ይህን መልስ ሰጡ።—ማቴዎስ 9:27፤ 12:23፤ ዮሐንስ 7:42

በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦ “ታዲያ ዳዊት በመንፈስ ተመርቶ እንዴት ጌታ ብሎ ይጠራዋል? ምክንያቱም ዳዊት ‘ይሖዋ ጌታዬን፦ “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው’ ሲል ተናግሯል። ታዲያ ዳዊት ጌታ ብሎ ከጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል?”—ማቴዎስ 22:43-45

ፈሪሳውያን ምንም መልስ አልሰጡም፤ ምክንያቱም እነሱ የሚጠብቁት ከሮማውያን አገዛዝ ነፃ ሊያወጣቸው የሚችል የዳዊት ዘር የሆነ ሰው እንደሚመጣ ነው። ኢየሱስ ግን በመዝሙር 110:1, 2 ላይ ዳዊት የተናገረውን ሐሳብ በመጥቀስ መሲሑ ከሰብዓዊ ገዢ የበለጠ ሚና እንደሚኖረው ገለጸ። መሲሑ የዳዊት ጌታ ሲሆን በአምላክ ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ በሥልጣኑ መጠቀም ይጀምራል። ኢየሱስ የሰጠው መልስ ተቃዋሚዎቹን ጸጥ አሰኛቸው።

ደቀ መዛሙርቱና ሌሎች ብዙ ሰዎች ኢየሱስን እያዳመጡት ነው። አሁን ኢየሱስ ጸሐፍትንና ፈሪሳውያንን አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ ሰጠ። እነዚህ ሰዎች የአምላክን ሕግ ለማስተማር “በገዛ ሥልጣናቸው የሙሴን ቦታ ወስደዋል።” ኢየሱስ አድማጮቹን “የሚነግሯችሁን ነገር ሁሉ አድርጉ፤ ጠብቁትም፤ ሆኖም የሚናገሩትን በተግባር ስለማያውሉ እነሱ የሚያደርጉትን አታድርጉ” በማለት አስጠነቀቀ።—ማቴዎስ 23:2, 3

ቀጥሎም ኢየሱስ ግብዝነታቸውን የሚያሳይ ምሳሌ ሲጠቅስ “ትልቅ ክታብ ያስራሉ” አለ። አንዳንድ አይሁዳውያን የሕጉን የተወሰኑ ክፍሎች የያዘ ትንሽ ማኅደር በግንባራቸው ወይም በግራ ክንዳቸው ላይ ያስራሉ። ፈሪሳውያን ግን ለሕጉ የሚቀኑ መስለው ለመታየት ሲሉ ትልቅ ክታብ ያስራሉ። ከዚህም ሌላ ‘የልብሳቸውን ዘርፍ ያስረዝማሉ።’ እስራኤላውያን በልብሳቸው ጫፍ ላይ ዘርፍ እንዲያደርጉ ታዘዋል፤ ይሁንና ፈሪሳውያን የልብሳቸውን ዘርፍ በጣም ያስረዝሙታል። (ዘኁልቁ 15:38-40) ይህን ሁሉ የሚያደርጉት “በሰዎች ለመታየት ብለው ነው።”—ማቴዎስ 23:5

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም እንኳ ከፍ ያለ ቦታ የማግኘት ፍላጎት ሊያድርባቸው ይችላል፤ በመሆኑም የሚከተለውን ምክር ሰጣቸው፦ “መምህራችሁ አንድ ስለሆነ ረቢ ተብላችሁ አትጠሩ፤ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ። በተጨማሪም አባታችሁ አንድ እሱም በሰማይ ያለው ብቻ ስለሆነ በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ። እንዲሁም መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ ስለሆነ መሪ ተብላችሁ አትጠሩ።” ታዲያ ደቀ መዛሙርቱ ለራሳቸው ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? ምን ማድረግስ ይኖርባቸዋል? ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ከመካከላችሁ ታላቅ የሆነው የእናንተ አገልጋይ መሆን ይገባዋል። ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል።”—ማቴዎስ 23:8-12

ኢየሱስ በመቀጠል ግብዝ የሆኑትን ጸሐፍትና ፈሪሳውያን የሚያወግዝ ነገር በተከታታይ ተናገረ፦ “እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዳይገቡ በሩን ስለምትዘጉ ወዮላችሁ! እናንተ ራሳችሁ አትገቡም፤ ለመግባት የሚመጡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።”—ማቴዎስ 23:13

ፈሪሳውያን፣ ይሖዋ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ነገሮች አቅልለው ስለሚመለከቱ ኢየሱስ አወገዛቸው፤ ይህ አስተሳሰባቸው ለእነሱ እንደሚመቻቸው በሚያወጧቸው ደንቦች ላይ ተንጸባርቋል። ለምሳሌ ያህል “አንድ ሰው በቤተ መቅደሱ ቢምል ምንም አይደለም፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባለው ወርቅ ቢምል ግን መሐላውን የመጠበቅ ግዴታ አለበት” ይላሉ። እንዲህ ማለታቸው፣ ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንደማይችሉ ያሳያል፤ ምክንያቱም የይሖዋ የአምልኮ ቦታ ከሆነው ቤተ መቅደስ ይልቅ በቤተ  መቅደሱ ውስጥ ያለውን ወርቅ ከፍ አድርገው ተመልክተዋል። በመሆኑም “በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን እንደ ፍትሕ፣ ምሕረትና ታማኝነት ያሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች” ችላ ብለዋል።—ማቴዎስ 23:16, 23፤ ሉቃስ 11:42

ኢየሱስ እነዚህን ፈሪሳውያን “እናንተ ዕውር መሪዎች! ትንኝን አጥልላችሁ ታወጣላችሁ፤ ግመልን ግን ትውጣላችሁ!” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 23:24) ፈሪሳውያን ከሚጠጡት ወይን ውስጥ ትንኝን አጥልለው የሚያወጡት በሕጉ መሠረት ርኩስ ስለሆነች ነው። ሆኖም በሕጉ ውስጥ ያሉትን የበለጠ ክብደት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ችላ ማለታቸው ርኩስ የሆነውንና ከትንኝ እጅግ የሚበልጠውን ግመል ከመዋጥ የሚተናነስ አይደለም።—ዘሌዋውያን 11:4, 21-24