በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 123

እጅግ አዝኖ እያለ ያቀረበው ጸሎት

እጅግ አዝኖ እያለ ያቀረበው ጸሎት

ማቴዎስ 26:30, 36-46 ማርቆስ 14:26, 32-42 ሉቃስ 22:39-46 ዮሐንስ 18:1

  • ኢየሱስ በጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ

  • ላቡ እንደሚንጠባጠብ ደም ሆነ

ኢየሱስ ከታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ሆኖ ያቀረበውን ጸሎት ደመደመ። ከዚያም “የውዳሴ መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄዱ።” (ማርቆስ 14:26) በስተ ምሥራቅ ወደሚገኝ ጌትሴማኒ የተባለ የአትክልት ስፍራ አቀኑ፤ ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ወደዚህ ቦታ ይሄዳል።

በወይራ ዛፎች መካከል ወደሚገኘው ወደዚህ ውብ የአትክልት ስፍራ ሲደርሱ ኢየሱስ ከሐዋርያቱ መካከል ስምንቱ እዚያ እንዲቆዩ አደረገ። “ወደዚያ ሄጄ በምጸልይበት ጊዜ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” ስላለ የተዋቸው በአትክልት ስፍራው መግቢያ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። ከዚያም ሦስት ሐዋርያቱን ይኸውም ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ አትክልት ስፍራው ገባ። እዚያ እያሉ በጣም በመረበሹ ሦስቱን ሐዋርያት “እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝኛለሁ። እዚህ ሁኑና ከእኔ ጋር ነቅታችሁ ጠብቁ” አላቸው።—ማቴዎስ 26:36-38

ከዚያም ኢየሱስ ከእነሱ ትንሽ ራቅ በማለት “መሬት ላይ ተደፍቶ . . . ይጸልይ ጀመር።” በጣም በተጨነቀበት በዚህ ወቅት ወደ አምላክ የሚጸልየው ስለ ምን ጉዳይ ነው? “አባት ሆይ፣ አንተ ሁሉን ነገር ማድረግ ትችላለህ፤ ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ። ሆኖም እኔ የምፈልገው ሳይሆን አንተ የምትፈልገው ይሁን” አለ። (ማርቆስ 14:35, 36) ኢየሱስ ምን ማለቱ ነው? ቤዛ እንዲሆን የተሰጠውን ሚና መወጣት እንደማይችል መግለጹ ይሆን? በፍጹም!

ሮማውያን የሚገድሏቸውን ሰዎች ምን ያህል በጭካኔ እንደሚያሠቃዩአቸው ኢየሱስ ሰማይ እያለ ተመልክቷል። አሁን ሰው በመሆኑ የሚደርስበት አካላዊ ሥቃይ ይሰማዋል፤ ይህ ደግሞ ደስ እያለው የሚጠብቀው ነገር አይደለም። ከሁሉ በላይ በከፍተኛ ጭንቀት የተዋጠው ግን እንደተናቀ ወንጀለኛ ተቆጥሮ መገደሉ በአባቱ ስም ላይ ነቀፋ እንደሚያመጣ ስለተሰማው ነው። አምላክን ሰድበሃል በሚል ተከሶ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በእንጨት ላይ ይሰቀላል።

ኢየሱስ ረዘም ላለ ጊዜ ሲጸልይ ከቆየ በኋላ ሲመለስ ሦስቱ ሐዋርያት ተኝተው አገኛቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር አንድ ሰዓት እንኳ ነቅታችሁ መጠበቅ አልቻላችሁም? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሳታሰልሱም ጸልዩ።” ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱም ውጥረት ውስጥ እንዳሉ፣ ሌሊቱ ደግሞ እንደገፋ በመገንዘብ “እርግጥ፣ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው” አለ።—ማቴዎስ 26:40, 41

ከዚያም ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ ትቷቸው በመሄድ “ይህን ጽዋ” እንዲያስወግድለት አምላክን ጠየቀ። ተመልሶ ሲመጣ ግን ሦስቱ ሐዋርያት ወደ ፈተና እንዳይገቡ መጸለይ ሲገባቸው አሁንም ተኝተው አገኛቸው። ኢየሱስ ሲያናግራቸው “የሚሉት ነገር ጠፋቸው።” (ማርቆስ 14:40) ኢየሱስ ለሦስተኛ ጊዜ በመሄድ ተንበርክኮ ጸለየ።

ኢየሱስ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ የሚሞት መሆኑ በአባቱ ስም ላይ የሚያመጣው ነቀፋ በጣም አሳስቦታል። ይሖዋም የልጁን ጸሎት በመስማት መልአክ ልኮ አበረታታው። ያም ቢሆን ኢየሱስ ወደ አባቱ ምልጃ ማቅረቡን አላቆመም፤ እንዲያውም “ከበፊቱ ይበልጥ አጥብቆ መጸለዩን ቀጠለ።” ኢየሱስ በከፍተኛ ጭንቀት ተውጧል። በኢየሱስ ጫንቃ ላይ ታላቅ ኃላፊነት ወድቋል! የእሱም ሆነ እምነት ያላቸው የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ተስፋ የተመካው  በእሱ ላይ ነው። ከጭንቀቱ የተነሳ ላቡ “መሬት ላይ እንደሚንጠባጠብ ደም” ሆነ።—ሉቃስ 22:44

ኢየሱስ ወደ ሐዋርያቱ ለሦስተኛ ጊዜ ሲመለስ እንደገና ተኝተው አገኛቸው። በመሆኑም እንዲህ አላቸው፦ “ይህ የእንቅልፍና የእረፍት ሰዓት ነው? እነሆ፣ የሰው ልጅ ለኃጢአተኞች አልፎ የሚሰጥበት ሰዓት ደርሷል። ተነሱ፣ እንሂድ። እነሆ፣ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል።”—ማቴዎስ 26:45, 46