በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 112

ንቁ ስለ መሆን የተሰጠ ትምህርት—ደናግሉ

ንቁ ስለ መሆን የተሰጠ ትምህርት—ደናግሉ

ማቴዎስ 25:1-13

  • ኢየሱስ የአሥሩን ደናግል ምሳሌ ተናገረ

ኢየሱስ፣ ከመገኘቱና ከሥርዓቱ መደምደሚያ ምልክት ጋር በተያያዘ ሐዋርያቱ ላቀረቡለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ቆይቷል። አሁንም ተጨማሪ ምሳሌ በመጠቀም ጥበብ ያዘለ ምክር ሰጣቸው። የምልክቱን ፍጻሜ ኢየሱስ በሥልጣኑ በሚገኝበት ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ ሰዎች ይመለከቱታል።

ኢየሱስ ምሳሌውን ሲጀምር እንዲህ አለ፦ “መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ ከወጡ አሥር ደናግል ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አምስቱ ሞኞች፣ አምስቱ ደግሞ ልባሞች ነበሩ።”—ማቴዎስ 25:1, 2

ኢየሱስ፣ መንግሥተ ሰማያትን ከሚወርሱት ደቀ መዛሙርቱ ግማሾቹ ሞኞች ግማሾቹ ደግሞ ልባሞች እንደሆኑ እየተናገረ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከመንግሥተ ሰማያት ጋር በተያያዘ እያንዳንዱ ደቀ መዝሙር ንቁ መሆኑ አሊያም ትኩረቱ መከፋፈሉ በራሱ ምርጫ ላይ የተመካ መሆኑን እየገለጸ ነው። ሆኖም ኢየሱስ፣ እያንዳንዱ የእሱ አገልጋይ ታማኝነቱን መጠበቅና የአባቱን በረከት ማግኘት እንደሚችል እርግጠኛ ነው።

በምሳሌው ላይ አሥሩም ደናግል ሙሽራውን ለመቀበልና ሠርጉን ለማጀብ ወጥተዋል። ሙሽራው ሲደርስ ደናግሉ መብራታቸውን አብርተው አካባቢውን ያደምቃሉ፤ ሙሽራው ሙሽራይቱን ወደተዘጋጀላት ቤት ሲያመጣት መብራታቸውን ማብራታቸው ለእሱ ያላቸውን አክብሮት ያሳያል። ታዲያ በምሳሌው ላይ የተገለጹት ደናግል ምን አጋጠማቸው?

ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሞኞቹ መብራታቸውን ቢይዙም መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር፤ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በዕቃ ዘይት ይዘው ነበር። ሙሽራው በዘገየ ጊዜ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ።” (ማቴዎስ  25:3-5) ሙሽራው እንደተጠበቀው ቶሎ አልመጣም። ረዘም ላለ ጊዜ የቆየ ይመስላል፤ በዚህ ጊዜ ደናግሉ እንቅልፍ ጣላቸው። ሐዋርያቱ፣ ኢየሱስ ወደ ሩቅ አገር ስለሄደና “ከጊዜ በኋላ ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተረክቦ” ስለመጣ አንድ መስፍን የነገራቸውን ምሳሌ ያስታውሱ ይሆናል።—ሉቃስ 19:11-15

ኢየሱስ ስለ አሥሩ ደናግል በተናገረው ምሳሌ ላይ ሙሽራው በመጣበት ወቅት ምን እንደተከናወነ ሲገልጽ እንዲህ አለ፦ “እኩለ ሌሊት ላይ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጫጫታ ተሰማ።” (ማቴዎስ 25:6) ለመሆኑ ደናግሉ ዝግጁና ንቁ ሆነው ጠብቀውታል?

ኢየሱስ ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ “በዚህ ጊዜ ደናግሉ ሁሉ ተነስተው መብራቶቻቸውን አዘጋጁ። ሞኞቹ ደናግል ልባሞቹን ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለሆነ ከያዛችሁት ዘይት ላይ ስጡን’ አሏቸው። ልባሞቹም ‘ለእናንተ ከሰጠናችሁ ለእኛም ለእናንተም ላይበቃን ስለሚችል ወደ ሻጮች ሄዳችሁ ለራሳችሁ የተወሰነ ዘይት ብትገዙ ይሻላል’ ብለው መለሱላቸው።”—ማቴዎስ 25:7-9

ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው አምስቱ ሞኝ ደናግል የሙሽራውን መምጣት ንቁና ዝግጁ ሆነው አልጠበቁም። ለመብራታቸው በቂ ዘይት ስላልያዙ ሄደው መግዛት አለባቸው። ኢየሱስ የተፈጸመውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገለጸ፦ “ሊገዙ ሄደው ሳሉም ሙሽራው ደረሰ። ተዘጋጅተው የነበሩት ደናግልም ወደ ሠርጉ ድግስ ገቡ፤ በሩም ተዘጋ። በኋላም የቀሩት ደናግል መጥተው ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ ክፈትልን!’ አሉ። እሱ ግን ‘እውነቴን ነው የምላችሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው።” (ማቴዎስ 25:10-12) ዝግጁና ንቁ ሆኖ አለመጠበቅ ያስከተለው መዘዝ ምንኛ አሳዛኝ ነው!

ሐዋርያቱ በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሙሽራ ኢየሱስን እንደሚያመለክት መረዳት ይችላሉ። ከዚህ ቀደም ኢየሱስ ራሱን ከሙሽራ ጋር አመሳስሏል። (ሉቃስ 5:34, 35) ልባሞቹ ደናግልስ ማንን ያመለክታሉ? ኢየሱስ፣ መንግሥት ስለሚወርሰው “ትንሽ መንጋ” ሲናገር “ወገባችሁን ታጠቁ፤ መብራታችሁንም አብሩ” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 12:32, 35) በመሆኑም ስለ ደናግሉ በሚገልጸው በዚህ ምሳሌ ላይ ኢየሱስ እንደ እነሱ ስላሉ ታማኝ ደቀ መዛሙርት እየተናገረ እንደሆነ ሐዋርያቱ መገንዘብ ይችላሉ። ታዲያ ኢየሱስ በዚህ ምሳሌ ተጠቅሞ ማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ምንድን ነው?

ነጥቡን ምንም በማያሻማ መንገድ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል። “እንግዲህ ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን ስለማታውቁ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት ምሳሌውን ደመደመ።—ማቴዎስ 25:13

ኢየሱስ ከእሱ መገኘት ጋር በተያያዘ ታማኝ ተከታዮቹ ‘ዘወትር ነቅተው መጠበቅ’ እንደሚያስፈልጋቸው እያሳሰበ እንደሆነ ግልጽ ነው። ኢየሱስ መምጣቱ አይቀርም፤ በመሆኑም ተከታዮቹ ውድ ለሆነው ተስፋቸው ትኩረት ሳይሰጡ ቀርተው ሽልማታቸውን እንዳያጡ እንደ አምስቱ ልባም ደናግል ዝግጁና ንቁ ሆነው መጠበቅ ያስፈልጋቸዋል።