በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 88

የሀብታሙ ሰውና የአልዓዛር ሁኔታ ተለወጠ

የሀብታሙ ሰውና የአልዓዛር ሁኔታ ተለወጠ

ሉቃስ 16:14-31

  • የሀብታሙ ሰውና የአልዓዛር ምሳሌ

ኢየሱስ ቁሳዊ ሀብትን እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ለደቀ መዛሙርቱ ጥሩ ምክር ሰጥቷቸዋል። እያዳመጡት ያሉት ግን ደቀ መዛሙርቱ ብቻ አይደሉም። ፈሪሳውያንም በቦታው የተገኙ ሲሆን እነሱም የኢየሱስን ምክር ልብ ሊሉት ይገባል። ለምን? “ገንዘብ ወዳድ” ስለሆኑ ነው። ኢየሱስ የተናገረውን ሲሰሙም “ያፌዙበት ጀመር።”—ሉቃስ 15:2፤ 16:13, 14

ኢየሱስ ግን በዚህ አልተደናገጠም። እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ በሰዎች ፊት ጻድቅ መስላችሁ ትቀርባላችሁ፤ አምላክ ግን ልባችሁን ያውቃል። በሰዎች ፊት ከፍ ተደርጎ የሚታየው ነገር በአምላክ ፊት አስጸያፊ ነውና።”—ሉቃስ 16:15

ፈሪሳውያን ‘በሰዎች ፊት ከፍ ተደርገው’ ሲታዩ ቆይተዋል፤ አሁን ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሊሆን ወይም ሁኔታዎች ሊለዋወጡ ነው። ከፍ ተደርገው የሚታዩ ሰዎች ይኸውም በዓለማዊ ሀብት የበለጸጉና ከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ያላቸው ግለሰቦች እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች ከቦታቸው ሊወርዱ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ተራ ሰዎች ከፍ ሊደረጉ ነው። ኢየሱስ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚመጣ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦

“ሕጉም ሆነ የነቢያት ቃል እስከ ዮሐንስ ድረስ ሲነገሩ ቆይተዋል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የአምላክ መንግሥት ምሥራች እየታወጀ ነው፤ የተለያዩ ዓይነት ሰዎችም ወደዚያ ለመግባት ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ከሕጉ የአንዷ ፊደል ጭረት ሳትፈጸም ከምትቀር ሰማይና ምድር ቢያልፉ ይቀላል።” (ሉቃስ 3:18፤ 16:16, 17) ታዲያ ኢየሱስ የተናገረው ነገር ለውጥ እየተካሄደ እንዳለ የሚያመለክተው እንዴት ነው?

የሃይማኖት መሪዎቹ የሙሴን ሕግ በጥብቅ እንደሚከተሉ በኩራት ይናገራሉ። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም አንድን ዓይነ ስውር በፈወሰበት ወቅት “እኛ . . . የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን። አምላክ ሙሴን እንዳነጋገረው እናውቃለን” በማለት በኩራት እንደተናገሩ ታስታውስ ይሆናል። (ዮሐንስ 9:13, 28, 29) በሙሴ በኩል የተሰጠው ሕግ አንዱ ዓላማ፣ ትሑት የሆኑ ሰዎችን ወደ መሲሑ ይኸውም ወደ ኢየሱስ መምራት ነው። መጥምቁ ዮሐንስ፣ ኢየሱስ የአምላክ በግ መሆኑን ተናግሯል። (ዮሐንስ 1:29-34) በመሆኑም ትሑት የሆኑ በተለይ ደግሞ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው አይሁዳውያን፣ ዮሐንስ መስበክ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ስለ “አምላክ መንግሥት” ሲሰሙ ቆይተዋል። በእርግጥም የሚሰበከው ነገር፣ የአምላክ መንግሥት ዜጎች ለመሆንና ከዚህ መንግሥት ለመጠቀም ለሚፈልጉ ሁሉ “ምሥራች” ነው።

የሙሴ ሕግ ሳይፈጸም አልቀረም፤ እንዲያውም ሕዝቡን ወደ መሲሑ መርቷል። ሆኖም ሕጉን መጠበቅ ግዴታ መሆኑ ሊቀር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ሕጉ በተለያዩ ምክንያቶች ፍቺን ይፈቅዳል፤ አሁን ግን ኢየሱስ “ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፤ ባሏ የፈታትንም ሴት የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል” በማለት ተናገረ። (ሉቃስ 16:18) ይህ ሐሳብ፣ ለሁሉ ነገር ሕግ ማውጣት የሚወዱትን ፈሪሳውያን ምንኛ አበሳጭቷቸው ይሆን!

ቀጥሎም ኢየሱስ፣ ምን ያህል ከፍተኛ ለውጥ እየተካሄደ እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ተናገረ። ምሳሌው ስለ ሁለት ሰዎች የሚያወሳ ሲሆን ሁለቱም ያሉበት ሁኔታ በአስገራሚ መንገድ ይለወጣል። ይህን ምሳሌ ስታነብ፣ ኢየሱስን  ከሚያዳምጡት መካከል “ገንዘብ ወዳድ” የሆኑትና በሰዎች ዘንድ ከፍ ተደርገው የሚታዩት ፈሪሳውያን እንደሚገኙበት አስታውስ።

ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሀብታም ሰው ነበር፤ ይህ ሰው ሐምራዊ ልብስና በፍታ ይለብስ የነበረ ከመሆኑም በላይ ዕለት ተዕለት በደስታና በቅንጦት ይኖር ነበር። ይሁን እንጂ እዚህ ሰው ደጃፍ ላይ እያመጡ የሚያስቀምጡት መላ ሰውነቱን ቁስል የወረሰው አልዓዛር የሚባል አንድ ለማኝ ነበር፤ እሱም ከሀብታሙ ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ በልቶ ለመጥገብ ይመኝ ነበር። ውሾችም ሳይቀር እየመጡ ቁስሉን ይልሱ ነበር።”—ሉቃስ 16:19-21

ፈሪሳውያን ገንዘብ ወዳዶች ናቸው፤ በመሆኑም በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተገለጸው “ሀብታም ሰው” ማንን እንደሚያመለክት ምንም አያሻማም። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች በጣም ውድ የሆነና የተንቆጠቆጠ ልብስ መልበስም ይወዳሉ። በቁሳዊ ረገድ ሀብታሞች ከመሆናቸውም ሌላ በመንፈሳዊ ሁኔታ የተለያዩ መብቶችና አጋጣሚዎች ስላሏቸው ሀብታም መስለው ይታያሉ። በምሳሌው ላይ ያለው ሰው፣ ሀብታም የሆኑ ሰዎች የሚለብሱት ዓይነት ሐምራዊ ልብስ እንደለበሰ መገለጹ የሃይማኖት መሪዎቹ ከፍተኛ ሥልጣን እንዳላቸው የሚያመለክት ሲሆን ነጩ በፍታ ደግሞ ተመጻዳቂ መሆናቸውን ይጠቁማል።—ዳንኤል 5:7

ሀብታምና ኩሩ የሆኑት መሪዎች፣ ድሃ ለሆነው ተራ ሕዝብ ምን አመለካከት አላቸው? እነዚህን ሰዎች በንቀት አምሃአሬትስ ይኸውም የአገሬው (የመሬት) ሰዎች በማለት የሚጠሯቸው ሲሆን ሕጉን እንደማያውቁና ለመማርም  ብቁ እንዳልሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። (ዮሐንስ 7:49) የእነዚህ ሰዎች ሁኔታ ‘አልዓዛር የተባለው ለማኝ’ ካለበት ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል፤ አልዓዛር “ከሀብታሙ ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ” እንኳ ለመብላት ይመኛል። መላ ሰውነቱን ቁስል እንደወረሰው እንደ አልዓዛር ሁሉ ተራው ሕዝብም በመንፈሳዊ ሁኔታ ሕመም ያለበት ያህል ዝቅ ተደርጎ ይታያል።

ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ለተወሰነ ጊዜ ቆይቷል፤ ይሁንና ኢየሱስ በሀብታሙ ሰውም ሆነ በአልዓዛር የተመሰሉት ሰዎች ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የሚለወጥበት ጊዜ እንደደረሰ ያውቃል።

የሀብታሙ ሰውና የአልዓዛር ሁኔታ መለወጥ

ኢየሱስ ሰዎቹ የነበሩበት ሁኔታ በሚያስገርም አኳኋን እንደተለዋወጠ በመግለጽ ታሪኩን ቀጠለ፦ “ከጊዜ በኋላ ለማኙ ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት። ሀብታሙም ሰው ሞተና ተቀበረ። በመቃብርም ሆኖ እየተሠቃየ ሳለ አሻቅቦ ሲመለከት ከሩቅ አብርሃምንና በእቅፉ ያለውን አልዓዛርን አየ።”—ሉቃስ 16:22, 23

የኢየሱስ አድማጮች አብርሃም ከሞተ ረጅም ጊዜ እንደሆነውና መቃብር ውስጥ እንዳለ ያውቃሉ። ቅዱሳን መጻሕፍት አብርሃምን ጨምሮ በመቃብር ወይም በሲኦል ያለ ማንኛውም ሰው ማየትም ሆነ መናገር እንደማይችል በግልጽ ያስተምራሉ። (መክብብ 9:5, 10) ታዲያ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች የኢየሱስን ምሳሌ እንዴት ይረዱት ይሆን? ኢየሱስ ስለ ተራው ሕዝብና ገንዘብ ወዳድ ስለሆኑት የሃይማኖት መሪዎች ምን መግለጽ ፈልጎ ይሆን?

ኢየሱስ ‘ሕጉም ሆነ የነቢያት ቃል እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ ሲነገሩ እንደቆዩና ከዚያን ጊዜ አንስቶ የአምላክ መንግሥት ምሥራች እየታወጀ እንደሆነ’ በመናገር ሁኔታዎች እንደተለወጡ ጠቁሟል። ስለዚህ አልዓዛርም ሆነ ሀብታሙ ሰው ቀድሞ ለነበሩበት ሁኔታ የሞቱት፣ በዮሐንስና በኢየሱስ ክርስቶስ ስብከት የተነሳ ነው፤ በአምላክ ዘንድ ያላቸው ቦታ ከዚህ በኋላ ይለወጣል።

በተለይ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ወይም ድሃ የሆኑት ሰዎች በመንፈሳዊ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ተርበው ቆይተዋል። ይሁንና መጀመሪያ መጥምቁ ዮሐንስ ከዚያም ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት የሰበኩት መልእክት ጠቅሟቸዋል፤ ደግሞም ይህን መልእክት ተቀብለዋል። ቀደም ሲል ከሃይማኖት መሪዎቹ ‘ማዕድ ከሚወድቅ ፍርፋሪ’ ጋር ከሚመሳሰል መንፈሳዊ ምግብ ያለፈ ነገር አያገኙም ነበር። አሁን ግን ጠቃሚ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን በተለይም ኢየሱስ የሚያስተምራቸውን አስደናቂ ነገሮች እያገኙ ነው። በመጨረሻ በይሖዋ አምላክ ዘንድ ሞገስ አገኙ።

በአንጻሩ ግን ሀብታም የሆኑትና ተሰሚነት ያላቸው የሃይማኖት መሪዎች፣ ዮሐንስ የሰበከውንና ኢየሱስ በመላው አገር ሲያውጅ የቆየውን የመንግሥቱን መልእክት ለመቀበል አሻፈረን ብለዋል። (ማቴዎስ 3:1, 2፤ 4:17) እንዲያውም ወደፊት ከአምላክ ዘንድ ስለሚመጣው በእሳት የተመሰለ ፍርድ የሚገልጸው የኢየሱስና የዮሐንስ መልእክት እያሠቃያቸው ወይም እያስቆጣቸው ነው። (ማቴዎስ 3:7-12) ገንዘብ ወዳድ የሆኑት የሃይማኖት መሪዎች፣ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የአምላክን መልእክት ማወጃቸውን  ጋብ ቢያደርጉ ከሥቃያቸው ትንሽ አረፍ ይላሉ። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች በምሳሌው ላይ እንደተገለጸውና የሚከተለውን እንደተናገረው ሀብታም ሰው ናቸው፦ “አብርሃም አባት ሆይ፣ በዚህ የሚንቀለቀል እሳት እየተሠቃየሁ ስለሆነ እባክህ ራራልኝና አልዓዛር የጣቱን ጫፍ ውኃ ውስጥ ነክሮ ምላሴን እንዲያቀዘቅዝልኝ ላከው።”—ሉቃስ 16:24

ይሁንና የጠየቀው ነገር አልተፈጸመም። አብዛኞቹ የሃይማኖት መሪዎች አመለካከታቸውን አያስተካክሉም። “ሙሴንና ነቢያትን” አልሰሙም፤ ይኸውም አምላክ የመረጠው መሲሕና ንጉሥ፣ ኢየሱስ መሆኑን የሚጠቁመውን የቅዱሳን መጻሕፍት ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም። (ሉቃስ 16:29, 31፤ ገላትያ 3:24) በተጨማሪም ኢየሱስን የተቀበሉትና አሁን መለኮታዊ ሞገስ ያገኙት ድሆች የሚያስተምሩትን ነገር የሃይማኖት መሪዎቹ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ መስማት አልፈለጉም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ደግሞ እነዚህን የሃይማኖት መሪዎች ለማስደሰት ወይም ከሥቃያቸው ለማሳረፍ ሲሉ እውነቱን አለሳልሰው ለማቅረብ አይሞክሩም። በምሳሌው ላይ “አብርሃም” ለሀብታሙ ሰው እንደተናገረ የተገለጸው ሐሳብ ይህን እውነታ ያሳያል፦

“ልጄ ሆይ፣ አንተ በሕይወት ዘመንህ መልካም ነገሮችን ሁሉ እንደተቀበልክ፣ አልዓዛር ግን መጥፎ ነገሮች እንደደረሱበት አስታውስ። አሁን ግን እሱ እዚህ ሲጽናና አንተ ትሠቃያለህ። ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ ከእኛ ወደ እናንተ መሻገር የሚፈልጉ መሻገር እንዳይችሉ እንዲሁም ሰዎች ከእናንተ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ትልቅ ገደል ተደርጓል።”—ሉቃስ 16:25, 26

እንዲህ ያለ አስገራሚ ለውጥ መከሰቱ ምንኛ ፍትሐዊና ተገቢ ነው! ይህ ለውጥ፣ ኩራተኛ የሆኑት የሃይማኖት መሪዎችና የኢየሱስን ቀንበር የተሸከሙት ትሑት ሰዎች ሁኔታ መቀያየሩን የሚያሳይ ነው፤ እነዚህ ትሑት ሰዎች በስተ መጨረሻ እረፍትና መንፈሳዊ ምግብ ማግኘት ችለዋል። (ማቴዎስ 11:28-30) ከጥቂት ወራት በኋላ፣ የሕጉ ቃል ኪዳን በአዲሱ ቃል ኪዳን ሲተካ ደግሞ ለውጡ ይበልጥ ግልጽ ይሆናል። (ኤርምያስ 31:31-33፤ ቆላስይስ 2:14፤ ዕብራውያን 8:7-13) በ33 ዓ.ም. የጴንጤቆስጤ ዕለት አምላክ ቅዱስ መንፈሱን ሲያፈስ፣ በአምላክ ፊት ሞገስ ያገኙት ፈሪሳውያንና አጋሮቻቸው የሆኑት ሌሎቹ የሃይማኖት መሪዎች ሳይሆኑ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መሆናቸው በማያሻማ መንገድ ግልጽ ይሆናል።