በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 2

ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት ክብር ተሰጥቶታል

ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት ክብር ተሰጥቶታል

ሉቃስ 1:34-56

  • ማርያም ዘመዷን ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ ሄደች

መልአኩ ገብርኤል፣ ኢየሱስ የሚባልና የዘላለም ንጉሥ የሚሆን ልጅ እንደምትወልድ ለወጣቷ ለማርያም ሲነግራት ማርያም “እኔ ከወንድ ጋር ግንኙነት ፈጽሜ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” በማለት ጠየቀችው።—ሉቃስ 1:34

ገብርኤልም እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑሉም ኃይል በአንቺ ላይ ያርፋል። ስለሆነም የሚወለደው ልጅ ቅዱስና የአምላክ ልጅ ይባላል።”—ሉቃስ 1:35

ማርያም መልእክቱን እንድታምን ብሎ ሳይሆን አይቀርም ገብርኤል አክሎ እንዲህ አላት፦ “እነሆ፣ ዘመድሽ ኤልሳቤጥም በስተርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መሃን ትባል የነበረ ቢሆንም ይኸው ስድስተኛ ወሯን ይዛለች፤ አምላክ የተናገረው ቃል ሳይፈጸም አይቀርምና።”—ሉቃስ 1:36, 37

ማርያም የገብርኤልን ቃል አምና ተቀበለች፤ የሰጠችውም ምላሽ ይህን ያሳያል። ማርያም “እነሆ፣ እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ! እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች።—ሉቃስ 1:38

ገብርኤል ከሄደ በኋላ ማርያም፣ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ በይሁዳ ኮረብቶች ከባሏ ከዘካርያስ ጋር ወደምትኖረው ወደ ኤልሳቤጥ ለመሄድ ተነሳች። ማርያም ከምትኖርበት ከናዝሬት ተነስቶ እዚያ ለመድረስ ሦስት ወይም አራት ቀን ሊወስድ ይችላል።

በመጨረሻ ማርያም ዘካርያስ ቤት ደረሰች። ወደ ቤት ስትገባም ለዘመዷ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበች። በዚህ ጊዜ ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ ማርያምን እንዲህ አለቻት፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማህፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው! የጌታዬ እናት ወደ እኔ መምጣቷ ለእኔ እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው! እነሆ፣ የሰላምታሽን ድምፅ እንደሰማሁ በማህፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሏልና።”—ሉቃስ 1:42-44

ማርያም ይህን ስትሰማ ከልብ በመነጨ የምስጋና ስሜት እንዲህ አለች፦ “ነፍሴ ይሖዋን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም አዳኜ በሆነው አምላክ እጅግ ደስ ይሰኛል፤ ምክንያቱም የባሪያውን መዋረድ ተመልክቷል። እነሆ፣ ከአሁን ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ደስተኛ ይሉኛል፤ ምክንያቱም ኃያል የሆነው አምላክ ታላላቅ ነገሮች አድርጎልኛል።” ማርያም በአምላክ ፊት ሞገስ ብታገኝም መከበር የሚገባው ይሖዋ መሆኑን እንደገለጸች ልብ በል። “ስሙም ቅዱስ ነው፤ ምሕረቱም በሚፈሩት ሁሉ ላይ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል” ብላለች።—ሉቃስ 1:46-50

ማርያም በመንፈስ መሪነት የሚከተለውን ትንቢት በመናገር አምላክን ማወደሷን ቀጠለች፦ “በክንዱም ታላላቅ ሥራዎች አከናውኗል፤ በልባቸው ሐሳብ ትዕቢተኛ የሆኑትንም በትኗቸዋል። ኃያላን ሰዎችን ከዙፋናቸው አውርዷል፤ ዝቅ ያሉትንም ከፍ አድርጓል፤ የተራቡትን በመልካም ነገሮች አጥግቧል፤ ሀብታሞችንም ባዶ እጃቸውን ሰዷቸዋል። ምሕረቱን በማስታወስ አገልጋዩን እስራኤልን ረድቷል፤ ይህን ያደረገው ለአባቶቻችን በገባው ቃል መሠረት ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረት ለማሳየት ነው።”—ሉቃስ 1:51-55

ማርያም ለሦስት ወር ያህል ከኤልሳቤጥ ጋር ቆየች፤ የኤልሳቤጥ የመውለጃ ጊዜ በተቃረበባቸው በእነዚህ የመጨረሻ ሳምንታት ማርያም ብዙ ሳታግዛት አልቀረችም። በአምላክ እርዳታ የፀነሱት እነዚህ ሁለት ታማኝ ሴቶች በዚህ ወቅት አንድ ላይ መሆናቸው እንዴት መልካም ነው!

ኢየሱስ ከመወለዱ በፊትም እንኳ ክብር እንደተሰጠው ልብ በል። ኤልሳቤጥ “ጌታዬ” ብላ ጠርታዋለች፤ በተጨማሪም ማርያም ስትመጣ በኤልሳቤጥ ማህፀን ውስጥ ያለው ፅንስ “በደስታ ዘሏል።” ወደፊት በዚህ መጽሐፍ ላይ እንደምንመለከተው ሌሎች ሰዎች ግን ለማርያምም ሆነ ለልጇ አክብሮት አላሳዩም።