በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 68

“የዓለም ብርሃን”—የአምላክ ልጅ

“የዓለም ብርሃን”—የአምላክ ልጅ

ዮሐንስ 8:12-36

  • ኢየሱስ የወልድን ማንነት አስረዳ

  • አይሁዳውያን ባሪያ የሆኑት እንዴት ነው?

በዳስ በዓል የመጨረሻ ቀን ማለትም በሰባተኛው ቀን ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ‘ግምጃ ቤት’ ተብሎ በሚጠራው ቦታ እያስተማረ ነው። (ዮሐንስ 8:20፤ ሉቃስ 21:1) ይህ ቦታ የሚገኘው ሰዎች መዋጮ በሚያደርጉበት በሴቶች አደባባይ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም።

በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚገኘው ይህ አካባቢ በዓሉ በሚከበርበት ወቅት ማታ ላይ ደማቅ ብርሃን ይኖረዋል። እያንዳንዳቸው በዘይት የተሞሉ አራት ትላልቅ ጎድጓዳ ሳህኖች ያሏቸው አራት ግዙፍ መቅረዞች በዚህ ስፍራ ቆመዋል። ከእነዚህ መቅረዞች የሚወጣው ብርሃን አካባቢው በሙሉ ፍንትው ብሎ እንዲታይ ያደርጋል። ኢየሱስ ቀጥሎ የተናገረው ነገር አድማጮቹ ይህን ብርሃን እንዲያስታውሱ ያደርጋቸው ይሆናል። “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ። እኔን የሚከተል ሁሉ በምንም ዓይነት በጨለማ አይሄድም፤ ከዚህ ይልቅ የሕይወት ብርሃን ያገኛል” አላቸው።—ዮሐንስ 8:12

ፈሪሳውያን ኢየሱስን በመቃወም “አንተ ስለ ራስህ ትመሠክራለህ፤ ምሥክርነትህም እውነት አይደለም” አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ስለ ራሴ ብመሠክር እንኳ ከየት እንደመጣሁና ወዴት እንደምሄድ ስለማውቅ ምሥክርነቴ እውነት ነው። እናንተ ግን ከየት እንደመጣሁና ወዴት እንደምሄድ አታውቁም።” አክሎም እንዲህ በማለት ተናገረ፦ “በሕጋችሁም ላይ ‘የሁለት ሰዎች ምሥክርነት እውነት ነው’ ተብሎ ተጽፏል። ስለ ራሴ የምመሠክር አንዱ እኔ ነኝ፤ ደግሞም የላከኝ አብ ስለ እኔ ይመሠክራል።”—ዮሐንስ 8:13-18

ፈሪሳውያን ያቀረበውን ሐሳብ ከመቀበል ይልቅ “አባትህ የት ነው?” አሉት። ኢየሱስም “እናንተ እኔንም ሆነ አባቴን አታውቁም። እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር” የሚል ቀጥተኛ መልስ ሰጣቸው። (ዮሐንስ 8:19) ፈሪሳውያን አሁንም ኢየሱስን መያዝ ቢፈልጉም አንድም ሰው አልያዘውም።

ኢየሱስ ከዚህ ቀደም የተናገረውን በመድገም እንዲህ አለ፦ “እኔ እሄዳለሁ፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ይሁንና ኃጢአተኛ እንደሆናችሁ ትሞታላችሁ። እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም።” አይሁዳውያኑ፣ ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ጨርሶ ስላልገባቸው “‘እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ  አትችሉም’ የሚለው ራሱን ሊገድል አስቦ ይሆን እንዴ?” አሉ። ኢየሱስ ከየት እንደመጣ ስለማያውቁ ምን ማለቱ እንደሆነ ሊረዱ አልቻሉም። እሱም “እናንተ ከምድር ናችሁ፤ እኔ ከላይ ነኝ። እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፤ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም” በማለት አስረዳቸው።—ዮሐንስ 8:21-23

ኢየሱስ ይህን ያለው፣ ሰው ከመሆኑ በፊት በሰማይ ስለነበረው ሕይወት እንዲሁም ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ ወይም ክርስቶስ መሆኑን ለመግለጽ ነው፤ የሃይማኖት መሪዎቹ መሲሑን ሊያውቁት ይገባል። እነሱ ግን በንቀት “ለመሆኑ አንተ ማን ነህ?” ብለው ጠየቁት።—ዮሐንስ 8:25

የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስን አልተቀበሉትም፤ እንዲያውም እየተቃወሙት ነው፤ በመሆኑም “ድሮውንም እኔ ከእናንተ ጋር የምነጋገረው እንዲያው በከንቱ ነው” አላቸው። ያም ቢሆን ለአባቱ ትኩረት የሰጠ ሲሆን አይሁዳውያን ወልድን ሊሰሙት የሚገባው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ “የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔም ከእሱ የሰማሁትን ያንኑ ነገር ለዓለም እየተናገርኩ ነው” አለ።—ዮሐንስ 8:25, 26

ከዚያም ኢየሱስ ከእነዚህ አይሁዳውያን በተቃራኒ እሱ በአባቱ እንደሚተማመን ሲገልጽ እንዲህ አለ፦ “የሰውን ልጅ ከሰቀላችሁት በኋላ እኔ እሱ እንደሆንኩና በራሴ ተነሳስቼ አንዳች ነገር እንደማላደርግ ከዚህ ይልቅ እነዚህን ነገሮች የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ መሆኑን ታውቃላችሁ። እኔን የላከኝ ከእኔ ጋር ነው፤ ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን ስለማደርግ ብቻዬን አልተወኝም።”—ዮሐንስ 8:28, 29

ይሁንና አንዳንድ አይሁዳውያን በኢየሱስ አመኑ፤ እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ቃሌን ጠብቃችሁ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል።”—ዮሐንስ 8:31, 32

‘ነፃ ትወጣላችሁ’ የሚለው ሐሳብ ለአንዳንዶች እንግዳ ሆነባቸው። በመሆኑም “እኛ የአብርሃም ዘር ነን፤ ለማንም ባሪያዎች ሆነን አናውቅም። ታዲያ አንተ ‘ነፃ ትወጣላችሁ’ እንዴት ትለናለህ?” በማለት ተቃውሟቸውን ገለጹ። አይሁዳውያን በሌሎች ብሔራት አገዛዝ ሥር የነበሩባቸው ወቅቶች እንዳሉ ቢያውቁም ባሪያ ተብለው መጠራት አልፈለጉም። ኢየሱስ ግን “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው” በማለት አሁንም ባሪያ እንደሆኑ ጠቆማቸው።—ዮሐንስ 8:33, 34

አይሁዳውያን የኃጢአት ባሪያዎች መሆናቸውን ለመቀበል ባለመፈለጋቸው በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ናቸው። ኢየሱስ “ባሪያ በጌታው ቤት ለዘለቄታው አይኖርም፤ ልጅ ከሆነ ግን ሁልጊዜ ይኖራል” አላቸው። (ዮሐንስ 8:35) አንድ ባሪያ የወራሽነት መብት የለውም፤ ደግሞም በማንኛውም ጊዜ ሊባረር ይችላል። በቤተሰቡ ውስጥ “ለዘለቄታው” ማለትም በሕይወት እስካለ ድረስ የሚቆየው ከቤተሰቡ የተወለደ ወይም በማደጎነት የተወሰደ ልጅ ብቻ ነው።

በመሆኑም ሞት ከሚያስከትል ኃጢአት ሰዎችን ለዘለቄታው ነፃ የሚያወጣው እውነት፣ ስለ ወልድ የሚገልጸው እውነት ነው። ኢየሱስ “ወልድ ነፃ ካወጣችሁ፣ በእርግጥ ነፃ ትሆናላችሁ” አለ።—ዮሐንስ 8:36