በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 65

ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ የሰጠው ትምህርት

ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ የሰጠው ትምህርት

ማቴዎስ 8:19-22 ሉቃስ 9:51-62 ዮሐንስ 7:2-10

  • የኢየሱስ ወንድሞች ለእሱ ያላቸው አመለካከት

  • የመንግሥቱ አገልግሎት ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

ኢየሱስ ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎቱን በዋነኝነት ያከናወነው በገሊላ ብቻ ነው፤ ከይሁዳ ይልቅ በዚህ አካባቢ ሰሚ ጆሮ አግኝቷል። በዚያ ላይ ደግሞ ኢየሩሳሌም በሄደበት ጊዜ በሰንበት አንድ ሰው በመፈወሱ ‘አይሁዳውያኑ እሱን ለመግደል ይበልጥ ተነስተው’ ነበር።—ዮሐንስ 5:18፤ 7:1

ወቅቱ በ32 ዓ.ም. መስከረም ወይም ጥቅምት ወር ሲሆን የዳስ በዓል የሚከበርበት ጊዜ ቀርቧል። ይህ በዓል የሚከበረው ለሰባት ቀን ነው፤ ከዚያም በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይደረጋል። በዓሉ የእርሻው ወቅት ማብቃቱን የሚያመለክት ሲሆን ሕዝቡ በጣም የሚደሰትበትና ምስጋና የሚያቀርብበት ጊዜ ነው።

የኢየሱስ ወንድሞች የሆኑት ያዕቆብ፣ ስምዖን፣ ዮሴፍና ይሁዳ “ከዚህ ተነስተህ ወደ ይሁዳ ሂድ” በማለት ጎተጎቱት። ኢየሩሳሌም የአገሪቱ ሃይማኖታዊ ማዕከል ነች። በሦስቱ ዓመታዊ በዓላት ወቅት ከተማዋ በሕዝብ ትጨናነቃለች። የኢየሱስ ወንድሞች “በይፋ እንዲታወቅ እየፈለገ በስውር የሚሠራ ሰው የለምና። እነዚህን ነገሮች የምትሠራ ከሆነ ራስህን ለዓለም ግለጥ” አሉት።—ዮሐንስ 7:3, 4

ለነገሩ እነዚህ አራት ወንድሞቹ መሲሕ መሆኑን “አላመኑበትም።” ያም ቢሆን ወንድሞቹ፣ በበዓሉ ላይ የሚገኙ ሁሉ ኢየሱስ ተአምር ሲፈጽም እንዲያዩት ፈልገዋል። ኢየሱስ ሁኔታው አደገኛ መሆኑን ስለተገነዘበ እንዲህ አላቸው፦ “ዓለም እናንተን የሚጠላበት ምንም ምክንያት የለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ እንደሆነ ስለምመሠክርበት ይጠላኛል። እናንተ ወደ በዓሉ ሂዱ፤ እኔ ግን ገና ጊዜዬ ስላልደረሰ ወደ በዓሉ አልሄድም።”—ዮሐንስ 7:5-8

የኢየሱስ ወንድሞች የተጓዙት፣ ወደ በዓሉ የሚሄዱት አብዛኞቹ ሰዎች ካሉበት ቡድን ጋር ነው፤ ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ብዙ ሰው ሳያያቸው በድብቅ ተጓዙ። ለመጓዝ የመረጡት፣ አብዛኞቹ ሰዎች በሚሄዱበት በዮርዳኖስ ወንዝ አቅራቢያ ባለው መንገድ ሳይሆን በሰማርያ በኩል ባለው ቀጥተኛ መንገድ ነው። ኢየሱስና አብረውት ያሉት ሰዎች በሰማርያ ማረፊያ ስለሚያስፈልጋቸው አንዳንድ ዝግጅቶች እንዲያደርጉ አስቀድሞ መልእክተኞች ላከ። በአንድ መንደር ያሉት ሰዎች ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄደ መሆኑን ስላወቁ እሱን ለመቀበልም ሆነ የተለመደውን መስተንግዶ ለማድረግ ፈቃደኞች አልሆኑም። ያዕቆብና ዮሐንስ በጣም ተናደው “ጌታ ሆይ፣ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲያጠፋቸው እንድናዝ ትፈልጋለህ?” ብለው ጠየቁት። (ሉቃስ 9:54) ኢየሱስ ግን እንዲህ ዓይነት ሐሳብ በማቅረባቸው ገሠጻቸው፤ ከዚያም ጉዟቸውን ቀጠሉ።

በመንገድ ላይ እያሉ ከጸሐፍት አንዱ ኢየሱስን “መምህር፣ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው። ኢየሱስም “ቀበሮዎች ጉድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ቦታ የለውም” ብሎ መለሰለት። (ማቴዎስ 8:19, 20) ኢየሱስ ይህን ሲል፣ ጸሐፊው የእሱ ተከታይ ከሆነ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሙት መግለጹ ነው። ጸሐፊው ኩሩ ስለሆነ እንዲህ ዓይነቱን አኗኗር የሚቀበል አይመስልም። እኛም ‘ኢየሱስን  ለመከተል ምን ያህል ፈቃደኛ ነኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን።

ኢየሱስ አንድን ሌላ ሰው “ተከታዬ ሁን” አለው። ሰውየውም “ጌታ ሆይ፣ በመጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” በማለት መለሰ። ኢየሱስ የሰውየውን ሁኔታ ስለተረዳ “ሙታን ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው፤ አንተ ግን ሄደህ የአምላክን መንግሥት በየቦታው አውጅ” አለው። (ሉቃስ 9:59, 60) ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው በወቅቱ የሰውየው አባት አልሞተም። ይህ ሰው አባቱ ሞቶ ቢሆን ኖሮ እዚህ መጥቶ ከኢየሱስ ጋር ይነጋገራል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ግለሰቡ በሕይወቱ ውስጥ የአምላክን መንግሥት ለማስቀደም አልተዘጋጀም።

ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርጉትን ጉዞ ሲቀጥሉ አንድ ሌላ ሰው “ጌታ ሆይ፣ እኔ እከተልሃለሁ፤ በመጀመሪያ ግን ቤተሰቤን እንድሰናበት ፍቀድልኝ” አለው። ኢየሱስም መልሶ “ዕርፍ ጨብጦ በኋላው ያሉትን ነገሮች የሚመለከት ሰው ለአምላክ መንግሥት የሚገባ አይደለም” አለው።—ሉቃስ 9:61, 62

የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መሆን የሚፈልጉ ሁሉ ትኩረታቸውን በመንግሥቱ አገልግሎት ላይ ማድረግ አለባቸው። አንድ አራሽ ፊት ለፊት የማያይ ከሆነ ትልሙ መጣመሙ አይቀርም። እንዲሁም ከኋላው ያለውን ለመመልከት ሲል ዕርፉን የሚያስቀምጥ ከሆነ ሥራው ይጓተታል። በተመሳሳይም ወደ ኋላ ዞሮ ይህን አሮጌ ሥርዓት የሚመለከት ማንኛውም ሰው ሊደናቀፍና ወደ ዘላለም ሕይወት ከሚወስደው መንገድ ሊወጣ ይችላል።