በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 30

ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ነው

ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ነው

ዮሐንስ 5:17-47

  • ይሖዋ የኢየሱስ አባት ነው

  • የትንሣኤ ተስፋ ተሰጠ

አንዳንድ አይሁዳውያን፣ ኢየሱስ አንድን ሰው በመፈወሱ የሰንበትን ሕግ እንደጣሰ ገልጸው በከሰሱት ጊዜ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም እሠራለሁ” ሲል መለሰላቸው።—ዮሐንስ 5:17

ኢየሱስ ያደረገው ነገር፣ አምላክ ስለ ሰንበት በሰጠው ሕግ ላይ የተከለከለ አይደለም። ኢየሱስ መስበኩና መፈወሱ፣ መልካም ሥራዎችን በማከናወን ረገድ የአምላክን ምሳሌ እንደተከተለ ያሳያል። በመሆኑም ኢየሱስ በየዕለቱ መልካም ነገር ያከናውናል። ከሳሾቹ ግን ኢየሱስ የሰጣቸው መልስ ከበፊቱ ይበልጥ አናደዳቸው፤ ሊገድሉትም ፈለጉ። ለምን?

ሊገድሉት የፈለጉት፣ ‘ኢየሱስ ሰዎችን በመፈወስ የሰንበትን ሕግ ጥሷል’ የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ስላላቸው ብቻ ሳይሆን የአምላክ ልጅ እንደሆነ በመናገሩ በጣም ስለተበሳጩም ጭምር ነው። ኢየሱስ፣ ይሖዋ አባቱ እንደሆነ መናገሩ አምላክን እንደ መዳፈር በሌላ አባባል ራሱን ከአምላክ ጋር እኩል እንደ ማድረግ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። ኢየሱስ ግን የፍርሃት ስሜት አላደረበትም፤ እንዲያውም ከአምላክ ጋር ስላለው ልዩ ዝምድና ተጨማሪ ነገር ነገራቸው። “አብ ወልድን ይወደዋል፤ እንዲሁም እሱ ራሱ የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ያሳየዋል” አላቸው።—ዮሐንስ 5:20

ሕይወት የሚሰጠው አብ ነው፤ እሱም ቀደም ባሉት ዘመናት ሰዎች ሙታንን እንዲያስነሱ ኃይል በመስጠት ይህንን አሳይቷል። ኢየሱስ በመቀጠል “አብ ሙታንን እንደሚያስነሳቸውና ሕያው እንደሚያደርጋቸው ሁሉ ወልድም እንዲሁ የፈለገውን ሰው ሕያው ያደርጋል” አለ። (ዮሐንስ 5:21) ትልቅ ትርጉም ያለው ይህ ሐሳብ እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ ነው! አሁንም እንኳ ወልድ በመንፈሳዊ ሁኔታ ሙታንን እያስነሳ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ “ቃሌን የሚሰማና የላከኝን የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ ወደ ፍርድም አይመጣም፤ ከዚህ ይልቅ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻግሯል” ብሏል።—ዮሐንስ 5:24

እስከዚህ ጊዜ ድረስ ኢየሱስ ከሞት ያስነሳው ሰው ስለመኖሩ የሚናገር ዘገባ ባይኖርም ወደፊት ቃል በቃል ሙታን እንደሚነሱ ለከሳሾቹ ነግሯቸዋል። ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን ሰምተው የሚወጡበት ሰዓት ይመጣል’ ብሏቸዋል።—ዮሐንስ 5:28, 29

ኢየሱስ ልዩ ሚና የተሰጠው ቢሆንም የአምላክ የበታች መሆኑን በግልጽ ሲናገር ‘በራሴ ተነሳስቼ አንድም ነገር ማድረግ አልችልም። የራሴን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ መፈጸም እፈልጋለሁ’ ብሏል። (ዮሐንስ 5:30) ያም ቢሆን ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና ገልጿል፤ እስከዚህ ጊዜ ድረስ በሕዝብ ፊት እንዲህ በግልጽ ተናግሮ አያውቅም። የኢየሱስ ከሳሾች ከእሱ በተጨማሪ ስለ እነዚህ ነገሮች የመሠከረላቸው ሰው አለ። ኢየሱስ “ወደ [መጥምቁ] ዮሐንስ ሰዎች ልካችሁ ነበር፤ እሱም ለእውነት መሥክሯል” በማለት አስታውሷቸዋል።—ዮሐንስ 5:33

የኢየሱስ ከሳሾች፣ ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት ዮሐንስ ከእሱ በኋላ ስለሚመጣው ሰው ይኸውም “ነቢዩ” እና “ክርስቶስ” ተብሎ ስለተጠራው ግለሰብ ለሃይማኖት መሪዎቹ መናገሩን ሰምተው መሆን አለበት። (ዮሐንስ 1:20-25) ኢየሱስ፣ ከሳሾቹ አሁን በእስር ላይ የሚገኘውን ዮሐንስን በአንድ ወቅት ከፍ አድርገው ይመለከቱት እንደነበር ለማስታወስ “ለጥቂት ጊዜ በእሱ ብርሃን እጅግ ለመደሰት ፈቃደኞች ነበራችሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 5:35) ሆኖም ኢየሱስ፣ ከመጥምቁ ዮሐንስ የላቀ ምሥክር እንዳለው ገልጿል።

“እየሠራሁት ያለው ይህ ሥራ [በዚህ ወቅት የፈጸመውን ተአምር ጨምሮ] አብ እንደላከኝ ይመሠክራል” አለ። አክሎም ኢየሱስ “የላከኝ አብም ራሱ ስለ እኔ መሥክሯል” ሲል ተናገረ። (ዮሐንስ 5:36, 37) ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በተጠመቀበት ጊዜ አምላክ ስለ እሱ መሥክሯል።—ማቴዎስ 3:17

በእርግጥም የኢየሱስ ከሳሾች እሱን ላለመቀበል ምንም ምክንያት የላቸውም። ከሳሾቹ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንደሚመረምሩ ይናገራሉ፤ እነዚያው መጻሕፍት ግን ስለ እሱ ይመሠክራሉ! ኢየሱስ እንዲህ ሲል ደመደመ፦ “ሙሴን ብታምኑት ኖሮ እኔንም ታምኑኝ ነበር፤ እሱ ስለ እኔ ጽፏልና። ሆኖም እሱ የጻፈውን ካላመናችሁ እኔ የምናገረውን እንዴት ታምናላችሁ?”—ዮሐንስ 5:46, 47