በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 95

ስለ ፍቺና ልጆችን ስለ መውደድ የተሰጠ ትምህርት

ስለ ፍቺና ልጆችን ስለ መውደድ የተሰጠ ትምህርት

ማቴዎስ 19:1-15 ማርቆስ 10:1-16 ሉቃስ 18:15-17

  • አምላክ ስለ ፍቺ ያለውን አመለካከት ኢየሱስ ገለጸ

  • ነጠላነት ስጦታ ነው

  • እንደ ልጆች መሆን አስፈላጊ ነው

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከገሊላ ተነስተው የዮርዳኖስን ወንዝ በመሻገር በፔሪያ በኩል አልፈው ወደ ደቡብ የሚያቀናውን መንገድ ተያያዙት። ኢየሱስ ከዚህ ቀደም ፔሪያ በነበረበት ጊዜ አምላክ ፍቺን አስመልክቶ የሰጠውን መመሪያ ለፈሪሳውያን ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 16:18) አሁን ፈሪሳውያን፣ ኢየሱስን ለመፈተን ይህንን ጉዳይ አነሱ።

አንዲት ሴት “ነውር የሆነ ነገር” ከተገኘባት ባሏ ሊፈታት እንደሚችል ሙሴ ጽፏል። (ዘዳግም 24:1) ለፍቺ ምክንያት የሚሆነውን ነገር በተመለከተ የተለያየ አመለካከት አለ። አንዳንዶች፣ ቀላል በሆኑ ምክንያቶችም እንኳ ፍቺ መፈጸም እንደሚቻል ያምናሉ። በመሆኑም ፈሪሳውያን “አንድ ሰው በማንኛውም ምክንያት ሚስቱን እንዲፈታ ሕግ ይፈቅድለታል?” ብለው ጠየቁት።—ማቴዎስ 19:3

ኢየሱስ ሰብዓዊ አመለካከትን ከመደገፍ ይልቅ አምላክ ጋብቻን እንዴት እንዳቋቋመ በመግለጽ በዘዴ መልስ ሰጠ። እንዲህ አለ፦ “ፈጣሪ ከመጀመሪያውም ወንድና ሴት አድርጎ እንደፈጠራቸው አላነበባችሁም? ‘ከዚህ የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ ብሎ እንደተናገረስ አላነበባችሁም? በመሆኑም ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።” (ማቴዎስ 19:4-6) አምላክ፣ አዳምንና ሔዋንን ሲያጋባ ትዳራቸውን ማፍረስ እንደሚችሉ አልተናገረም።

ፈሪሳውያን፣ ኢየሱስን በመቃወም “ታዲያ ሙሴ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ሰጥቶ እንዲፈታት ያዘዘው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። (ማቴዎስ 19:7) ኢየሱስም “ሙሴ የልባችሁን ደንዳናነት አይቶ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ ፈቀደላችሁ እንጂ ከመጀመሪያው እንዲህ አልነበረም” አላቸው። (ማቴዎስ 19:8) “ከመጀመሪያ” የተባለው የሙሴ ዘመን ሳይሆን አምላክ በኤደን የመጀመሪያውን ጋብቻ ያቋቋመበት ጊዜ ነው።

ኢየሱስ በመቀጠል የሚከተለውን ጠቃሚ ሐቅ ተናገረ፦ “እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፆታ ብልግና [ግሪክኛ፣ ፖርኒያ] ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።” (ማቴዎስ 19:9) እንግዲያው ከቅዱሳን መጻሕፍት አንጻር ተቀባይነት ያለው ለፍቺ መሠረት የሚሆን ምክንያት የፆታ ብልግና ብቻ ነው።

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህን ሲሰሙ “በባልና በሚስት መካከል ያለው ሁኔታ እንዲህ ከሆነስ አለማግባት ይመረጣል” አሉ። (ማቴዎስ 19:10) በእርግጥም ለማግባት የሚያስብ ሰው ትዳር ዘላቂ ጥምረት እንደሆነ ማስታወስ ይኖርበታል!

ከነጠላነት ጋር በተያያዘ ደግሞ ኢየሱስ፣ አንዳንዶች ጃንደረባ ሆነው ስለሚወለዱ የፆታ ግንኙነት መፈጸም እንደማይችሉ ገለጸ። ሌሎች የፆታ ግንኙነት መፈጸም የማይችሉት ሰዎች ስለሰለቧቸው ነው። አንዳንዶች ግን የፆታ ስሜታቸውን በመግታት ራሳቸውን ጃንደረባ ያደርጋሉ። ይህን የሚያደርጉት ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ይበልጥ ትኩረት ለመስጠት ሲሉ ነው። ኢየሱስ “ይህን [ነጠላነትን] ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው” በማለት አድማጮቹን አሳሰበ።—ማቴዎስ 19:12

በዚህ ጊዜ ሰዎች ሕፃናትን ወደ ኢየሱስ ያመጡ ጀመር። ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስን እንዳይረብሹት አስበው ሳይሆን አይቀርም ሕዝቡን ገሠጿቸው። ኢየሱስ ይህን ሲያይ ተቆጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የአምላክ መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ነውና። እውነት እላችኋለሁ፣ የአምላክን መንግሥት እንደ አንድ ትንሽ ልጅ ሆኖ የማይቀበል ሁሉ ፈጽሞ ወደዚህ መንግሥት አይገባም።”—ማርቆስ 10:14, 15፤ ሉቃስ 18:15

ይህ እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ነው! የአምላክን መንግሥት ለመውረስ ልክ እንደ ትናንሽ ልጆች የዋሆችና ለመማር ዝግጁዎች መሆን አለብን። ኢየሱስ ሕፃናቱን በማቀፍና በመባረክ እንደሚወዳቸው አሳይቷል። “የአምላክን መንግሥት እንደ አንድ ትንሽ ልጅ ሆኖ” ለሚቀበል ሁሉ ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ጥልቅ ፍቅር አለው።—ሉቃስ 18:17