በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 85

ንስሐ በሚገባ ኃጢአተኛ መደሰት

ንስሐ በሚገባ ኃጢአተኛ መደሰት

ሉቃስ 15:1-10

  • የጠፋችው በግ እና የጠፋው ሳንቲም ምሳሌ

  • በሰማይ ያሉ መላእክት ይደሰታሉ

ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲያከናውን የትሕትናን አስፈላጊነት በተለያዩ ጊዜያት ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ሉቃስ 14:8-11) አምላክን በትሕትና ማገልገል የሚፈልጉ ሰዎችን ለማግኘት ጓጉቷል። እስካሁን ካገኛቸው እንደዚህ ዓይነት ሰዎች አንዳንዶቹ አሁንም በኃጢአት ጎዳና እየተመላለሱ ሊሆን ይችላል።

እንዲህ ያሉትን ሰዎች ፈሪሳውያንና ጸሐፍት ብቁ እንዳልሆኑ አድርገው ይቆጥሯቸዋል፤ ሆኖም እነዚህ ሰዎች ኢየሱስንም ሆነ መልእክቱን እንደተቀበሉ ፈሪሳውያንና ጸሐፍት አስተውለዋል። በመሆኑም “ይህ ሰው ኃጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነሱም ጋር ይበላል” ብለው አጉረመረሙ። (ሉቃስ 15:2) ፈሪሳውያንና ጸሐፍት ራሳቸውን ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ከመሆኑም በላይ ተራውን ሕዝብ እግራቸው ሥር እንዳለ ቆሻሻ አድርገው ይቆጥሩታል። እንዲያውም የሃይማኖት መሪዎቹ ለእነዚህ ሰዎች ያላቸውን ንቀት ለመግለጽ አምሃአሬትስ ይኸውም “የአገሬው [የመሬት] ሰዎች” የሚለውን የዕብራይስጥ አገላለጽ ይጠቀማሉ።

ከዚህ በተቃራኒ ኢየሱስ ሁሉንም ሰው በአክብሮት፣ በደግነትና በርኅራኄ ይይዛል። በዚህም ምክንያት በኃጢአት ድርጊታቸው በስፋት የሚታወቁ አንዳንድ ሰዎችን ጨምሮ ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ብዙዎች ኢየሱስን ለመስማት ይጓጓሉ። ታዲያ ኢየሱስ እንዲህ ያሉትን ሰዎች በመርዳቱ ትችት ሲሰነዘርበት ምን ተሰማው? ምን ምላሽስ ሰጠ?

ኢየሱስ ቀደም ሲል በቅፍርናሆም ከሰጠው ጋር የሚመሳሰል ልብ የሚነካ ምሳሌ በመናገር ለዚህ ጥያቄ ግልጽ መልስ ሰጠ። (ማቴዎስ 18:12-14) ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ ፈሪሳውያኑን ጻድቅ እንደሆኑና በአምላክ በረት ውስጥ እንዳሉ አድርጎ ገልጿቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ዝቅ ተደርገው የሚታዩት ሰዎች እንደባዘኑና እንደጠፉ ተደርገው ተገልጸዋል። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦

“ከእናንተ መካከል 100 በጎች ያሉት ሰው አንዷ ብትጠፋበት 99ኙን በምድረ በዳ ትቶ የጠፋችውን እስኪያገኝ ድረስ አይፈልግም? በሚያገኛትም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ላይ ይሸከማታል። ቤት ሲደርስም ጓደኞቹንና ጎረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ ‘የጠፋችውን በጌን ስላገኘኋት የደስታዬ ተካፋዮች ሁኑ’ ይላቸዋል።”—ሉቃስ 15:4-6

ኢየሱስ ከታሪኩ የሚገኘውን ትምህርት ያብራራው እንዴት ነው? “እላችኋለሁ፣ ልክ እንደዚሁ ንስሐ መግባት ከማያስፈልጋቸው 99 ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ አንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ታላቅ ደስታ ይሆናል” አለ።—ሉቃስ 15:7

ኢየሱስ ንስሐ ስለ መግባት መናገሩ ፈሪሳውያኑን ሳያስገርማቸው አልቀረም። ፈሪሳውያን ራሳቸውን እንደ ጻድቅ አድርገው የሚቆጥሩ ሲሆን ንስሐ መግባት እንደሚያስፈልጋቸው አይሰማቸውም። ከሁለት ዓመት በፊት አንዳንዶቹ ኢየሱስን ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኃጢአተኞች ጋር በመብላቱ በነቀፉት ጊዜ “እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ልጠራ ነው” ብሏቸው ነበር። (ማርቆስ 2:15-17) ራሳቸውን የሚያመጻድቁት ፈሪሳውያን፣ ንስሐ  መግባት እንዳለባቸው አያስተውሉም፤ በመሆኑም በእነሱ የተነሳ በሰማይ ደስታ አይኖርም። ኃጢአተኞች ንስሐ ሲገቡ ግን ሁኔታው ከዚህ እጅግ የተለየ ነው።

ኢየሱስ፣ የጠፉ ኃጢአተኞች መመለሳቸው በሰማይ ታላቅ ደስታ የሚያመጣ መሆኑን ይበልጥ ጠበቅ አድርጎ ለመግለጽ ሌላ ምሳሌ ተናገረ፤ ይህ ምሳሌ በቤት ውስጥ በሚያጋጥም ነገር ላይ ያተኮረ ነው፦ “አሥር ድራክማ ሳንቲሞች ያሏት አንዲት ሴት አንዱ ድራክማ ቢጠፋባት መብራት አብርታ ቤቷን በመጥረግ እስክታገኘው ድረስ በደንብ አትፈልገውም? ሳንቲሙን ባገኘችው ጊዜም ጓደኞቿንና ጎረቤቶቿን በአንድነት ጠርታ ‘የጠፋብኝን ድራክማ ሳንቲም ስላገኘሁት የደስታዬ ተካፋዮች ሁኑ’ ትላቸዋለች።”—ሉቃስ 15:8, 9

ከዚህ ምሳሌ የሚገኘው ትምህርት ኢየሱስ ስለ ጠፋችው በግ ከተናገረው ምሳሌ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ “እላችኋለሁ፣ ልክ እንደዚሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በአምላክ መላእክት ዘንድ ደስታ ይሆናል” አለ።—ሉቃስ 15:10

እስቲ አስበው፣ የአምላክ መላእክት የጠፉ ኃጢአተኞችን መመለስ በከፍተኛ ትኩረት ይከታተላሉ! ይህም የሚያስደንቅ ነው፤ ምክንያቱም ንስሐ ገብተው በሰማይ የሚገኘውን የአምላክ መንግሥት የሚወርሱት ኃጢአተኛ የነበሩ ሰዎች ከመላእክት እንኳ የላቀ ቦታ ይሰጣቸዋል! (1 ቆሮንቶስ 6:2, 3) ይሁን እንጂ መላእክት የቅናት ስሜት አያድርባቸውም። ታዲያ እኛስ አንድ ኃጢአተኛ ከልቡ ንስሐ ገብቶ ወደ አምላክ ሲመለስ ምን ሊሰማን ይገባል?