በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 138

ክርስቶስ በአምላክ ቀኝ

ክርስቶስ በአምላክ ቀኝ

የሐዋርያት ሥራ 7:56

  • ኢየሱስ በአምላክ ቀኝ ተቀመጠ

  • ሳኦል ደቀ መዝሙር ሆነ

  • የምንደሰትበት ምክንያት አለን

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ ከአሥር ቀናት በኋላ፣ በጴንጤቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ መፍሰሱ እሱ በሰማይ እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ይህን የሚያረጋግጥ ሌላም ማስረጃ ሊታይ ነው። ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስ በታማኝነት በመስበኩ ከመወገሩ በፊት “እነሆ፣ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በአምላክ ቀኝ ቆሞ አያለሁ” ሲል ተናገረ።—የሐዋርያት ሥራ 7:56

ኢየሱስ ከአባቱ ጋር በሰማይ ተቀምጦ በአምላክ ቃል ውስጥ በትንቢት የተነገረው ትእዛዝ እስኪሰጠው ይጠብቃል። ዳዊት በመንፈስ መሪነት “ይሖዋ ጌታዬን [ኢየሱስን] ‘ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ’ አለው” በማለት ጽፏል። በአምላክ ቀኝ ሆኖ የሚጠብቅበት ጊዜ ሲጠናቀቅ ኢየሱስ ‘በጠላቶቹ መካከል በድል አድራጊነት ይገዛል።’ (መዝሙር 110:1, 2) ሆኖም ኢየሱስ በጠላቶቹ ላይ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ እስኪደርስ በሰማይ ሆኖ ሲጠብቅ ምን ያከናውናል?

በ33 ዓ.ም. በተከበረው ጴንጤቆስጤ ላይ የክርስቲያን ጉባኤ ተቋቋመ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ከሰማይ ሆኖ በመንፈስ በተቀቡ ደቀ መዛሙርቱ ላይ መግዛት ጀመረ። (ቆላስይስ 1:13) ለስብከቱ ሥራቸው አመራር የሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ ወደፊት ለሚኖራቸው ሚና አዘጋጃቸው። ይህ ሚና ምንድን ነው? እስከ ሞት ድረስ ታማኝ የሆኑት ደቀ መዛሙርት ከጊዜ በኋላ ትንሣኤ አግኝተው በመንግሥቱ ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ ነገሥታት ይሆናሉ።

ነገሥታት ከሚሆኑት መካከል አንዱ፣ ጳውሎስ በሚለው ሮማዊ ስሙ ይበልጥ የሚታወቀው ሳኦል ነው። ሳኦል ለአምላክ ሕግ ሲቀና የኖረ አይሁዳዊ ነው፤ ሆኖም የሃይማኖት መሪዎቹ የተሳሳተ አመለካከት እንዲያዳብር ስላደረጉት በእስጢፋኖስ መወገር እንኳ ተስማምቷል። ከዚያም “በጌታ ደቀ መዛሙርት ላይ በመዛትና እነሱን ለመግደል ቆርጦ በመነሳት” ወደ ደማስቆ ሄደ። ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት አስሮ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያመጣ ለሳኦል ሥልጣን ሰጠው። (የሐዋርያት ሥራ 7:58፤ 9:1) ይሁንና ሳኦል መንገድ ላይ እያለ ደማቅ ብርሃን በዙሪያው አንጸባረቀ፤ እሱም መሬት ላይ ወደቀ።

ከዚያም “ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምፅ ሰማ፤ ተናጋሪውን ግን ማየት አልቻለም። ሳኦልም “ጌታዬ፣ አንተ ማን ነህ?” ሲል ጠየቀ። በዚህ ጊዜ “እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ” የሚል መልስ አገኘ።—የሐዋርያት ሥራ 9:4, 5

ኢየሱስ፣ ሳኦል ወደ ደማስቆ ገብቶ ተጨማሪ መመሪያ እስኪሰጠው ድረስ እንዲጠብቅ ነገረው፤ ሆኖም ተአምራዊው ብርሃን ዓይኑን ስላሳወረው ወደ ከተማዋ ለመግባት የሚመራው ሰው አስፈለገው። በዚሁ ጊዜ ኢየሱስ በደማስቆ ከሚኖሩ ደቀ መዛሙርቱ አንዱ ለሆነው ለሐናንያ በራእይ  ተገለጠለት። ከዚያም ሐናንያ ወደ አንድ ቤት ሄዶ ሳኦልን እንዲያገኘው ነገረው። ሐናንያ ይህን ማድረግ ቢያስፈራውም ኢየሱስ የሚከተለውን ማረጋገጫ ሰጠው፦ “ይህ ሰው በአሕዛብ እንዲሁም በነገሥታትና በእስራኤል ልጆች ፊት ስሜን እንዲሸከም ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ስለሆነ ወደ እሱ ሂድ።” በኋላም ሳኦል እንደገና ማየት ቻለ፤ ከዚያም በደማስቆ “ስለ ኢየሱስ እሱ የአምላክ ልጅ እንደሆነ . . . መስበክ ጀመረ።”—የሐዋርያት ሥራ 9:15, 20

ጳውሎስና ሌሎች ወንጌላውያን ኢየሱስ የጀመረውን የስብከት ሥራ ቀጠሉ፤ የእሱ ድጋፍም አልተለያቸውም። አምላክ በጣም ውጤታማ እንዲሆኑ በመርዳት ባረካቸው። ጳውሎስ፣ ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ ኢየሱስ ከተገለጠለት ከ25 ዓመታት ገደማ በኋላ ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ” እንደተሰበከ ጽፏል።—ቆላስይስ 1:23

ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ ደግሞ ኢየሱስ በጣም ለሚወደው ለሐዋርያው ዮሐንስ ተከታታይ ራእዮችን አሳየው፤ እነዚህ ራእዮች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በራእይ መጽሐፍ ላይ ተመዝግበዋል። ዮሐንስ በሕይወት ቆይቶ፣ ኢየሱስ በመንግሥቱ ሥልጣን ሲመጣ በእነዚህ ራእዮች አማካኝነት ተመልክቷል። (ዮሐንስ 21:22) ዮሐንስ “በመንፈስ ወደ ጌታ ቀን ተወሰድኩ” ብሏል። (ራእይ 1:10) ይህ ጊዜ መቼ ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን በሚገባ ስንመረምር ‘የጌታ ቀን’ የጀመረው በዘመናችን እንደሆነ እንረዳለን። በ1914 አንደኛው የዓለም ጦርነት ፈነዳ። ከዚያ በኋላ ያሉት አሥርተ ዓመታት በጦርነት፣ በቸነፈር፣ በረሃብና በምድር መናወጥ ይታወቃሉ፤ እነዚህ ነገሮችና ሌሎች ማስረጃዎች ኢየሱስ ስለ ‘መገኘቱ’ እና ስለ “መጨረሻው” ለሐዋርያቱ የሰጠው “ምልክት” ታላቅ ፍጻሜውን እያገኘ እንዳለ ይጠቁማሉ። (ማቴዎስ 24:3, 7, 8, 14) በአሁኑ ጊዜ የመንግሥቱ ምሥራች በሮም ግዛት ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም እየተሰበከ ነው።

ዮሐንስ ይህ ምን ትርጉም እንዳለው በመንፈስ መሪነት ሲጽፍ “አሁን የአምላካችን ማዳን፣ ኃይልና መንግሥት እንዲሁም የእሱ መሲሕ ሥልጣን ሆኗል” ብሏል። (ራእይ 12:10) አዎን፣ ኢየሱስ በስፋት ያወጀውና በሰማይ ሆኖ የሚገዛው የአምላክ መንግሥት እውን ሆኗል!

ይህ ለኢየሱስ ታማኝ ደቀ መዛሙርት በሙሉ አስደሳች ዜና ነው። ዮሐንስ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ልብ ሊሉ ይችላሉ፦ “ስለዚህ እናንተ ሰማያትና በውስጣቸው የምትኖሩ ሁሉ ደስ ይበላችሁ! ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል።”—ራእይ 12:12

በመሆኑም ኢየሱስ አሁን በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ እየጠበቀ አይደለም። ንጉሥ ሆኖ እየገዛ ነው፤ በቅርቡ ደግሞ ጠላቶቹን በሙሉ ያጠፋል። (ዕብራውያን 10:12, 13) በእርግጥም ወደፊት የሚፈጸሙት ነገሮች በጣም የሚያጓጉ ናቸው!