በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኢየሱስ ከሞት የተነሳው ምን ዓይነት አካል ይዞ ነው? ሥጋዊ ወይስ መንፈሳዊ?

ኢየሱስ ከሞት የተነሳው ምን ዓይነት አካል ይዞ ነው? ሥጋዊ ወይስ መንፈሳዊ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ “ሥጋዊ አካል ለብሶ እያለ ተገደለ፤ ሆኖም መንፈሳዊ አካል ይዞ ሕያው ሆነ” በማለት ይናገራል።—1 ጴጥሮስ 3:18፤ የሐዋርያት ሥራ 13:34፤ 1 ቆሮንቶስ 15:45፤ 2 ቆሮንቶስ 5:16

 ኢየሱስ ቀደም ብሎ የተናገራቸው ቃላት በሥጋና በደም እንደማይነሳ ያሳያሉ። ኢየሱስ ‘ለዓለም ሕይወት ሲል ሥጋውን በመስጠት’ ለሰው ልጆች ቤዛ እንደሚሆን ተናግሯል። (ዮሐንስ 6:51፤ ማቴዎስ 20:28) ከሞት በተነሳ ጊዜ ሥጋውን ለብሶ ቢነሳ ኖሮ፣ ቤዛዊ መሥዋዕቱን እንደከፈለ ሊቆጠር አይችልም ነበር። ይህ ደግሞ ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ሥጋና ደሙን “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” መሥዋዕት አድርጎ እንዳቀረበ ይገልጻል።—ዕብራውያን 9:11, 12

ኢየሱስ የተነሳው መንፈሳዊ አካል ለብሶ ከነበረ ደቀ መዛሙርቱ እንዴት ሊያዩት ቻሉ?

  •  መንፈሳዊ ፍጥረታት ሥጋዊ አካል መልበስ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በጥንት ጊዜ አንዳንድ መላእክት ሥጋ ለብሰው ከመጡ በኋላ ከሰዎች ጋር እንደበሉና እንደጠጡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሶ እናገኛለን። (ዘፍጥረት 18:1-8፤ 19:1-3) ያም ሆኖ መንፍሳዊ ፍጥረታት ስለሆኑ ግዑዙን ዓለም ለቀው መሄድ ይችላሉ።—መሳፍንት 13:15-21

  •  ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ መላእክት ቀደም ብሎ ያደርጉት እንደነበረው ለአጭር ጊዜ የሰው አካል ለብሷል። ይሁንና መንፈሳዊ አካል እንደመሆኑ መጠን በድንገት መከሰትም ሆነ መሰወር ይችል ነበር። (ሉቃስ 24:31፤ ዮሐንስ 20:19, 26) ለብሶት ይታይ የነበረው ሥጋዊ አካል ሁልጊዜ ተመሳሳይ አልነበረም። በመሆኑም የቅርብ ወዳጆቹ እንኳን ኢየሱስን ይለዩት የነበረው በሚናገረው ወይም በሚያደርገው ነገር ነበር።—ሉቃስ 24:30, 31, 35፤ ዮሐንስ 20:14-16፤ 21:6, 7

  •  ኢየሱስ ለሐዋርያው ቶማስ በተገለጠ ጊዜ በለበሰው ሥጋዊ አካል ላይ የቁስሉ ምልክቶች ይታዩ ነበር። ይህንን ያደረገው ቶማስ የኢየሱስን መነሳት ተጠራጥሮ ስለነበር የእሱን እምነት ለማጠናከር ብሎ ነው።—ዮሐንስ 20:24-29