ኢዮብ 17:1-16

  • ኢዮብ መልስ መስጠቱን ቀጠለ (1-16)

    • “ፌዘኞች ከበውኛል” (2)

    • “አምላክ የሰዎች መቀለጃ አደረገኝ” (6)

    • “መቃብር፣ ቤቴ ይሆናል” (13)

17  “መንፈሴ ተሰብሯል፤ ዘመኔ አብቅቷል፤መቃብር ይጠብቀኛል።+   ፌዘኞች ከበውኛል፤+ዓይኔም የዓመፅ ተግባራቸውን በትኩረት ትመለከታለች።*   እባክህ፣ መያዣዬን ተቀብለህ አንተ ዘንድ አስቀምጥልኝ። እጄን የሚመታና ተያዥ የሚሆነኝ ሌላ ማን ይኖራል?+   ማስተዋልን ከልባቸው ሰውረሃልና፤+ከዚህም የተነሳ ከፍ ከፍ አታደርጋቸውም።   የልጆቹ ዓይን ደክሞ እያለ፣ያለውን ለወዳጆቹ ሊያካፍል ይችላል።   አምላክ የሰዎች መቀለጃ* አደረገኝ፤+በመሆኑም ፊቱ ላይ እንደሚተፉበት ሰው ሆንኩ።+   ከሐዘን የተነሳ ዓይኔ ፈዘዘ፤+እጆቼና እግሮቼም እንደ ጥላ ሆኑ።   ቅን የሆኑ ሰዎች በዚህ ነገር በመገረም ትኩር ብለው ይመለከታሉ፤ንጹሕ የሆነውም፣ አምላክ የለሽ* በሆነው ሰው ይረበሻል።   ጻድቅ መንገዱን በጥብቅ ይከተላል፤+እጁ ንጹሕ የሆነ ሰውም እየበረታ ይሄዳል።+ 10  ይሁን እንጂ ሁላችሁም ተመልሳችሁ መከራከራችሁን መቀጠል ትችላላችሁ፤ከእናንተ መካከል አንድም ጥበበኛ አላገኘሁምና።+ 11  የሕይወት ዘመኔ አበቃ፤+ዕቅዴና የልቤ ምኞት ተንኮታኮተ።+ 12  ሌሊቱን ወደ ቀን ይለውጣሉ፤‘ጨለማ ስለሆነ ብርሃን የሚፈነጥቅበት ጊዜ ቀርቧል’ ይላሉ። 13  ዝም ብዬ ብጠብቅ ያን ጊዜ መቃብር፣* ቤቴ ይሆናል፤+በጨለማ መኝታዬን እዘረጋለሁ።+ 14  ጉድጓዱን*+ ‘አንተ አባቴ ነህ!’ እለዋለሁ፤ ትሏን ‘አንቺ እናቴና እህቴ ነሽ!’ እላታለሁ። 15  እንግዲህ የእኔ ተስፋ የት አለ?+ ተስፋ እንዳለኝ አድርጎ የሚያስብስ ማን ነው? 16  ሁላችንም ተያይዘን ወደ አፈር ስንገባ፣ተስፋዬ ወደተቀረቀሩ የመቃብር* በሮች ይወርዳል።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በዓመፅ ተግባራቸው ላይ ተተከለች።”
ቃል በቃል “መተረቻ፤ ምሳሌ።”
ወይም “ከሃዲ።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “መቃብሩን።”
ወይም “የሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።