ኢዮብ 15:1-35

  • የኤሊፋዝ ሁለተኛ ዙር ንግግር (1-35)

    • ኢዮብ ፈሪሃ አምላክ እንደሌለው ተናገረ (4)

    • ኢዮብ እብሪተኛ እንደሆነ ገለጸ (7-9)

    • ‘አምላክ በቅዱሳኑ ላይ እምነት የለውም’ (15)

    • ‘ሥቃይ የሚደርስበት ሰው ክፉ ነው’ (20-24)

15  ቴማናዊው ኤሊፋዝ+ እንዲህ ሲል መለሰ፦   “ጥበበኛ ሰው ከንቱ በሆነ ንግግር* ይመልሳል?ወይስ በምሥራቅ ነፋስ ሆዱን ይሞላል?   በማይረባ ቃል መውቀስ ምንም ዋጋ የለውም፤ደግሞም ወሬ ብቻውን ምንም ጥቅም የለውም።   አንተ ፈሪሃ አምላክን ታጣጥላለህና፤ስለ አምላክ ማሰብም ዋጋ የለውም ትላለህ።   በደልህ በምትናገረው ነገር ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፤*ተንኮል ያዘለ ንግግር መናገርም ትመርጣለህ።   እኔ ሳልሆን የገዛ አፍህ ይፈርድብሃል፤የገዛ ከንፈሮችህ ይመሠክሩብሃል።+   ለመሆኑ ከሰው ሁሉ በፊት የተወለድከው አንተ ነህ?ወይስ የተወለድከው ከኮረብቶች በፊት ነው?   የአምላክን ሚስጥር ትሰማለህ?ወይስ ጥበብ ያለህ አንተ ብቻ ነህ?   እኛ የማናውቀው አንተ ግን የምታውቀው ምን ነገር አለ?+ ደግሞስ እኛ የማናስተውለው አንተ ግን የምታስተውለው ምን ነገር አለ? 10  የሸበቱም ሆኑ በዕድሜ የገፉ፣እንዲሁም ከአባትህ በዕድሜ እጅግ የሚበልጡ ከእኛ ጋር አሉ።+ 11  የአምላክ ማጽናኛ፣ወይም በለሰለሰ አንደበት የተነገረህ ቃል አነሰህ? 12  ልብህ ለምን ይታበያል?ዓይኖችህስ ለምን በቁጣ ይጉረጠረጣሉ? 13  በአምላክ ላይ ተቆጥተሃልና፤እንዲህ ያሉ ቃላትም ከገዛ አፍህ ወጥተዋል። 14  ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሟች የሆነ ሰው ምንድን ነው?ወይስ ጻድቅ ይሆን ዘንድ ከሴት የተወለደ ሰው ምንድን ነው?+ 15  እነሆ፣ በቅዱሳኑ* ላይ እምነት የለውም፤ሰማያትም እንኳ በፊቱ ንጹሐን አይደሉም።+ 16  ታዲያ ክፋትን እንደ ውኃ የሚጠጣ፣አስጸያፊና ብልሹ የሆነ ሰውማ እንዴት ሊታመን ይችላል?+ 17  አዳምጠኝ! እኔ አሳውቅሃለሁ። ያየሁትን እናገራለሁ፤ 18  ጥበበኛ ሰዎች ከአባቶቻቸው ሰምተው የተናገሩትን፣+ደግሞም ከሌሎች ያልሸሸጉትን ነገር እነግርሃለሁ። 19  ምድሪቱ የተሰጠችው ለእነሱ ብቻ ነበር፤በመካከላቸውም ባዕድ ሰው አላለፈም። 20  ክፉ ሰው ዕድሜውን ሁሉ፣ለጨቋኙ በተመደቡት ዓመታት በሙሉ ይሠቃያል። 21  አስፈሪ ድምፆችን ይሰማል፤+በሰላም ጊዜ ወራሪዎች ጥቃት ይሰነዝሩበታል። 22  ከጨለማ እንደሚያመልጥ አያምንም፤+ሰይፍም ይጠብቀዋል። 23  ‘ወዴት ነው?’ እያለ ምግብ* ፍለጋ ይቅበዘበዛል፤ የጨለማ ቀን እንደደረሰ በሚገባ ያውቃል። 24  ጭንቀትና ሥቃይ ያሸብሩታል፤ጥቃት ለመሰንዘር እንደተዘጋጀ ንጉሥ ያይሉበታል። 25  በአምላክ ላይ እጁን ያነሳልና፤ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ለመገዳደርም* ይሞክራል፤ 26  ወፍራምና ጠንካራ ጋሻ* አንግቦ፣በእልኸኝነት እየገሰገሰ ይመጣበታል፤ 27  ፊቱ በስብ ተሸፍኗል፤ወገቡም በስብ ተወጥሯል፤ 28  በሚፈራርሱ ከተሞች፣ደግሞም ማንም በማይኖርባቸውናየድንጋይ ክምር በሚሆኑ ቤቶች ውስጥ ይኖራል። 29  ባለጸጋ አይሆንም፤ ሀብቱም አይከማችም፤ንብረቱም በምድሪቱ ላይ አይበረክትም። 30  ከጨለማ አያመልጥም፤ነበልባል ቅርንጫፉን ያደርቀዋል፤*ከአምላክም* አፍ በሚወጣ እስትንፋስ ይጠፋል።+ 31  መንገድ መሳትና ከንቱ በሆነ ነገር መታመን የለበትም፤በአጸፋው የሚያገኘው ነገር ዋጋ አይኖረውምና፤ 32  ቀኑ ከመድረሱ በፊት ይፈጸማል፤ቅርንጫፎቹም አይለመልሙም።+ 33  ያልበሰሉ ፍሬዎቹን እንደሚጥል የወይን ተክል፣አበቦቹን እንደሚያረግፍ የወይራ ዛፍም ይሆናል። 34  አምላክ የለሽ የሆኑ ሰዎች* ጉባኤ ይመክናልና፤+የጉቦ ድንኳኖችም እሳት ይበላቸዋል። 35  ችግር ይፀንሳሉ፤ ክፉ ነገርም ይወልዳሉ፤ማህፀናቸውም ተንኮል ያፈራል።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “እንደ ነፋስ በሆነ እውቀት።”
ወይም “በደልህ አፍህን ያሠለጥነዋል።”
ወይም “በመላእክቱ።”
ቃል በቃል “ዳቦ።”
ወይም “ለማሸነፍም።”
ቃል በቃል “ወፍራም የጋሻ ጉብጉባት።”
ምንም ዓይነት የማንሰራራት ተስፋ እንደሌለው ያመለክታል።
ቃል በቃል “ከእሱም።”
ወይም “የከሃዲዎች።”