ኢዮብ 2:1-13

  • ሰይጣን የኢዮብን የልብ ዝንባሌ በተመለከተ በድጋሚ ጥያቄ አነሳ (1-5)

  • ሰይጣን ኢዮብን በቁስል እንዲመታው ተፈቀደለት (6-8)

  • የኢዮብ ሚስት “አምላክን እርገምና ሙት!” አለችው (9, 10)

  • የኢዮብ ሦስት ጓደኞች መጡ (11-13)

2  የእውነተኛው አምላክ ልጆች፣*+ በይሖዋ ፊት ለመቆም+ የሚገቡበት ቀን በደረሰ ጊዜ ሰይጣንም በይሖዋ ፊት ለመቆም እነሱ መካከል ገባ።+  ከዚያም ይሖዋ ሰይጣንን “ከየት መጣህ?” አለው። ሰይጣንም “በምድር ሁሉ ላይ ስዞርና በእሷ ላይ ስመላለስ ቆይቼ መጣሁ”+ ሲል ለይሖዋ መለሰ።  ይሖዋም ሰይጣንን እንዲህ አለው፦ “አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትከው?* በምድር ላይ እንደ እሱ ያለ ሰው የለም። በንጹሕ አቋም የሚመላለስ ቅን ሰው*+ እንዲሁም አምላክን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ነው። ያለምንም ምክንያት እንዳጠፋው* እኔን ለማነሳሳት ብትሞክርም+ እንኳ አሁንም በንጹሕ አቋሙ እንደጸና ነው።”+  ሆኖም ሰይጣን እንዲህ ሲል ለይሖዋ መለሰ፦ “ቁርበት ስለ ቁርበት ነው። ሰውም ለሕይወቱ* ሲል ያለውን ነገር ሁሉ ይሰጣል።  ሆኖም እስቲ እጅህን ዘርግተህ በአጥንቱና በሥጋው ላይ ጉዳት አድርስበት፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።”+  ከዚያም ይሖዋ ሰይጣንን “እነሆ፣ እሱ በእጅህ* ነው! ብቻ ሕይወቱን* እንዳታጠፋ!” አለው።  ሰይጣንም ከይሖዋ ፊት ወጥቶ በመሄድ ኢዮብን ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ ድረስ ክፉኛ በሚያሠቃይ እባጭ መታው።*+  ኢዮብም ገላውን የሚያክበት ገል ወሰደ፤ በአመድም ላይ ተቀመጠ።+  በመጨረሻም ሚስቱ “አሁንም በንጹሕ አቋምህ* እንደጸናህ ነው? አምላክን እርገምና ሙት!” አለችው። 10  እሱ ግን እንዲህ አላት፦ “የምትናገሪው ማመዛዘን እንደጎደላት ሴት ነው። ከእውነተኛው አምላክ መቀበል ያለብን መልካም ነገር ብቻ ነው? ክፉውንስ መቀበል የለብንም?”+ ኢዮብ ይህ ሁሉ ቢደርስበትም በከንፈሩ አልበደለም።+ 11  የኢዮብ ሦስት ጓደኞች* በእሱ ላይ የደረሰውን መከራ ሁሉ ሰምተው እያንዳንዳቸው ከሚኖሩበት ቦታ መጡ፤ ጓደኞቹም ቴማናዊው ኤሊፋዝ፣+ ሹሃዊው+ በልዳዶስ+ እና ናአማታዊው ሶፋር+ ነበሩ። እነሱም አንድ ላይ ተገናኝተው ወደ ኢዮብ በመሄድ እሱን ለማስተዛዘንና ለማጽናናት ተስማሙ። 12  ከሩቅ ሲመለከቱት እሱ መሆኑን መለየት አቃታቸው። እነሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማልቀስ ጀመሩ፤ ልብሳቸውንም ቀደዱ፤ እንዲሁም አቧራ ወደ ላይ በተኑ፤ ራሳቸውም ላይ ነሰነሱ።+ 13  ከዚያም ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊት መሬት ላይ ከእሱ ጋር ተቀመጡ። ሥቃዩ በጣም ከባድ+ መሆኑን ስለተረዱ ከመካከላቸው አንድም ቃል የተናገረው አልነበረም።

የግርጌ ማስታወሻዎች

የአምላክ ልጆች የሆኑትን መላእክት የሚያመለክት የዕብራይስጥ ፈሊጣዊ አነጋገር ነው።
ቃል በቃል “(በአገልጋዬ በኢዮብ) ላይ ልብህን አኑረሃል?”
ወይም “ነቀፋ የሌለበትና ቅን ሰው።”
ቃል በቃል “እንድውጠው።”
ወይም “ለነፍሱ።”
ወይም “በቁጥጥርህ ሥር።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “በከባድ ቁስል መታው።”
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል የሥነ ምግባር ንጽሕናን፣ ሁለት ልብ አለመሆንንና እንከን የለሽ መሆንን ያመለክታል።
ወይም “ኢዮብን የሚያውቁት ሦስት ሰዎች።”