ኢዮብ 36:1-33

 • ኤሊሁ የአምላክን ታላቅነት ከፍ ከፍ አደረገ (1-33)

  • ታዛዦች ይበለጽጋሉ፤ አምላክ የለሾች ግን ተቀባይነት አያገኙም (11-13)

  • ‘እንደ አምላክ ያለ አስተማሪ ማን ነው?’ (22)

  • ኢዮብ አምላክን ከፍ ከፍ ማድረግ ይጠበቅበታል (24)

  • “አምላክ እኛ ልናውቀው ከምንችለው በላይ ታላቅ ነው” (26)

  • አምላክ ዝናብንና መብረቅን ይቆጣጠራል (27-33)

36  ኤሊሁ በመቀጠል እንዲህ አለ፦   “አምላክን ወክዬ ገና የምናገረው ነገር ስላለጉዳዩን በማብራራበት ጊዜ ትንሽ ታገሠኝ።   ስለማውቀው ነገር በሰፊው እናገራለሁ፤ፈጣሪዬ ጻድቅ እንደሆነም አስታውቃለሁ።+   በእርግጥ የምናገረው ቃል ውሸት አይደለም፤እውቀቱ ፍጹም የሆነው አምላክ+ በፊትህ ነው።   በእርግጥ አምላክ ኃያል ነው፤+ ደግሞም ማንንም ገሸሽ አያደርግም፤የማስተዋል ችሎታው* ታላቅ ነው።   የክፉዎችን ሕይወት አይጠብቅም፤+ጎስቋላው ግን ፍትሕ እንዲያገኝ ያደርጋል።+   ዓይኖቹን ከጻድቃን ላይ አያነሳም፤+ከነገሥታት ጋር በዙፋን ላይ ያስቀምጣቸዋል፤*+ እነሱም ለዘላለም ከፍ ከፍ ይላሉ።   ይሁንና ሰዎች በሰንሰለት ቢታሰሩ፣በመከራም ገመድ ቢጠፈሩ፣   ከመታበያቸው የተነሳ ስለፈጸሙት ድርጊትይኸውም ስለ በደላቸው ይነግራቸዋል። 10  እርማት እንዲቀበሉ ጆሯቸውን ይከፍታል፤ከክፋትም እንዲመለሱ ይነግራቸዋል።+ 11  ቢታዘዙትና ቢያገለግሉት፣የሕይወት ዘመናቸውን በብልጽግና ይፈጽማሉ፤ሕይወታቸውም አስደሳች ይሆናል።+ 12  ባይታዘዙ ግን በሰይፍ* ይጠፋሉ፤+ያለእውቀትም ይሞታሉ። 13  በልባቸው አምላክ የለሽ* የሆኑ ቂም ይይዛሉ። እሱ በሚያስራቸው ጊዜም እንኳ እርዳታ ለማግኘት አይጮኹም። 14  ገና ወጣት እያሉ ይሞታሉ፤*+በቤተ መቅደስ ቀላጮች* መካከል ሕይወታቸውን ያሳልፋሉ።*+ 15  ሆኖም አምላክ* የተጎሳቆሉ ሰዎችን ከጉስቁልናቸው ይታደጋቸዋል፤ጭቆና በሚደርስባቸው ጊዜ ጆሯቸውን ይከፍታል። 16  እሱ ከመከራ መንጋጋ አስጥሎ+የሚያጨናንቅ ነገር ወደሌለበት ሰፊ ስፍራ ያመጣሃል፤+ማዕድህ ምርጥ በሆነ ምግብ የተሞላ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ያጽናናሃል።+ 17  ፍርድ ሲበየንና ፍትሕ ሲሰፍን፣በክፉዎች ላይ በሚፈጸመው ፍርድ ትረካለህ።+ 18  ይሁንና ቁጣ ወደ ክፋት* እንዳይመራህ ተጠንቀቅ፤+ጠቀም ያለ ጉቦም አያስትህ። 19  እርዳታ ለማግኘት መጮኽህ፣ወይም የምታደርገው ማንኛውም ብርቱ ጥረት ከጭንቀት ነፃ ያደርግሃል?+ 20  ሰዎች ካሉበት ስፍራ የሚጠፉበትንየሌሊቱን ጊዜ አትናፍቅ። 21  ከጉስቁልና ይልቅ ይህን መርጠህ፣+ወደ ክፋት እንዳትመለስ ተጠንቀቅ። 22  እነሆ፣ አምላክ በኃይሉ ከፍ ከፍ ብሏል፤እንደ እሱ ያለ አስተማሪ ማን ነው? 23  እሱን መንገድ የመራው፣*ወይም ‘የሠራኸው ነገር ትክክል አይደለም’ ያለው ማን ነው?+ 24  ሰዎች በመዝሙር ያወደሱትን፣+የእሱን ሥራ ከፍ ከፍ ማድረግ አትዘንጋ።+ 25  የሰው ልጆች ሁሉ አይተውታል፤ሟች የሆነ ሰው ከሩቅ ያያል። 26  አዎ፣ አምላክ እኛ ልናውቀው ከምንችለው በላይ ታላቅ ነው፤+የዘመኑም ቁጥር ከመረዳት ችሎታ በላይ ነው።*+ 27  እሱ የውኃ ጠብታዎችን ወደ ላይ ይስባል፤+ጭጋጉም ወደ ዝናብነት ይለወጣል፤ 28  ከዚያም ደመናት ያዘንባሉ፤+በሰው ልጆችም ላይ ዶፍ ያወርዳሉ። 29  የደመናትን ንብርብር፣ከድንኳኑም የሚሰማውን ነጎድጓድ+ ማን ሊያስተውል ይችላል? 30  መብረቁን*+ በላዩ ላይ እንዴት እንደሚዘረጋ፣የባሕሩንም ወለል* እንዴት እንደሚሸፍን ተመልከት። 31  በእነዚህም ሕዝቦችን ያኖራል፤*ምግብ አትረፍርፎ ይሰጣቸዋል።+ 32  በእጆቹ መብረቁን ይሸፍናል፤ወደ ዒላማውም ይሰደዋል።+ 33  ነጎድጓዱ ስለ እሱ ይናገራል፤ከብቶች እንኳ ሳይቀሩ ማን* እየመጣ እንዳለ ይጠቁማሉ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “የልቡ ኃይል።”
“ነገሥታትን በዙፋን ላይ ያስቀምጣል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በመሣሪያ (በተወንጫፊ መሣሪያ)።”
ወይም “ከሃዲ።”
ወይም “ነፍሳቸው ትሞታለች።”
ግብረ ሰዶማውያን ሆነው የሴት ዓይነት ሚና ያላቸውን ወንዶች ያመለክታል።
“ሕይወታቸው ይቀጫል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “እሱ።”
ወይም “ይሁንና ቁጣ በንቀት ወደማጨብጨብ።”
“እሱን የተቸው፤ ተጠያቂ ያደረገው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “አይመረመርም።”
ቃል በቃል “ብርሃኑን።”
ቃል በቃል “ሥር።”
“ለሕዝቦች ይሟገታል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“ምን” ማለትም ሊሆን ይችላል።