ኢዮብ 39:1-30

 • እንስሳት የሰውን አላዋቂነት ያሳያሉ (1-30)

  • የተራራ ፍየሎችና ርኤሞች (1-4)

  • የዱር አህያ (5-8)

  • የዱር በሬ (9-12)

  • ሰጎን (13-18)

  • ፈረስ (19-25)

  • ሲላ እና ንስር (26-30)

39  “የተራራ ፍየሎች የሚወልዱበትን ጊዜ ታውቃለህ?+ ርኤሞች* ግልገሎቻቸውን ሲወልዱ ተመልክተሃል?+   የእርግዝናቸው ወራት ምን ያህል እንደሆነ መቁጠር ትችላለህ? የሚወልዱበትን ጊዜስ ታውቃለህ?   ግልገሎቻቸውን ተንበርክከው ይወልዳሉ፤ከምጣቸውም ይገላገላሉ።   ግልገሎቻቸው ይጠነክራሉ፤ በሜዳም ያድጋሉ፤ይሄዳሉ፤ ወደ እነሱም አይመለሱም።   የዱር አህያውን ነፃ የለቀቀው፣+የዱር አህያውን ከእስራቱ የፈታውስ ማን ነው?   በረሃማው ሜዳ ቤቱ፣ጨዋማውም ምድር መኖሪያው እንዲሆን አደረግኩ።   በከተማ ሁካታ ያፌዛል፤የነጂውንም ጩኸት አይሰማም።   መሰማሪያ ለማግኘት በኮረብቶች ላይ ይቅበዘበዛል፤ማንኛውንም አረንጓዴ ተክል ይፈልጋል።   የዱር በሬ አንተን ለማገልገል ፈቃደኛ ነው?+ በጋጣህ ውስጥ ያድራል? 10  የዱር በሬ ትልም እንዲያወጣልህ ልትጠምደው ትችላለህ?ወይስ እየተከተለህ ሸለቆውን ያርሳል?* 11  በብርቱ ጉልበቱ ትታመናለህ?ደግሞስ ከባዱን ሥራህን እንዲሠራልህ ታደርጋለህ? 12  እህልህን እንዲሰበስብልህ፣በአውድማህም ላይ እንዲያከማችልህ በእሱ ትታመናለህ? 13  የሰጎን ክንፍ በደስታ ይርገበገባል፤ይሁንና የራዛ*+ ዓይነት ክንፍና ላባ አላት? 14  እንቁላሎቿን መሬት ላይ ትጥላለች፤በአፈርም ውስጥ ታሞቃቸዋለች። 15  እግር ሊሰብራቸው፣የዱር አውሬም ሊረግጣቸው እንደሚችል አታስብም። 16  ልጆቿ የራሷ ያልሆኑ ይመስል ትጨክንባቸዋለች፤+ድካሜ ሁሉ ከንቱ ይሆናል የሚል ስጋት አያድርባትም። 17  አምላክ ጥበብ ነስቷታልና፤*ማስተዋልንም አልሰጣትም። 18  ተነስታ ክንፎቿን በምታርገበግብበት ጊዜ ግን፣በፈረሱና በፈረሰኛው ላይ ትስቃለች። 19  ለፈረስ ጉልበት የምትሰጠው አንተ ነህ?+ አንገቱንስ የሚርገፈገፍ ጋማ ታለብሰዋለህ? 20  እንደ አንበጣ እንዲዘል ልታደርገው ትችላለህ? የፉርፉርታው ግርማ አስፈሪ ነው።+ 21  የሸለቆውን መሬት ይጎደፍራል፤ ደግሞም በኃይል ይዘላል፤+ወደ ውጊያ ይገሰግሳል።*+ 22  በፍርሃት ላይ ይስቃል፤ የሚያስፈራውም ነገር የለም።+ ሰይፍ አይቶም ወደኋላ አይልም። 23  ኮሮጆው በጎኑ ይንኳኳል፤ጭሬውና ጦሩ ያብረቀርቃል። 24  በደስታ እየተርገፈገፈ ወደ ፊት ይሸመጥጣል፤*የቀንደ መለከት ድምፅ ሲሰማ ያቅበጠብጠዋል።* 25  ቀንደ መለከቱ ሲነፋ ‘እሰይ!’ ይላል፤ ጦርነቱን ከሩቅ ያሸታል፤ደግሞም የጦር አዛዦችን ጩኸትና ቀረርቶውን ይሰማል።+ 26  ሲላ ክንፎቹን ወደ ደቡብ ዘርግቶወደ ላይ የሚወነጨፈው በአንተ ማስተዋል ነው? 27  ወይስ ንስር ወደ ላይ የሚመጥቀው፣+ጎጆውንም ከፍ ባለ ቦታ ላይ የሚሠራው+ አንተ አዘኸው ነው? 28  በገደል ላይ ያድራል፤በገደሉ አፋፍ ላይ በሚገኝ ዓለታማ ምሽግ ውስጥ* ይኖራል። 29  በዚያም ሆኖ የሚበላውን ነገር ይፈልጋል፤+ዓይኖቹም እጅግ ሩቅ ወደሆነ ቦታ ይመለከታሉ። 30  ጫጩቶቹም ደም ይጠጣሉ፤በድን ባለበት ስፍራም ሁሉ ይገኛል።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቅርንጫፍ የሚመስሉ ቀንዶች ያሉት አጥቢ እንስሳ፤ ከአጋዘን ጋር ይመሳሰላል።
ወይም “የሸለቆውን ጓል ይከሰክሳል።”
ባለ ረጃጅም እግር ትልቅ አሞራ።
ቃል በቃል “(ጥበብን) እንድትረሳ አድርጓታል።”
ቃል በቃል “የጦር መሣሪያን ለመገናኘት ይወጣል።”
ቃል በቃል “ምድርን (መሬትን) ይውጣል።”
“ጆሮውን ማመን ያቅተዋል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “በቋጥኝ ጥርስ ላይ።”