ኢዮብ 20:1-29

  • የሶፋር ሁለተኛ ዙር ንግግር (1-29)

    • ኢዮብ እንደዘለፈው ተሰማው (2, 3)

    • ኢዮብ ክፉ እንደሆነ የሚጠቁም ቃል ተናገረ (5)

    • ኢዮብ በኃጢአት እንደሚደሰት ተናገረ (12, 13)

20  ናአማታዊው ሶፋር+ እንዲህ ሲል መለሰ፦   “ስሜቴ ስለታወከ፣የሚረብሸኝ ሐሳብ መልስ እንድሰጥ ይገፋፋኛል።   እኔን የሚዘልፍ ወቀሳ ሰምቻለሁ፤ያለኝ ማስተዋል* መልስ እንድሰጥ ይገፋፋኛል።   ከድሮ ጀምሮ ይህን ታውቅ ነበር ማለት ነው፤ሰው* በምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እንዲህ ነበርና፤+   የክፉዎች እልልታ ለአጭር ጊዜ፣አምላክ የለሽ የሆነ* ሰው ደስታም ለቅጽበት ነው።+   ታላቅነቱ ወደ ሰማይ ከፍ ቢል፣ራሱም እስከ ደመናት ቢደርስ፣   እንደ ራሱ እዳሪ ለዘላለም ይጠፋል፤ያዩት የነበሩ ሰዎችም ‘የት ገባ?’ ይላሉ።   እንደ ሕልም በሮ ይጠፋል፤ እነሱም አያገኙትም፤እንደ ሌሊት ራእይ ይሰደዳል።   ቀድሞ ያየው ዓይን ዳግመኛ አያየውም፤የነበረበት ስፍራም ከእንግዲህ አይመለከተውም።+ 10  የገዛ ልጆቹ የድሆችን ሞገስ ለማግኘት ይሻሉ፤የገዛ እጆቹም ሀብቱን መልሰው ይሰጣሉ።+ 11  አጥንቶቹ በወጣትነት ጉልበት የተሞሉ ነበሩ፤ሆኖም ጉልበቱ ከእሱ ጋር አፈር ውስጥ ይተኛል። 12  መጥፎ የሆነ ነገር በአፉ ውስጥ ቢጣፍጥ፣ከምላሱም በታች ቢደብቀው፣ 13  እንዳያልቅበት ሳስቶ ቢያላምጠው፣በአፉም ውስጥ ቢያቆየው፣ 14  ምግቡ በውስጡ ይጎመዝዛል፤በውስጡም እንደ ጉበና* መርዝ* ይሆናል። 15  የዋጠውን ሀብት መልሶ ይተፋዋል፤አምላክ ከሆዱ ውስጥ ያወጣዋል። 16  የጉበናዎችን መርዝ ይጠባል፤የእፉኝት ጥርስ* ይገድለዋል። 17  የውኃ ፈሳሾችን፣የማርና የቅቤ ጅረቶችን ፈጽሞ አያይም። 18  ንብረቱን ሳይጠቀምበት ይመልሳል፤ነግዶ ባገኘው ሀብት አይደሰትም።+ 19  ድሆችን አድቅቋልና፤ ደግሞም ትቷቸዋል፤ያልገነባውን ቤት ቀምቷል። 20  ሆኖም በውስጡ ሰላም አይኖረውም፤ያካበተው ሀብት አያድነውም። 21  ሊበላው የሚችል የተረፈ ነገር አይኖርም፤ከዚህም የተነሳ ብልጽግናው ዘላቂ አይሆንም። 22  ሀብቱ ሲትረፈረፍ በጭንቀት ይዋጣል፤የመከራ ዓይነት ይፈራረቅበታል። 23  ሆዱ በሞላ ጊዜ፣አምላክ* የሚነድ ቁጣውን በእሱ ላይ በመላክ፣ወደ አንጀቱ እስኪገባ ያዘንብበታል። 24  ከብረት የጦር መሣሪያ ሲሸሽ፣ከመዳብ የተሠራ ቀስት ይወጋዋል። 25  ቀስት ከጀርባው፣የሚያብረቀርቅ መሣሪያ ከሐሞቱ መዝዞ ያወጣል፤በሽብርም ይዋጣል።+ 26  ውድ ሀብቱ ለድቅድቅ ጨለማ ይዳረጋል፤ማንም ያላርገበገበው እሳት እሱን ይበላዋል፤በድንኳኑ ውስጥ የቀረ ማንኛውም ሰው ጥፋት ይደርስበታል። 27  ሰማይ በደሉን ይገልጥበታል፤ምድር በእሱ ላይ ትነሳለች። 28  ጎርፍ ቤቱን ጠርጎ ይወስደዋል፤በአምላክ የቁጣ ቀን* የውኃ መጥለቅለቅ ይከሰታል። 29  ክፉ ሰው ከአምላክ የሚቀበለው ድርሻ፣አምላክም የወሰነለት ርስት ይህ ነው።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ማስተዋሌ ያስገኘው መንፈስ።”
ወይም “የሰው ልጅ፤ አዳም።”
ወይም “የከሃዲ።”
በእስያና በአፍሪካ የሚገኝ እጅግ መርዘኛ የሆነ እባብ፤ ኮብራ።
ወይም “ሐሞት።”
ቃል በቃል “ምላስ።”
ቃል በቃል “እሱ።”
ቃል በቃል “በእሱ የቁጣ ቀን።”