ኢዮብ 32:1-22

  • ወጣቱ ኤሊሁ በውይይቱ መሳተፍ ጀመረ (1-22)

    • በኢዮብና በኢዮብ ጓደኞች ላይ ተቆጣ (2, 3)

    • በአክብሮት ዝም ብሎ ቆየ (6, 7)

    • “ዕድሜ በራሱ ሰውን ጥበበኛ አያደርገውም” (9)

    • ኤሊሁ ለመናገር ተነሳሳ (18-20)

32  ኢዮብ ጻድቅ ነኝ የሚል ጽኑ እምነት ስለነበረው፣*+ እነዚህ ሦስት ሰዎች ለእሱ መልስ መስጠታቸውን አቆሙ።  ይሁን እንጂ ከራም ወገን የሆነው የቡዛዊው+ የባራክኤል ልጅ ኤሊሁ እጅግ ተቆጣ። ከአምላክ ይልቅ ራሱን* ጻድቅ ለማድረግ ስለሞከረ+ በኢዮብ ላይ ቁጣው ነደደ።  በተጨማሪም ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆች መልስ መስጠት ባለመቻላቸው፣ ይልቁንም አምላክን ክፉ በማድረጋቸው+ በእነሱም ላይ እጅግ ተቆጣ።  ኤሊሁ በዕድሜ ይበልጡት ስለነበር፣ ተናግረው እስኪጨርሱ ድረስ ለኢዮብ ምንም መልስ ሳይሰጥ ሲጠብቅ ቆየ።+  ኤሊሁ ሦስቱ ሰዎች መልስ መስጠት እንደተሳናቸው ባየ ጊዜ ቁጣው ነደደ።  በመሆኑም የቡዛዊው የባራክኤል ልጅ ኤሊሁ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፦ “እኔ በዕድሜ ትንሽ ነኝ፤*እናንተ ግን ትላልቆች ናችሁ።+ ለእናንተ ካለኝ አክብሮት የተነሳ ከመናገር ዝም አልኩ፤+ደግሞም የማውቀውን ለመናገር አልደፈርኩም።   እኔም ‘ዕድሜ ይናገር፤*ረጅም ዘመንም ጥበብን ያሳውቅ’ ብዬ አስቤ ነበር።   ሆኖም ለሰዎች ማስተዋል የሚሰጠው በውስጣቸው ያለው መንፈስ፣ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ እስትንፋስ ነው።+   ዕድሜ* በራሱ ሰውን ጥበበኛ አያደርገውም፤ትክክለኛውን ነገር የሚያስተውሉትም በዕድሜ የገፉ ሰዎች ብቻ አይደሉም።+ 10  ስለዚህ ‘እኔን ስማኝ፤እኔም የማውቀውን እነግርሃለሁ’ አልኩ። 11  እነሆ፣ እናንተ የተናገራችሁትን በትዕግሥት ሳዳምጥ ቆይቻለሁ፤የምትናገሩትን ነገር አውጥታችሁ አውርዳችሁ፣+ሐሳባችሁን በምትገልጹበት ጊዜ በትኩረት ስሰማ ነበር።+ 12  ልብ ብዬ አዳመጥኳችሁ፤ሆኖም አንዳችሁም ኢዮብ መሳሳቱን ማስረዳት፣*ወይም ላቀረበው የመከራከሪያ ሐሳብ መልስ መስጠት አልቻላችሁም። 13  ስለሆነም ‘እኛ ጥበብ አለን፤እሱ መሳሳቱን የሚነግረው አምላክ እንጂ ሰው አይደለም’ አትበሉ። 14  እሱ በእኔ ላይ የተናገረው ነገር የለም፤በመሆኑም እንደ እናንተ አልመልስለትም። 15  እነሱ ተሸብረዋል፤ መልስ መስጠትም ተስኗቸዋል፤የሚናገሩትም ጠፍቷቸዋል። 16  እኔ ጠበቅኳቸው፤ እነሱ ግን ንግግራቸውን መቀጠል አልቻሉም፤ከዚህ በላይ መልስ መስጠት አቅቷቸው ዝም ብለው ቆመዋል። 17  ስለዚህ እኔም መልስ እሰጣለሁ፤የማውቀውንም እናገራለሁ፤ 18  ብዙ የምናገረው ነገር አለኝና፤በውስጤ ያለው መንፈስ ገፋፍቶኛል። 19  ውስጤ መተንፈሻ እንዳጣ የወይን ጠጅ፣ሊፈነዳ እንደተቃረበ አዲስ አቁማዳ ሆኗል።+ 20  እፎይታ እንዳገኝ እስቲ ልናገር! አፌንም ከፍቼ መልስ እሰጣለሁ። 21  ለማንም ፈጽሞ አላዳላም፤+ማንንም ሰው አልሸነግልም፤* 22  ሰውን መሸንገል አላውቅበትምና፤እንደዛ ባደርግ ፈጣሪዬ ወዲያውኑ ባስወገደኝ ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በገዛ ዓይኑ ጻድቅ ስለነበር።”
ወይም “ነፍሱን።”
ቃል በቃል “ቀኖቼ ጥቂት ናቸው።”
ቃል በቃል “ቀኖች (ይናገሩ)።”
ወይም “ብዙ ቀን።”
ወይም “ኢዮብን መውቀስ።”
ወይም “ለማንም ሰው የማዕረግ ስም አልሰጥም።”