ምሳሌ 15:1-33

  • “የለዘበ መልስ ቁጣን ያበርዳል” (1)

  • “የይሖዋ ዓይኖች በሁሉም ቦታ ናቸው” (3)

  • ‘የቅኖች ጸሎት አምላክን ደስ ያሰኛል’ (8)

  • “መመካከር ከሌለ የታቀደው ነገር ሳይሳካ ይቀራል” (22)

  • መልስ ከመስጠትህ በፊት አሰላስል (28)

15  የለዘበ* መልስ ቁጣን ያበርዳል፤+ክፉ* ቃል ግን ቁጣን ያነሳሳል።+   የጥበበኞች ምላስ እውቀትን በሚገባ ይጠቀማል፤+የሞኞች አፍ ግን ሞኝነትን ይገልጣል።   የይሖዋ ዓይኖች በሁሉም ቦታ ናቸው፤ክፉዎችንም ሆነ ጥሩ ሰዎችን ይመለከታሉ።+   የረጋ አንደበት* የሕይወት ዛፍ ነው፤+ጠማማ ንግግር ግን ተስፋ ያስቆርጣል።*   ሞኝ የአባቱን ተግሣጽ ይንቃል፤+ብልህ ግን እርማትን ይቀበላል።+   በጻድቅ ሰው ቤት ብዙ ሀብት አለ፤የክፉ ሰው ምርት* ግን ችግር ያስከትልበታል።+   የጥበበኞች ከንፈር እውቀትን ታስፋፋለች፤+የሞኞች ልብ ግን እንዲህ አይደለም።+   ይሖዋ የክፉዎችን መሥዋዕት ይጸየፋል፤+የቅኖች ጸሎት ግን ደስ ያሰኘዋል።+   ይሖዋ የክፉውን መንገድ ይጸየፋል፤+ጽድቅን የሚከታተለውን ግን ይወደዋል።+ 10  ከመንገድ የሚወጣ ሰው፣ ተግሣጽ መጥፎ* ነገር ይመስለዋል፤+ወቀሳን የሚጠላ ሁሉ ግን ይሞታል።+ 11  መቃብርና* የጥፋት ቦታ* በይሖዋ ፊት ወለል ብለው ይታያሉ።+ የሰዎች ልብማ በፊቱ ምንኛ የተገለጠ ነው!+ 12  ፌዘኛ የሚያርመውን* ሰው አይወድም።+ ጥበበኞችን አያማክርም።+ 13  ደስተኛ ልብ ፊትን ያፈካል፤የልብ ሐዘን ግን መንፈስን ይደቁሳል።+ 14  አስተዋይ ልብ እውቀትን ይፈልጋል፤+የሞኞች አፍ ግን ቂልነትን ይመገባል።*+ 15  ጎስቋላ ሰው ዘመኑ ሁሉ አስከፊ ነው፤+ደስተኛ* ልብ ያለው ሰው ግን ሁልጊዜ ግብዣ ላይ ያለ ያህል ነው።+ 16  ከጭንቀት* ጋር ከሚገኝ ብዙ ሀብት ይልቅይሖዋን በመፍራት የሚገኝ ጥቂት ነገር ይሻላል።+ 17  ጥላቻ ባለበት የሰባ* ፍሪዳ ከመብላት ይልቅፍቅር ባለበት አትክልት መብላት ይሻላል።+ 18  ግልፍተኛ ሰው ጭቅጭቅ ይፈጥራል፤+ቶሎ የማይቆጣ ሰው ግን ጠብን ያበርዳል።+ 19  የሰነፍ መንገድ እንደ እሾህ አጥር ነው፤+የቅኖች መንገድ ግን እንደተስተካከለ አውራ ጎዳና ነው።+ 20  ጥበበኛ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤+ሞኝ ግን እናቱን ያቃልላል።+ 21  ማስተዋል* የጎደለው ሰው ሞኝነት ያስደስተዋል፤+ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰው ግን ቀጥተኛውን መንገድ ተከትሎ ይሄዳል።+ 22  መመካከር* ከሌለ የታቀደው ነገር ሳይሳካ ይቀራል፤በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል።+ 23  ሰው ትክክለኛውን መልስ በመስጠት* ሐሴት ያደርጋል፤+በትክክለኛው ጊዜ የተነገረ ቃልም ምንኛ መልካም ነው!+ 24  ጥልቅ ማስተዋል ያለው ሰው ወደ መቃብር* ከመውረድ ይድን ዘንድየሕይወት መንገድ ወደ ላይ ይመራዋል።+ 25  ይሖዋ የትዕቢተኞችን ቤት ያፈርሳል፤+የመበለቲቱን ወሰን ግን ያስከብራል።+ 26  ይሖዋ የክፉውን ሰው ሐሳብ ይጸየፋል፤+ያማረ ቃል ግን በፊቱ ንጹሕ ነው።+ 27  በማጭበርበር የተገኘ ትርፍ የሚያጋብስ ሰው በቤተሰቡ ላይ ችግር* ያመጣል፤+ጉቦን የሚጠላ ግን በሕይወት ይኖራል።+ 28  የጻድቅ ልብ፣ መልስ ከመስጠቱ በፊት ያሰላስላል፤*+የክፉዎች አፍ ግን መጥፎ ነገር ይዘከዝካል። 29  ይሖዋ ከክፉዎች እጅግ የራቀ ነው፤የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል።+ 30  ብሩህ ዓይን* ልብን ደስ ያሰኛል፤መልካም ዜናም አጥንትን ያበረታል።*+ 31  ሕይወት የሚያስገኝ ወቀሳን የሚሰማ፣በጥበበኛ ሰዎች መካከል ይኖራል።+ 32  ተግሣጽን ገሸሽ የሚያደርግ ሰው ሁሉ ሕይወቱን* ያቃልላል፤+ወቀሳን የሚሰማ ሁሉ ግን ማስተዋል* ያገኛል።+ 33  ይሖዋን መፍራት ጥበብን ያስተምራል፤+ትሕትናም ክብርን ትቀድማለች።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የሚያቆስል።”
ወይም “ደግነት የተሞላበት።”
ወይም “ፈዋሽ ምላስ።”
ቃል በቃል “መንፈስን ያደቃል።”
ወይም “ገቢ።”
ወይም “ከባድ።”
ወይም “ሲኦልና።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “አባዶን።”
ወይም “የሚወቅሰውን።”
ወይም “ይከታተላል።”
ወይም “ጥሩ።”
ወይም “ከሽብር።”
ቃል በቃል “በግርግም የተቀለበ።”
ቃል በቃል “ልብ።”
ወይም “ልብ ለልብ መነጋገር።”
ቃል በቃል “በአፉ መልስ።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ውርደት።”
ወይም “ምን ብሎ እንደሚመልስ በጥሞና ያስባል፤ ከመናገሩ በፊት ያስባል።”
ቃል በቃል “ያሰባል።”
ወይም “በፈገግታ የተሞላ ፊት።”
ወይም “ነፍሱን።”
ቃል በቃል “ልብ።”