ምሳሌ 14:1-35

  • “ልብ የራሱን ምሬት ያውቃል” (10)

  • ትክክል መስሎ የሚታይ መንገድ ወደ ሞት ሊመራ ይችላል (12)

  • “ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል” (15)

  • ‘የባለጸጋ ወዳጆች ብዙ ናቸው’ (20)

  • “የሰከነ ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል” (30)

14  ጥበበኛ ሴት ቤቷን ትገነባለች፤+ሞኝ ሴት ግን በገዛ እጇ ታፈርሰዋለች።   አካሄዱ ቅን የሆነ ሰው ይሖዋን ይፈራል፤መንገዱ መሠሪ* የሆነ ግን ይንቀዋል።   በሞኝ ሰው አፍ የትዕቢት በትር አለ፤የጥበበኞች ከንፈር ግን ትጠብቃቸዋለች።   ከብት በሌለበት ግርግሙ ንጹሕ ይሆናል፤የበሬ ጉልበት ግን ብዙ ምርት ያስገኛል።   ሐቀኛ ምሥክር አይዋሽም፤ሐሰተኛ ምሥክር ግን ባወራ ቁጥር ይዋሻል።+   ፌዘኛ ጥበብን ይፈልጋል፤ ሆኖም አያገኛትም፤አስተዋይ ሰው ግን እውቀትን በቀላሉ ያገኛል።+   ከሞኝ ሰው ራቅ፤ከከንፈሮቹ ምንም ዓይነት እውቀት አታገኝምና።+   ብልህ ሰው የሚሄድበትን መንገድ በጥበብ ያስተውላል፤ሞኞች ግን በቂልነታቸው ይታለላሉ።*+   ሞኞች በደል ፈጽመው* ያፌዛሉ፤+ቅኖች ግን እርቅ ለመፍጠር ፈቃደኞች ናቸው።* 10  ልብ የራሱን* ምሬት ያውቃል፤ደስታውንም ሌላ ሰው ሊጋራው አይችልም። 11  የክፉዎች ቤት ይወድማል፤+የቅኖች ድንኳን ግን ይበለጽጋል። 12  ለሰው ትክክለኛ መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤+በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ይመራል።+ 13  አንድ ሰው እየሳቀ እንኳ ልቡ ሊያዝን ይችላል፤ደስታም በሐዘን ሊቋጭ ይችላል። 14  በልቡ ጋጠወጥ የሆነ ሰው አካሄዱ የሚያስከትለውን መዘዝ ይቀበላል፤+ጥሩ ሰው ግን የሥራውን ውጤት ያገኛል።+ 15  ተላላ* ቃልን ሁሉ ያምናል፤ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል።+ 16  ጥበበኛ ሰው ጠንቃቃ ነው፤ ከክፉም ይርቃል፤ሞኝ ግን ደንታ ቢስ ነው፤* ደግሞም ከልክ በላይ በራሱ ይመካል። 17  ለቁጣ የሚቸኩል ሰው የሞኝነት ተግባር ይፈጽማል፤+በጥሞና የሚያስብ ሰው* አይወደድም። 18  ተላሎች* ሞኝነትን ይወርሳሉ፤ብልሆች ግን እውቀትን እንደ አክሊል ይጎናጸፋሉ።+ 19  መጥፎ ሰዎች በጥሩ ሰዎች ፊት፣ክፉዎችም በጻድቅ ደጃፍ ይሰግዳሉ። 20  ድሃ በባልንጀሮቹ ዘንድ እንኳ የተጠላ ነው፤+የባለጸጋ ወዳጆች ግን ብዙ ናቸው።+ 21  ባልንጀራውን የሚንቅ ኃጢአት ይሆንበታል፤ለችግረኞች የሚራራ ግን ደስተኛ ነው።+ 22  ተንኮል የሚሸርቡ ሰዎች መንገድ ይስቱ የለም? መልካም ነገር ለመሥራት የሚያስቡ ሰዎች ግን ታማኝ ፍቅርንና ታማኝነትን ያተርፋሉ።+ 23  በትጋት ያከናወኑት ነገር ሁሉ ጥቅም ያስገኛል፤እንዲሁ ማውራት ግን ችግር ላይ ይጥላል።+ 24  የጥበበኞች ዘውድ ሀብታቸው ነው፤የሞኞች ቂልነት ግን ለከፋ ሞኝነት ይዳርጋል።+ 25  እውነተኛ ምሥክር ሕይወትን* ይታደጋል፤አታላይ ግን ባወራ ቁጥር ይዋሻል። 26  ይሖዋን የሚፈራ ሁሉ በማንኛውም ነገር በእሱ ይታመናል፤+ልጆቹም መጠጊያ ያገኛሉ።+ 27  ይሖዋን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው፤ሰውን ከሞት ወጥመድ እንዲያመልጥ ይረዳዋል። 28  የሕዝብ ብዛት የንጉሥ ግርማ ነው፤+ተገዢዎች የሌሉት ገዢ ግን ይጠፋል። 29  ቶሎ የማይቆጣ ሰው ትልቅ ማስተዋል አለው፤+ትዕግሥት የሌለው ሰው ግን ሞኝነቱን ይገልጣል።+ 30  የሰከነ ልብ ለሰውነት ሕይወት* ይሰጣል፤ቅናት ግን አጥንትን ያነቅዛል።+ 31  ችግረኛን የሚያጭበረብር ፈጣሪውን ይሰድባል፤+ለድሃ የሚራራ ሁሉ ግን አምላክን ያከብራል።+ 32  ክፉ ሰው በገዛ ክፋቱ ይወድቃል፤ጻድቅ ግን ንጹሕ አቋሙ* መጠጊያ ያስገኝለታል።+ 33  ጥበብ በአስተዋይ ልብ ውስጥ በጸጥታ ታርፋለች፤+በሞኞች መካከል ግን ራሷን ትገልጣለች። 34  ጽድቅ አንድን ብሔር ከፍ ከፍ ታደርጋለች፤+ኃጢአት ግን ሕዝብን ታዋርዳለች። 35  ንጉሥ አስተውሎ በሚሠራ አገልጋይ ደስ ይሰኛል፤+አሳፋሪ ድርጊት በሚፈጽም አገልጋይ ላይ ግን ይቆጣል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ጠማማ።”
“ሞኞች ግን ሌሎችን ያታልላሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በበደል ካሳ።”
ወይም “በቅኖች መካከል ግን በጎ ፈቃድ አለ።”
ወይም “የነፍሱን።”
ወይም “ተሞክሮ የሌለው።”
ወይም “ይቆጣል።”
ወይም “የማመዛዘን ችሎታ ያለው ሰው።”
ወይም “ተሞክሮ የሌላቸው።”
ወይም “ነፍስን።”
ወይም “ጤና።”
ምሳሌ 2:7 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።