ምሳሌ 24:1-34

  • “በክፉ ሰዎች አትቅና” (1)

  • “ቤት በጥበብ ይገነባል” (3)

  • ጻድቅ ቢወድቅ እንኳ ይነሳል (16)

  • “እንዳደረገብኝ እንዲሁ አደርግበታለሁ” አትበል (29)

  • ማንቀላፋት ድህነት ያስከትላል (33, 34)

24  በክፉ ሰዎች አትቅና፤ከእነሱም ጋር ለመሆን አትጓጓ፤+   ልባቸው ዓመፅን ያውጠነጥናልና፤ከንፈራቸውም ተንኮልን ያወራል።   ቤት በጥበብ ይገነባል፤*+በማስተዋልም ይጸናል።   በእውቀት አማካኝነት ክፍሎቹበተለያዩ ውድ የሆኑና ያማሩ ነገሮች ተሞልተዋል።+   ጥበበኛ ሰው ኃያል ነው፤+ሰውም በእውቀት ኃይሉን ይጨምራል።   ጥበብ ያለበት አመራር ተቀብለህ ለውጊያ ትወጣለህ፤+በብዙ አማካሪዎችም ድል* ይገኛል።+   ለሞኝ ሰው እውነተኛ ጥበብ ሊገኝ የማይችል ነገር ነው፤+በከተማው በር ላይ አንዳች የሚናገረው ነገር የለውም።   መጥፎ ነገር ለማድረግ የሚያሴር ሁሉሴራ በመጠንሰስ የተካነ ተብሎ ይጠራል።+   በሞኝነት የሚጠነሰስ ሴራ* ኃጢአት ነው፤ሰዎችም ፌዘኛን ይጸየፋሉ።+ 10  በመከራ ቀን* ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነጉልበትህ እጅግ ይዳከማል። 11  ወደ ሞት እየተወሰዱ ያሉትን ታደግ፤ለእርድ እየተውተረተሩ የሚሄዱትንም አስጥል።+ 12  “እኛ ግን ስለዚህ ጉዳይ ምንም አናውቅም” ብትል፣ ልብን* የሚመረምረው እሱ ይህን አያስተውልም?+ አዎ፣ አንተን* የሚመለከተው አምላክ ያውቃል፤ለእያንዳንዱም ሰው እንደ ሥራው ይከፍለዋል።+ 13  ልጄ ሆይ፣ መልካም ስለሆነ ማር ብላ፤ከማር እንጀራ የሚገኝ ማር ጣፋጭ ጣዕም አለው። 14  በተመሳሳይም ጥበብ ለአንተ መልካም* እንደሆነ እወቅ።+ ጥበብን ብታገኝ የወደፊት ሕይወትህ የተሳካ ይሆናል፤ተስፋህም ከንቱ አይሆንም።+ 15  በጻድቁ ቤት ላይ በክፋት አትሸምቅ፤ማረፊያ ቦታውንም አታፍርስበት። 16  ጻድቅ ሰባት ጊዜ ቢወድቅ እንኳ መልሶ ይነሳልና፤+ክፉ ሰው ግን በሚደርስበት መከራ ይሰናከላል።+ 17  ጠላትህ ሲወድቅ ሐሴት አታድርግ፤ሲሰናከልም ልብህ ደስ አይበለው፤+ 18  አለዚያ ይሖዋ ይህን አይቶ ያዝናል፤ቁጣውንም ከእሱ* ይመልሳል።+ 19  መጥፎ በሆኑ ሰዎች አትበሳጭ፤በክፉዎች አትቅና፤ 20  መጥፎ ሰው ሁሉ ምንም ተስፋ የለውምና፤+የክፉዎች መብራት ይጠፋል።+ 21  ልጄ ሆይ፣ ይሖዋንና ንጉሥን ፍራ።+ ከተቃዋሚዎች* ጋር አትተባበር፤+ 22  ጥፋታቸው ድንገት ይመጣልና።+ ሁለቱም* በእነሱ ላይ የሚያመጡትን ጥፋት ማን ያውቃል?+ 23  እነዚህም አባባሎች የጥበበኞች ናቸው፦ በፍርድ ማዳላት ጥሩ አይደለም።+ 24  ክፉውን “አንተ ጻድቅ ነህ”+ የሚለውን ሰው ሁሉ ሕዝቦች ይረግሙታል፤ ብሔራትም ያወግዙታል። 25  እሱን የሚወቅሱት ግን መልካም ይሆንላቸዋል፤+በመልካም ነገሮችም ይባረካሉ።+ 26  ሰዎች በሐቀኝነት መልስ የሚሰጥን ሰው ከንፈር ይስማሉ።*+ 27  በደጅ ያለህን ሥራ አሰናዳ፤ በእርሻም ላይ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ አዘጋጅ፤ከዚያ በኋላ ቤትህን ሥራ።* 28  ምንም መሠረት ሳይኖርህ በባልንጀራህ ላይ አትመሥክር።+ በከንፈሮችህ ሌሎችን አታታል።+ 29  “እሱ እንዳደረገብኝ እንዲሁ አደርግበታለሁ፤እንደ ሥራው እከፍለዋለሁ”* አትበል።+ 30  በሰነፍ ሰው እርሻ፣+ማስተዋል* በጎደለው ሰው የወይን ቦታ አለፍኩ። 31  እርሻው አረም ወርሶት አየሁ፤መሬቱን ሳማ ሸፍኖት፣የድንጋዩም አጥር ፈራርሶ ነበር።+ 32  ይህን ተመልክቼ በጥሞና አሰብኩበት፤ካየሁትም ነገር ይህን ትምህርት አገኘሁ፦* 33  ቆይ ትንሽ ልተኛ፣ ቆይ ትንሽ ላንቀላፋ፣እጄንም አጣጥፌ እስቲ ትንሽ ጋደም ልበል ካልክ፣ 34  ድህነት እንደ ወንበዴ፣ችጋርም መሣሪያ እንደታጠቀ ሰው ይመጣብሃል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ቤተሰብ በጥበብ ይገነባል።”
ወይም “ስኬት፤ መዳን።”
ወይም “የሞኝ ሴራ።”
ወይም “በችግር ጊዜ።”
ወይም “ውስጣዊ ዓላማን።”
ወይም “ነፍስህን።”
ወይም “ለነፍስህ ጣፋጭ።”
ጠላትን ያመለክታል።
ወይም “ለውጥ ለማካሄድ ከተነሱ ሰዎች።”
ይሖዋንና ንጉሡን ያመለክታል።
“በቀጥታ መልስ መስጠት እንደ መሳም ይቆጠራል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ቤተሰብህን ገንባ።”
ወይም “አጸፋውን እመልሳለሁ።”
ቃል በቃል “ልብ።”
ቃል በቃል “ተግሣጽ ተቀበልኩ፦”