ምሳሌ 29:1-27

  • መረን የተለቀቀ ልጅ ለውርደት ይዳርጋል (15)

  • “ራእይ ከሌለ ሕዝብ እንዳሻው ይሆናል” (18)

  • “የሚቆጣ ሰው ጠብ ያስነሳል” (22)

  • ትሑት ሰው ክብር ይጎናጸፋል (23)

  • “ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው” (25)

29  ብዙ ጊዜ ተወቅሶ አንገቱን ያደነደነ* ሰው፣+ሊፈወስ በማይችል ሁኔታ በድንገት ይሰበራል።+   ጻድቃን ሲበዙ ሕዝብ ሐሴት ያደርጋል፤ክፉ ሰው ሲገዛ ግን ሕዝብ ይቃትታል።+   ጥበብን የሚወድ ሰው አባቱን ደስ ያሰኛል፤+ከዝሙት አዳሪዎች ጋር የሚወዳጅ ግን ሀብቱን ያባክናል።+   ንጉሥ ፍትሕ በማስፈን አገርን ያረጋጋል፤+ጉቦ የሚፈልግ ሰው ግን ያወድማታል።   ባልንጀራውን የሚሸነግል ሰው፣ለእግሩ ወጥመድ ይዘረጋበታል።+   መጥፎ ሰው በደሉ ወጥመድ ይሆንበታል፤+ጻድቅ ግን እልል ይላል፤ ሐሴትም ያደርጋል።+   ጻድቅ ለድሆች መብት ይቆረቆራል፤+ክፉ ሰው ግን ለእንዲህ ዓይነት ጉዳይ ደንታ የለውም።+   ጉራ የሚነዙ ሰዎች ከተማን ያቃጥላሉ፤+ጥበበኞች ግን ቁጣን ያበርዳሉ።+   ጥበበኛ ሰው ከሞኝ ጋር ቢሟገት፣ሁከትና ፌዝ ይነግሣል፤ ደስታ ግን አይኖርም።+ 10  ደም የተጠሙ ሰዎች ንጹሕ የሆነን* ሰው ሁሉ ይጠላሉ፤+ቅን የሆነውን ሰው ሕይወት* ለማጥፋት ይሻሉ።* 11  ሞኝ ስሜቱን* ሁሉ እንዳሻው ይገልጻል፤+ጥበበኛ ግን ስሜቱን ይቆጣጠራል።+ 12  ገዢ የሐሰት ወሬ የሚሰማ ከሆነ፣አገልጋዮቹ ሁሉ ክፉዎች ይሆናሉ።+ 13  ድሃንና ጨቋኝን የሚያመሳስላቸው* ነገር አለ፦ ይሖዋ ለሁለቱም የዓይን ብርሃን ይሰጣል።* 14  ንጉሥ ለድሆች በትክክል ሲፈርድ፣+ዙፋኑ ምንጊዜም ጸንቶ ይኖራል።+ 15  በትርና* ወቀሳ ጥበብ ያስገኛሉ፤+መረን የተለቀቀ ልጅ ግን እናቱን ያሳፍራል። 16  ክፉዎች ሲበዙ ክፋት ይበዛል፤ጻድቃን ግን የእነሱን ውድቀት ያያሉ።+ 17  ልጅህን ገሥጸው፤ ሰላም ይሰጥሃል፤ደግሞም እጅግ ደስ ያሰኝሃል።*+ 18  ራእይ* ከሌለ ሕዝብ እንዳሻው ይሆናል፤+ሕግን የሚጠብቁ ግን ደስተኞች ናቸው።+ 19  አገልጋይ በቃል ብቻ ለመታረም ፈቃደኛ አይሆንም፤የሚነገረውን ነገር ቢረዳውም እንኳ እሺ ብሎ አይታዘዝምና።+ 20  ለመናገር የሚቸኩል ሰው አይተህ ታውቃለህ?+ ከእሱ ይልቅ ሞኝ የተሻለ ተስፋ አለው።+ 21  አገልጋይ ከልጅነቱ ጀምሮ ከተሞላቀቀ፣የኋላ ኋላ ምስጋና ቢስ ይሆናል። 22  በቀላሉ የሚቆጣ ሰው ጠብ ያስነሳል፤+ግልፍተኛ የሆነም ብዙ በደል ይፈጽማል።+ 23  ሰውን ትዕቢቱ ያዋርደዋል፤+ትሑት መንፈስ ያለው ግን ክብር ይጎናጸፋል።+ 24  የሌባ ግብረ አበር ራሱን* ይጠላል። እንዲመሠክር የቀረበለትን ጥሪ* ቢሰማም ምንም አይናገርም።+ 25  ሰውን መፍራት* ወጥመድ ነው፤+በይሖዋ የሚታመን ግን ጥበቃ ያገኛል።+ 26  ብዙዎች ከገዢ ጋር ተገናኝተው መነጋገር* ይሻሉ፤ሰው ግን ፍትሕ የሚያገኘው ከይሖዋ ነው።+ 27  ጻድቅ ፍትሐዊ ያልሆነን ሰው ይጸየፋል፤+ክፉ ሰው ግን በቀና መንገድ የሚሄደውን ይጸየፋል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ግትር የሆነ።”
ወይም “ነቀፋ የሌለበትን።”
ወይም “ነፍስ።”
“ቅን የሆነ ሰው ግን ሕይወቱን ለመጠበቅ ይሻል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “መንፈሱን።”
ቃል በቃል “የሚያገናኛቸው።”
ሕይወት እንደሚሰጣቸው ያመለክታል።
ወይም “ተግሣጽና፤ ቅጣትና።”
ወይም “ነፍስህን እጅግ ደስ ያሰኛታል።”
ወይም “ትንቢታዊ ራእይ።”
ወይም “የገዛ ነፍሱን።”
ወይም “እርግማን የሚያስከትለውን መሐላ።”
ወይም “በሰው ፊት መንቀጥቀጥ።”
“የገዢን ሞገስ ማግኘት” ማለትም ሊሆን ይችላል። ቃል በቃል “የገዢን ፊት።”