የማርቆስ ወንጌል 1:1-45

  • አጥማቂው ዮሐንስ ሰበከ (1-8)

  • ኢየሱስ ተጠመቀ (9-11)

  • ኢየሱስ በሰይጣን ተፈተነ (12, 13)

  • ኢየሱስ በገሊላ መስበክ ጀመረ (14, 15)

  • የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ተጠሩ (16-20)

  • ኢየሱስ ርኩሱን መንፈስ አስወጣ (21-28)

  • ኢየሱስ በቅፍርናሆም ብዙ ሰዎችን ፈወሰ (29-34)

  • ገለል ወዳለ ስፍራ ሄዶ ጸለየ (35-39)

  • በሥጋ ደዌ ተይዞ የነበረ ሰው ተፈወሰ (40-45)

1  የአምላክ ልጅ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጸው ምሥራች የሚጀምረው እንደሚከተለው ነው፦  ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “(እነሆ፣ መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ፤ እሱም መንገድህን ያዘጋጃል።)*+  አንድ ሰው በምድረ በዳ ‘የይሖዋን* መንገድ አዘጋጁ፤ ጎዳናዎቹንም አቅኑ’ በማለት ይጮኻል።”+  አጥማቂው ዮሐንስ ለኃጢአት ይቅርታ፣ የንስሐ ምልክት የሆነውን ጥምቀት በምድረ በዳ እየሰበከ ነበር።+  መላው የይሁዳ ምድር እንዲሁም የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች በሙሉ ወደ እሱ ይመጡ ነበር፤ ደግሞም ኃጢአታቸውን በግልጽ እየተናዘዙ ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በእሱ ይጠመቁ* ነበር።+  ዮሐንስ የግመል ፀጉር ይለብስ፣ ወገቡም ላይ የቆዳ ቀበቶ ይታጠቅ+ የነበረ ሲሆን አንበጣና የዱር ማር ይበላ ነበር።+  እንዲህ እያለም ይሰብክ ነበር፦ “ከእኔ በኋላ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እኔ ጎንበስ ብዬ የጫማውን ማሰሪያ እንኳ ለመፍታት አልበቃም።+  እኔ በውኃ አጠመቅኳችሁ፤ እሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል።”+  በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት መጥቶ ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በዮሐንስ ተጠመቀ።+ 10  ወዲያው ከውኃው እንደወጣ ሰማያት ተከፍተው መንፈስ እንደ ርግብ በእሱ ላይ ሲወርድ አየ።+ 11  ከዚያም “አንተ የምወድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ።+ 12  ወዲያውም መንፈስ ወደ ምድረ በዳ እንዲሄድ ገፋፋው። 13  በምድረ በዳም 40 ቀን ቆየ። በዚያ ሳለ ሰይጣን ፈተነው፤+ ከአራዊትም ጋር ነበረ። መላእክትም ያገለግሉት ነበር።+ 14  ዮሐንስ ከታሰረ በኋላ ኢየሱስ የአምላክን ምሥራች እየሰበከ+ ወደ ገሊላ ሄደ።+ 15  “የተወሰነው ጊዜ ደርሷል፤ የአምላክ መንግሥት ቀርቧል። ንስሐ ግቡ፤+ በምሥራቹም እመኑ” ይል ነበር። 16  በገሊላ ባሕር* አጠገብ እየሄደ ሳለ ዓሣ አጥማጆች የነበሩት+ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ+ መረቦቻቸውን ወደ ባሕሩ ሲጥሉ አየ።+ 17  ኢየሱስም “ኑ ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው።+ 18  እነሱም ወዲያውኑ መረቦቻቸውን ትተው ተከተሉት።+ 19  ትንሽ እልፍ እንዳለ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን ጀልባቸው ላይ ሆነው መረቦቻቸውን ሲጠግኑ+ አያቸውና 20  ወዲያውኑ ጠራቸው። እነሱም አባታቸውን ዘብዴዎስን ከቅጥር ሠራተኞቹ ጋር ጀልባው ላይ ትተው ተከተሉት። 21  ከዚያም ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ። የሰንበት ቀን እንደደረሰም ወደ ምኩራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ።+ 22  እንደ ጸሐፍት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ስለነበረ ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ።+ 23  በዚሁ ጊዜ በምኩራባቸው ውስጥ የነበረ፣ ርኩስ መንፈስ የያዘው አንድ ሰው በኃይል ጮኾ እንዲህ አለ፦ 24  “የናዝሬቱ ኢየሱስ፣ እኛ ከአንተ ጋር ምን ጉዳይ አለን?+ የመጣኸው ልታጠፋን ነው? ማን እንደሆንክ በሚገባ አውቃለሁ፤ አንተ የአምላክ ቅዱስ አገልጋይ ነህ!”+ 25  ሆኖም ኢየሱስ “ዝም በል፤ ከእሱም ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። 26  ርኩሱም መንፈስ ሰውየውን ጥሎ ካንፈራገጠው በኋላ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእሱ ወጣ። 27  ሕዝቡ ሁሉ እጅግ በመገረም እርስ በርሳቸው “ይህ ምንድን ነው? ትምህርቱ ለየት ያለ ነው! ርኩሳን መናፍስትን እንኳ ሳይቀር በሥልጣን ያዛል፤ እነሱም ይታዘዙለታል” ተባባሉ። 28  ወዲያውኑም በመላው የገሊላ ግዛት በየአቅጣጫው ስለ እሱ በስፋት ተወራ። 29  በዚህ ጊዜ ከምኩራብ ወጥተው ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና እንድርያስ ቤት ሄዱ።+ 30  የስምዖን አማት+ ትኩሳት ይዟት ተኝታ ነበር፤ ስለ እሷም ወዲያው ለኢየሱስ ነገሩት። 31  እሱም ወደተኛችበት በመሄድ እጇን ይዞ አስነሳት። በዚህ ጊዜ ትኩሳቱ ለቀቃትና ታገለግላቸው ጀመር። 32  ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ፣ ምሽት ላይ ሰዎች የታመሙትንና በአጋንንት የተያዙትን ሁሉ ወደ እሱ ያመጡ ጀመር፤+ 33  የከተማዋም ሰው ሁሉ በደጅ ተሰብስቦ ነበር። 34  ኢየሱስም በተለያየ በሽታ የተያዙ በርካታ ሰዎችን ፈወሰ፤+ ብዙ አጋንንትንም አወጣ። ሆኖም አጋንንቱ ክርስቶስ መሆኑን አውቀው ስለነበር* እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም። 35  ኢየሱስ በማለዳ ገና ጎህ ሳይቀድ ተነስቶ ከቤት ወጣና ገለል ወዳለ ስፍራ ሄደ፤ እዚያም መጸለይ ጀመረ።+ 36  ይሁን እንጂ ስምዖንና ከእሱ ጋር የነበሩት አጥብቀው ፈለጉት፤ 37  ባገኙትም ጊዜ “ሰው ሁሉ እየፈለገህ ነው” አሉት። 38  እሱ ግን “በዚያም እንድሰብክ በአቅራቢያ ወዳሉት ከተሞች እንሂድ፤ የመጣሁት ለዚሁ ነውና” አላቸው።+ 39  እንዳለውም በምኩራቦቻቸው እየሰበከና አጋንንትን እያወጣ በመላዋ ገሊላ ተዘዋወረ።+ 40  በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰውም ወደ እሱ ቀርቦ “ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት ተንበርክኮ ተማጸነው።+ 41  በዚህ ጊዜ በጣም አዘነለትና እጁን ዘርግቶ ዳሰሰው፤ ከዚያም “እፈልጋለሁ! ንጻ” አለው።+ 42  ወዲያውኑ የሥጋ ደዌው ለቀቀውና ነጻ። 43  ከዚያም ኢየሱስ ሰውየውን በጥብቅ አስጠንቅቆ ቶሎ አሰናበተው፤ 44  እንዲህም አለው፦ “ለማንም አንዳች ነገር እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ሙሴ ያዘዛቸውንም ነገሮች አቅርብ፤+ ካህናቱም ማስረጃውን ይመለከታሉ።”+ 45  ሰውየው ግን ከሄደ በኋላ የሆነውን ነገር በሰፊው አወራ፤ ወሬውንም በየቦታው አሰራጨ፤ ስለሆነም ኢየሱስ ከዚህ በኋላ በግልጽ ወደ ከተማ መግባት ባለመቻሉ ከከተማ ውጭ ገለል ባሉ ቦታዎች ይኖር ጀመር። ይሁንና ሰዎች ከየአቅጣጫው ወደ እሱ መምጣታቸውን ቀጠሉ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

እዚህ ላይ የተጠቀሰው ሐሳብ የተወሰደው ከሚልክያስ 3:1 ነው።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ይነከሩ፤ ይጠልቁ።”
ማቴ 4:18 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
“የእሱን ማንነት አውቀው ስለነበር” ማለትም ሊሆን ይችላል።