የማርቆስ ወንጌል 2:1-28

  • ኢየሱስ አንድ ሽባ ፈወሰ (1-12)

  • ኢየሱስ ሌዊን ጠራው (13-17)

  • ጾምን በተመለከተ የቀረበ ጥያቄ (18-22)

  • ኢየሱስ ‘የሰንበት ጌታ ነው’ (23-28)

2  ይሁን እንጂ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ተመልሶ መጣ፤ ደግሞም ቤት ውስጥ እንዳለ ተወራ።+ 2  በመሆኑም ቤቱ ሞልቶ ደጅ ላይ እንኳ ቦታ እስኪታጣ ድረስ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ እሱም የአምላክን ቃል ይነግራቸው ጀመር።+ 3  ሰዎችም አንድ ሽባ በአራት ሰዎች አሸክመው ወደ እሱ አመጡ።+ 4  ሆኖም ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ሽባውን ወደ ኢየሱስ ማቅረብ ስላልቻሉ ከኢየሱስ በላይ ያለውን ጣሪያ ከነደሉ በኋላ ሽባው የተኛበትን ቃሬዛ ወደ ታች አወረዱት። 5  ኢየሱስም እምነታቸውን በማየት+ ሽባውን “ልጄ ሆይ፣ ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል” አለው።+ 6  በዚያ ተቀምጠው የነበሩ አንዳንድ ጸሐፍት ግን እንዲህ ሲሉ በልባቸው አሰቡ፦+ 7  “ይህ ሰው እንዲህ ብሎ የሚናገረው ለምንድን ነው? አምላክን እየተዳፈረ እኮ ነው። ከአንዱ ከአምላክ በቀር ኃጢአትን ማን ይቅር ሊል ይችላል?”+ 8  ሆኖም ኢየሱስ በልባቸው ይህን እያሰቡ እንዳሉ ወዲያው በመንፈሱ ተረድቶ “በልባችሁ እንዲህ እያላችሁ የምታስቡት ለምንድን ነው?+ 9  ሽባውን ‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሏል’ ከማለትና ‘ተነሳና ቃሬዛህን ተሸክመህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል? 10  ይሁንና የሰው ልጅ+ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ . . .”+ ካለ በኋላ ሽባውን እንዲህ አለው፦ 11  “ተነስ፣ ቃሬዛህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ።” 12  በዚህ ጊዜ ሽባው ብድግ ብሎ ወዲያው ቃሬዛውን በማንሳት በሁሉ ፊት እየተራመደ ወጣ። ይህን ሲያዩ ሁሉም እጅግ ተደነቁ፤ ደግሞም “እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይተን አናውቅም”+ በማለት አምላክን አከበሩ። 13  ኢየሱስ እንደገና ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሄደ፤ ሕዝቡም ወደ እሱ ጎረፈ፤ እሱም ያስተምራቸው ጀመር። 14  በመንገድ እያለፈ ሳለም የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን በቀረጥ መሰብሰቢያው ቦታ ተቀምጦ አየውና “ተከታዬ ሁን” አለው። በዚህ ጊዜ ተነስቶ ተከተለው።+ 15  በኋላም በሌዊ ቤት ተቀምጦ እየበላ ነበር፤ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኃጢአተኞችም ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እየበሉ ነበር። ከእነሱም መካከል ብዙዎቹ እሱን መከተል ጀምረው ነበር።+ 16  ሆኖም ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ ጸሐፍት ከኃጢአተኞችና ከቀረጥ ሰብሳቢዎች ጋር ሲበላ ባዩ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “እንዴት ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኃጢአተኞች ጋር ይበላል?” አሏቸው። 17  ኢየሱስ ይህን ሲሰማ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም። እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ልጠራ ነው” አላቸው።+ 18  የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን የመጾም ልማድ ነበራቸው። ስለዚህም ወደ እሱ መጥተው “የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ዘወትር ሲጾሙ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጾሙት ለምንድን ነው?” አሉት።+ 19  ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሙሽራው+ ከእነሱ ጋር እያለ ጓደኞቹ የሚጾሙበት ምን ምክንያት አለ? ሙሽራው አብሯቸው እስካለ ድረስ ሊጾሙ አይችሉም። 20  ሆኖም ሙሽራው ከእነሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤+ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ። 21  በአሮጌ ልብስ ላይ ውኃ ያልነካው አዲስ ጨርቅ የሚጥፍ ሰው የለም። እንዲህ ቢያደርግ ግን አዲሱ ጨርቅ ሲሸበሸብ አሮጌውን ስለሚስበው ቀዳዳው የባሰ ይሰፋል።+ 22  እንዲሁም ባረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያስቀምጥ ሰው የለም። እንዲህ ቢያደርግ ግን የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁ ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ይሁንና አዲስ የወይን ጠጅ የሚቀመጠው በአዲስ አቁማዳ ነው።” 23  በሰንበት ቀን በእህል እርሻ መካከል እያለፈ ሳለ አብረውት ይሄዱ የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር።+ 24  በመሆኑም ፈሪሳውያን “ተመልከት! በሰንበት ቀን በሕግ የተከለከለ ነገር የሚያደርጉት ለምንድን ነው?” አሉት። 25  እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ዳዊት የሚበላው ባጣ ጊዜ እንዲሁም እሱና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ያደረገውን ነገር ፈጽሞ አላነበባችሁም?+ 26  ሊቀ ካህናት ስለሆነው ስለ አብያታር+ በሚናገረው ታሪክ ላይ ዳዊት ወደ አምላክ ቤት ገብቶ ከካህናት በቀር ማንም እንዲበላ ያልተፈቀደውን በአምላክ ፊት የቀረበ ኅብስት+ እንደበላና ከእሱ ጋር ለነበሩትም እንደሰጣቸው አላነበባችሁም?” 27  ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ሰንበት ለሰው ተሰጠ እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም።+ 28  በመሆኑም የሰው ልጅ የሰንበትም እንኳ ጌታ ነው።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች