የማርቆስ ወንጌል 13:1-37

  • የሥርዓቱ መደምደሚያ (1-37)

    • ጦርነት፣ የምድር ነውጥ፣ የምግብ እጥረት (8)

    • ምሥራቹ ይሰበካል (10)

    • ታላቅ መከራ (19)

    • የሰው ልጅ መምጣት (26)

    • የበለስ ዛፍ ምሳሌ (28-31)

    • “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ” (32-37)

13  ከቤተ መቅደስ እየወጣ ሳለ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ “መምህር፣ እንዴት ያሉ ግሩም ድንጋዮችና ሕንጻዎች እንደሆኑ ተመልከት!” አለው።+ 2  ኢየሱስ ግን “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህ? ይህ ሁሉ ሳይፈርስ እንዲህ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ ከቶ አይኖርም” አለው።+ 3  በቤተ መቅደሱ ትይዩ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ ብቻቸውን ሆነው እንዲህ በማለት ጠየቁት፦ 4  “እስቲ ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የእነዚህ ነገሮች ሁሉ መደምደሚያ መቅረቡን የሚያሳየው ምልክትስ ምንድን ነው?”+ 5  ኢየሱስም እንዲህ ይላቸው ጀመር፦ “ማንም እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ።+ 6  ብዙዎች ‘እኔ እሱ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ። 7  ከዚህም ሌላ ጦርነትና የጦርነት ወሬ ስትሰሙ አትደናገጡ፤ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸው የግድ ነው፤ ሆኖም ፍጻሜው ገና ነው።+ 8  “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤+ በተለያየ ስፍራ የምድር ነውጥ ይከሰታል፤ በተጨማሪም የምግብ እጥረት ይኖራል።+ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።+ 9  “እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ሰዎች ለፍርድ ሸንጎዎች አሳልፈው ይሰጧችኋል፤+ በምኩራብም ትገረፋላችሁ፤+ በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ያቀርቧችኋል፤ በዚያ ጊዜ ለእነሱ መመሥከር ትችላላችሁ።+ 10  አስቀድሞም ምሥራቹ ለብሔራት ሁሉ መሰበክ አለበት።+ 11  አሳልፈው ለመስጠት በሚወስዷችሁ ጊዜም ምን እንላለን በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።+ 12  በተጨማሪም ወንድም ወንድሙን፣ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሳሉ፤ ደግሞም ያስገድሏቸዋል።+ 13  በስሜ የተነሳም ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል።+ እስከ መጨረሻው የጸና+ ግን* ይድናል።+ 14  “ይሁንና ጥፋት የሚያመጣው ‘ርኩስ ነገር’+ በማይገባው ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል፤ በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ።+ 15  በጣሪያ* ላይ ያለ ሰው አይውረድ፤ አንዳችም ነገር ለመውሰድ ወደ ቤቱ አይግባ፤ 16  በእርሻም ያለ መደረቢያውን ለመውሰድ ወደ ኋላ አይመለስ። 17  በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው!+ 18  ይህ በክረምት እንዳይሆን ዘወትር ጸልዩ፤ 19  ምክንያቱም በእነዚያ ቀናት ከአምላክ የፍጥረት ሥራ መጀመሪያ አንስቶ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን+ መከራ+ ይከሰታል። 20  እንዲያውም ይሖዋ* ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ ሥጋ ሁሉ ባልዳነ ነበር። ሆኖም እሱ ለመረጣቸው ምርጦች ሲል ቀኖቹን አሳጥሯል።+ 21  “በዚያን ጊዜም ማንም ‘እነሆ፣ ክርስቶስ ይኸውላችሁ’ ወይም ‘እነሆ፣ ያውላችሁ’ ቢላችሁ አትመኑ።+ 22  ምክንያቱም ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፤+ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ምልክቶችና አስደናቂ ነገሮች ያደርጋሉ። 23  ስለዚህ ተጠንቀቁ።+ ሁሉን ነገር አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ። 24  “ሆኖም በእነዚያ ቀናት፣ ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤+ 25  ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ በሰማያት ያሉ ኃይላትም ይናወጣሉ። 26  ከዚያም የሰው ልጅ+ በታላቅ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።+ 27  እሱም መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፣ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ ለእሱ የተመረጡትን ይሰበስባል።+ 28  “እንግዲያው ይህን ምሳሌ ከበለስ ዛፍ ተማሩ፦ ቅርንጫፎቿ ሲለመልሙና ቅጠሎቿ ሲያቆጠቁጡ በጋ* እንደቀረበ ታውቃላችሁ።+ 29  በተመሳሳይ እናንተም እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ ስታዩ የሰው ልጅ ደጃፍ ላይ እንደደረሰ እርግጠኞች ሁኑ።+ 30  እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም።+ 31  ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤+ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም።+ 32  “ስለዚያ ቀን ወይም ሰዓት ከአብ በቀር በሰማይ ያሉ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም።+ 33  ስለዚህ የተወሰነው ጊዜ መቼ እንደሆነ ስለማታውቁ+ ምንጊዜም በንቃት ተከታተሉ፤ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።+ 34  ይህም ለባሪያዎቹ ሥልጣን ከሰጠና ለእያንዳንዱ የሥራ ድርሻውን ከመደበ በኋላ በር ጠባቂውን ነቅቶ እንዲጠብቅ በማዘዝ+ ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደሄደ ሰው ነው።+ 35  ስለዚህ የቤቱ ጌታ፣ በምሽት* ይሁን በእኩለ ሌሊት* ወይም ዶሮ ሲጮኽ* ይሁን ከመንጋቱ* በፊት፣ መቼ እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ፤+ 36  አለዚያ ድንገት ሲመጣ ተኝታችሁ ያገኛችኋል።+ 37  ይሁንና ለእናንተ የምነግራችሁን ለሁሉም እናገራለሁ፤ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

^ ወይም “የሚጸና ግን።”
^ ማቴ 24:17 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
^ ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
^ በጳለስጢና ምድር ዕፀዋት የሚለመልሙት በበጋ ነው።
^ “ምሽት።” ግሪካውያንና ሮማውያን የሌሊቱን ጊዜ በሚከፋፍሉበት መሠረት የመጀመሪያው ክፍለ ሌሊት ሲሆን ይህም ፀሐይ ከጠለቀችበት ጊዜ አንስቶ እስከ 3 ሰዓት ገደማ ድረስ ነው።
^ “እኩለ ሌሊት።” ሁለተኛው ክፍለ ሌሊት ሲሆን ይህም ከምሽቱ 3 ሰዓት ገደማ አንስቶ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ነው።
^ “ዶሮ ሲጮኽ።” ሦስተኛው ክፍለ ሌሊት ሲሆን ይህም ከእኩለ ሌሊት እስከ ሌሊቱ 9 ሰዓት ገደማ ድረስ ነው።
^ “ንጋት።” አራተኛው ክፍለ ሌሊት ሲሆን ይህም ከሌሊቱ 9 ሰዓት ገደማ አንስቶ ፀሐይ እስከምትወጣበት ጊዜ ድረስ ነው።