በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

መጽሐፍ ቅዱስ ሊጠቅመኝ የሚችለው እንዴት ነው?—ክፍል 3፦ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የተሟላ ጥቅም ማግኘት

መጽሐፍ ቅዱስ ሊጠቅመኝ የሚችለው እንዴት ነው?—ክፍል 3፦ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የተሟላ ጥቅም ማግኘት

 መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ገጽ ያለው ትልቅ መጽሐፍ እንደሆነ ታውቃለህ። ሆኖም ይህ ተስፋ እንዲያስቆርጥህ አትፍቀድ! ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን ከድግስ ቡፌ ጋር ልታመሳስለው ትችላለህ። የቀረበውን ነገር ሁሉ ልትበላ አትችልም። ሆኖም የምትፈልገውን ምግብ መርጠህ እስክትጠግብ ድረስ መብላት ትችላለህ።

 ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ የተሟላ ጥቅም ማግኘት ከፈለግክ ሙሉ ትኩረትህን በምታነበው ነገር ላይ ማሳረፍ ይኖርብሃል። ከታች የቀረቡት ሐሳቦች እንዲህ እንድታደርግ ይረዱሃል።

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 በምታነበው ነገር ላይ ሙሉ ትኩረትህን ማሳረፍ ያለብህ ለምንድን ነው?

 ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ የምታውለው ጥረት በጨመረ መጠን ከንባብህ የምታገኘው ጥቅምም ይጨምራል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድን የሻይ ከረጢት ትኩስ ውኃ ውስጥ በችኮላ ነከር አድርገህ ካወጣኸው የሻዩን ጣዕም በተወሰነ መጠን ልታገኝ ትችላለህ። ውኃው ውስጥ ነክረህ ካቆየኸው ግን ጣዕሙ ይበልጥ ይጨምራል።

 ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በችኮላ ከማንበብ ይልቅ ጊዜ ወስደህ አእምሮህና ልብህ በትምህርቱ ላይ እንዲያተኩር አድርግ። የመዝሙር 119 ጸሐፊም ያደረገው ይህንኑ ነው። ስለ አምላክ ሕግ ሲናገር “ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ” ብሏል።—መዝሙር 119:97

 እርግጥ ይህ ሲባል ቃል በቃል ቀኑን ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስን እያነበብክና እያሰላሰልክ መዋል አለብህ ማለት አይደለም። ታዲያ ነጥቡ ምንድን ነው? መዝሙራዊው ስለ አምላክ ቃል ለማሰብ ጊዜ መድቧል። እንዲህ ማድረጉ ደግሞ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ረድቶታል።—መዝሙር 119:98-100

 “እናቴ በአንድ ወቅት እንዲህ ብላኝ ነበር፦ ‘በሳምንት ውስጥ ሰባት ቀናት አሉ፤ በእነዚህ ቀናት ውስጥ ለራስሽ ብዙ ነገር ታደርጊያለሽ። ታዲያ ለይሖዋ የተወሰነ ጊዜ ብትሰጪው ምክንያታዊ አይመስልሽም?’”—ሜላኒ

 ጊዜ ወስደህ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ማሰብህ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ይረዳሃል፤ ለምሳሌ ጓደኛ ስትመርጥ ወይም መጥፎ ነገር እንድታደርግ ስትፈተን የተሻለ ውሳኔ ማድረግ ትችላለህ።

 ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

  •   ዕቅድ አውጣ። ጁሊያ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስን የምታነቡበት ፕሮግራም አውጡ። ምን እንደምታነብቡ፣ መቼ እንደምታነብቡና የት እንደምታነብቡ ወስኑ።”

  •   አካባቢህን ምቹ አድርግ። ጂያና የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ጸጥ ያለ ቦታ ፈልጉ። በተጨማሪም የቤተሰባችሁ አባላት እንዳይረብሿችሁ መጽሐፍ ቅዱስን የምታነቡበትን ሰዓት ንገሯቸው።”

     ለማንበብ የምትጠቀመው የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ከሆነ ምንም ዓይነት መልእክት እንዳይመጣልህ አድርግ። ምናልባትም የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም ትችል ይሆናል። እንዲያውም አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከወረቀት ላይ ማንበብህ ሐሳቡን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ሊያግዝህ ይችላል። በአንጻሩ ግን ከስክሪን ላይ ስታነብ ትኩረትህን መሰብሰብ ሊከብድህ ይችላል።

     “ከስክሪን ላይ ሳነብ ትኩረቴ ይከፋፈላል። መልእክት ሊመጣልኝ፣ ባትሪዬ ሊያልቅ ወይም ኢንተርኔት ሊጠፋ ይችላል። የማነበው ከመጽሐፍ ላይ ከሆነ ግን የሚያሳስበኝ በቂ ብርሃን መኖሩ ብቻ ነው።”—ኤሌና

  •   ከማንበብህ በፊት ጸልይ። ለማንበብ ያሰብከውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለመረዳት፣ ለማስታወስና ከትምህርቱ ጥቅም ለማግኘት እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው።—ያዕቆብ 1:5

     ከጸሎትህ ጋር የሚስማማ እርምጃ ለመውሰድ ደግሞ ስለምታነበው ዘገባ በጥልቀት ቆፍር። እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? JW Library አፕሊኬሽን ወይም ኢንተርኔት ላይ የሚገኘውን መጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመህ የምታነብ ከሆነ አንድን ጥቅስ ጠቅ በማድረግ ስለ ጥቅሱ ምርምር ማድረግ ወይም ጥቅሱን የሚያብራሩ ጽሑፎች ማግኘት ትችላለህ።

  •   ጥያቄ ጠይቅ። ለምሳሌ፦ ‘ይህ ዘገባ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል? ጎልቶ የሚታየው የትኛው የይሖዋ ባሕርይ ነው? እኔስ በዚህ ረገድ እሱን መምሰል እችል ይሆን?’ (ኤፌሶን 5:1) ‘ከዚህ ዘገባ ለሕይወቴ የሚጠቅመኝ ምን ትምህርት አገኛለሁ?’ (መዝሙር 119:105) ‘ያነበብኩትን ነገር ሌሎችን ለመርዳት ልጠቀምበት እችላለሁ?’—ሮም 1:11

     በተጨማሪም ‘ያነበብኩት ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። በተለይ ይህ ጥያቄ በጣም አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ያለው ሐሳብ በሙሉ ከአንድ መሠረታዊ ጭብጥ ጋር በሆነ መንገድ ተያያዥነት አለው፤ ይህ ጭብጥ ይሖዋ ሰማይ ላይ ባለው መንግሥቱ አማካኝነት ስሙን የሚያስቀድሰው እንዲሁም የመግዛት መብት እንዳለውና የእሱ አገዛዝ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ የሚያረጋግጠው እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ ነው።