የወጣቶች ጥያቄ
ሁለት ዓይነት ሕይወት መኖሬን እንዴት ላቁም?
አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ‘የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች ለመጠበቅ ያን ያህል የምጨነቀው ለምንድን ነው?’ ብለው የሚያስቡበት ጊዜ አለ። (መዝሙር 73:2, 3) ቀስ ብለው ደግሞ ከይሖዋ ሕጎች ጋር የሚጋጩ ነገሮችን ማድረግ ይጀምሩ ይሆናል፤ ከዚያም መጥፎ ምግባራቸውን በመደበቅ በሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ፊት ያልሆኑትን መስለው ለመታየት ይሞክራሉ።
ይህን የማስመሰል ጎዳና የጀመሩ ሆኖም አካሄዳቸውን ማስተካከል የሚፈልጉ ሁሉ ለውጥ ማድረግ ይችላሉ፤ ይህ ርዕስ የተዘጋጀው እነሱን ለመርዳት ነው።
በዚህ ገጽ ላይ
ሁለት ዓይነት ሕይወት ምንድን ነው?
ሁለት ዓይነት ሕይወት የሚመራ ሰው ይሖዋን ከማይታዘዙ እኩዮቹ ጋር ሲሆን፣ ስህተት እንደሆነ የሚያውቀውን ነገር ያደርጋል፤ አምላክን ከሚያገለግሉ ሰዎች ጋር ሲሆን ግን ይሖዋን ማገልገል የሚፈልግ መስሎ ለመታየት ይሞክራል። አንድ ሰው፣ ግን ሁለት ማንነት እንደ ማለት ነው፤ እዚያም እዚህም ያልሆነውን ሆኖ ይታያል።
“ሁለት ዓይነት ሕይወት የምትመራ ከሆነ በሁለቱም ቦታ ማንነትህን ደብቀህ ነው የምትኖረው፤ እውነተኛ ማንነትህን የሚያውቅ ሰው የለም። እንደ እውነቱ ከሆነ ሁለት ዓይነት ሕይወት፣ ሁለቱንም ወገኖች መዋሸት ነው።”—ኤሪን
ይህን ታውቅ ነበር? ብቻህን ስትሆን ይሖዋ እንደማይወደው የምታውቀውን ነገር የምታደርግ ከሆነም ሁለት ዓይነት ሕይወት እየኖርክ ነው።
“በ14 ዓመቴ ኢንተርኔት ላይ የብልግና ምስሎችን ማየት ጀመርኩ። ከሌሎች ጋር ስሆን ፖርኖግራፊ የምጠላ መስዬ ነው የምታየው፤ በውስጤ ግን አልጠላውም።”—ኖላን
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል።”—ማቴዎስ 6:24
ሁለት ዓይነት ሕይወት የምኖር ከሆነ መጥፎ ሰው ነኝ ማለት ነው?
ላይሆን ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ላለመከተል የመረጡ ሰዎች እንዳሉ የታወቀ ነው። አንተ ግን እንደዚህ ዓይነት ሰው ነህ? ወይስ ለዚህ አካሄድህ ምክንያት የሆነህ ሌላ ነገር አለ? ለምሳሌ፦
ከእኩዮችህ መለየት ስለሚያሳፍርህ
ከጉባኤህ ወንድሞችና እህቶች ይልቅ አብረውህ ከሚማሩት ልጆች ጋር ብዙ የሚያመሳስልህ ነገር እንዳለ ስለሚሰማህ
ሁሉንም የአምላክ መመሪያዎች መከተል ከአቅምህ በላይ እንደሆነ ስለምታስብ
“አንዳንድ ወጣቶች ሁለት ዓይነት ሕይወት የሚመሩት መገለል ስለማይፈልጉ ነው። አብረዋቸው የሚሆኑት ሰዎች እንደ እነሱ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች የሚከተሉ ባይሆኑም እንኳ ለእነሱ ለውጥ አያመጣም።”—ዴቪድ
እርግጥ ነው፣ ከላይ ከተዘረዘሩት ነገሮች መካከል የትኛውም ቢሆን ሁለት ዓይነት ሕይወት ለመኖር በቂ ምክንያት ሊሆን አይችልም። ያም ቢሆን ጥሩ ሰዎችም እንኳ ወደዚህ አካሄድ የሚያመሩት ለምን እንደሆነ ይጠቁመናል። አንተም በዚህ ወጥመድ ተይዘህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?
ሁለት ዓይነት ሕይወት መኖሬን እንዴት ላቁም?
1. የአሁኑን ሕይወትህን ገምግም። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ሰው ሆኜ ነው መኖር የምፈልገው? በዚህ አካሄዴ ከቀጠልኩ ሕይወቴ ምን ዓይነት ይሆናል?’
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ብልህ ሰው አደጋ አይቶ ይሸሸጋል፤ ተሞክሮ የሌለው ሰው ግን ዝም ብሎ ይሄዳል፤ መዘዙንም ይቀበላል።”—ምሳሌ 27:12
2. ያለህበትን ሁኔታ በግልጽ ተናገር። ለወላጆችህ ወይም የይሖዋን ሕግ ለሚከተል አንድ የበሰለ ወዳጅህ ያለህበትን ሁኔታ ንገራቸው። እንዲረዱህ በመጠየቅህ መደሰታቸው አይቀርም። ትክክል የሆነውን ለማድረግ በመፈለግህም ይኮሩብሃል።
በሁለት ዓይነት ሕይወት ወጥመድ ውስጥ ጠልቀህ ገብተህ ከሆነ እርዳታ ለማግኘት ተጣራ
“የምከተለውን የተሳሳተ አካሄድ ለሌሎች መናገር በሕይወቴ ውስጥ በጣም ከከበዱኝ ነገሮች አንዱ ነበር፤ አንዴ ከተናገርኩ በኋላ ግን በጣም ቀለለኝ።”—ኖላን
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የሠራውን በደል የሚሸፋፍን አይሳካለትም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ሁሉ ግን ምሕረት ያገኛል።”—ምሳሌ 28:13
3. አካሄድህ የሚያስከትለውን ነገር ተቀበል። ልታስታውሰው የሚገባው አንድ ነገር፣ አኗኗርህን ከወላጆችህ ወይም ከጉባኤው ደብቀህ ስለቆየህ በአንተ ላይ ያላቸው እምነት በተወሰነ መጠንም ቢሆን ይቀንሳል። በመሆኑም ወላጆችህ ወይም የጉባኤው ሽማግሌዎች አንዳንድ ገደቦች ሊጥሉብህ ይችላሉ። አካሄድህ ያስከተለውን ውጤት በጸጋ ተቀበል፤ ከዚህ በኋላም “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር” ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።—ዕብራውያን 13:18
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የኋላ ኋላ ጥበበኛ እንድትሆን ምክርን ስማ፤ ተግሣጽንም ተቀበል።”—ምሳሌ 19:20
4. አምላክ እንደሚወድህ ጠንካራ እምነት ይኑርህ። ይሖዋ ስለሚወደን የምናደርገውን ነገር በሙሉ ያውቃል። ሁለት ዓይነት ሕይወት እየኖርክ ከሆነ ይሖዋ ይህን ያውቃል፤ ድርጊትህም ያሳዝነዋል። ያም ቢሆን ‘ስለ አንተ ስለሚያስብ’ አካሄድህን እንድታስተካክል ሊረዳህ ይፈልጋል።—1 ጴጥሮስ 5:7
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን ያሳይ ዘንድ የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመላለሳሉ።”—2 ዜና መዋዕል 16:9