በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

የደረሰብኝን አሳዛኝ ሁኔታ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

የደረሰብኝን አሳዛኝ ሁኔታ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

 ማንኛችንም ብንሆን አሳዛኝ ሁኔታ ያጋጥመናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ፈጣኖች በውድድር ሁልጊዜ አያሸንፉም፤ ኃያላን በውጊያ ሁልጊዜ ድል አይቀናቸውም” ይላል። ሁሉም “ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል።” (መክብብ 9:11) ይህ ጥቅስ አሳዛኝ ሁኔታ ለደረሰባቸው ወጣቶችም ይሠራል። የደረሰባቸውን ነገር የተቋቋሙት እንዴት ነው? እስቲ ሁለት ምሳሌዎች ተመልከት።

 ሬቤካ

 የ14 ዓመት ልጅ እያለሁ ወላጆቼ ተፋቱ።

 አባቴ ለተወሰነ ጊዜ ብቻውን መሆን ስለ ፈለገ ነው እንጂ ወላጆቼ ሊፋቱ አይችሉም ብዬ አሰብኩ። አባቴ እናቴን ይወዳታል፤ ታዲያ ለምንድን ነው ጥሏት የሚሄደው? እሺ እኔንስ ለምን ትቶኝ ይሄዳል?

 የተፈጠረውን ሁኔታ አንስቼ ለሰው ማውራት ከበደኝ። ይህንን ሐሳብ ጨርሶ ከአእምሮዬ ማውጣት ፈልጌ ነበር። በወቅቱ ባላስተውለውም እንኳ ጉዳዩ በጣም አናዶኝ ነበር። ለጭንቀት የተዳረግኩ ከመሆኑም ሌላ ጥሩ እንቅልፍ አልተኛም ነበር።

 የ19 ዓመት ልጅ እያለሁ እናቴ በካንሰር ሞተች። እሷ ምርጥ ጓደኛዬ ነበረች።

 የወላጆቼ መፋታት በጣም ጎድቶኝ ነበር፤ የእናቴ ሞት ደግሞ ፍጹም ከአቅሜ በላይ ሆነብኝ። እስከ አሁን ድረስ ከሐዘኔ አላገገምኩም። እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር የማደሩ ነገር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰብኝ ነው፤ አሁንም ጭንቀቱ አልለቀቀኝም።

 ሆኖም በዚያው ወቅት፣ ጠቃሚ የሆኑ ብዙ ነገሮች አግኝቻለሁ። ለምሳሌ ያህል፣ ምሳሌ 18:1 ራሳችንን ከሰዎች ማግለል እንደሌለብን ይመክረናል፤ በመሆኑም ይህንን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ እየጣርኩ ነው።

 በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኔ መጠን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ የሚያበረታቱ ጽሑፎቻችንን ለማንበብ ጥረት አደርጋለሁ። በተለይ ወላጆቼ በተፋቱበት ወቅት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለው መጽሐፍ በጣም ጠቅሞኛል። እንዲያውም በመጽሐፉ ሁለተኛ ጥራዝ ላይ የሚገኘውን “ከአንደኛው ወላጄ ጋር ብቻ እየኖርኩ ደስተኛ መሆን እችላለሁ?” የሚለውን ምዕራፍ ማንበቤ ትዝ ይለኛል።

 የሚሰማኝን ውጥረት እንድቋቋም ከሚረዱኝ የምወዳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንዱ ማቴዎስ 6:25-34 ነው። በቁጥር 27 ላይ ኢየሱስ “ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ርዝማኔ ላይ አንድ ክንድ a መጨመር የሚችል ይኖራል?” በማለት ጠይቋል።

 ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ መጥፎ ነገሮች ያጋጥሙናል። ሆኖም ከእናቴ ምሳሌ የተማርኩት ነገር ቢኖር የሚደርሱብንን ችግሮች የምንቋቋምበት መንገድ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። እናቴ ብዙ መከራ አሳልፋለች፦ ፍቺን ጨምሮ በማይድን በሽታ ተሠቃይታለች። ይሁንና በዚህ ጊዜ ሁሉ አዎንታዊ አመለካከት የነበራት ሲሆን በአምላክ ላይ የነበራትን ጠንካራ እምነትም እስከ መጨረሻው ጠብቃለች። ስለ ይሖዋ ያስተማረችኝን ነገር መቼም ቢሆን አልረሳውም።

 ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ማንበብህ መከራን ለመቋቋም የሚረዳህ እንዴት ነው?—መዝሙር 94:19

 ኮርዴል

 የ17 ዓመት ልጅ እያለሁ አባቴ ሕይወቱ ባለፈበት ሰዓት ከጎኑ ነበርኩ። እሱን በሞት ማጣቴ በሕይወቴ የገጠመኝ ከሁሉ የከፋው ነገር ነበር። ቅስሜ ተሰበረ።

 መሞቱን አምኖ መቀበል በጣም ከብዶኝ ነበር፤ አስከሬኑን በጨርቅ ሲሸፍኑት ውስጥ ያለው አባቴ ነው ብሎ መቀበል አቃተኝ። ‘ነገ ይነሳል’ ብዬ አሰብኩ። በባዶነት ስሜት ተዋጥኩ፤ ደግሞም ግራ ተጋባሁ።

 እኔና ቤተሰቦቼ የይሖዋ ምሥክሮች ስንሆን አባቴ በሞተበት ወቅት የጉባኤያችን አባላት ትልቅ ድጋፍ ሰጥተውናል። ወንድሞችና እህቶች ምግብ ያመጡልን ነበር፤ እኛ ጋር ለማደር ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸውልናል፤ እንዲሁም ከአጠገባችን አልራቁም። ይህንንም በወረት ሳይሆን ረዘም ላለ ጊዜ አድርገውልናል። ያደረጉልን ድጋፍ የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደሆኑ እንዳረጋግጥ አስችሎኛል።—ዮሐንስ 13:35

 በተለይ ያበረታታኝ ጥቅስ 2 ቆሮንቶስ 4:17, 18 ነው። እንዲህ ይላል፦ የሚደርስብን መከራ ጊዜያዊና ቀላል ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድና ዘላለማዊ የሆነ ክብር ያስገኝልናል፤ ስለዚህ ዓይናችን እንዲያተኩር የምናደርገው በሚታዩት ነገሮች ላይ ሳይሆን በማይታዩት ነገሮች ላይ ነው። የሚታዩት ጊዜያዊ ናቸውና፤ የማይታዩት ግን ዘላለማዊ ናቸው።”

 በተለይ በጥቅሱ መጨረሻ ላይ የተገለጸው ሐሳብ በጥልቅ ነክቶኛል። የአባቴ ሥቃይ ጊዜያዊ ነበር፤ አምላክ የገባው የተስፋ ቃል ግን ዘላለማዊ ነው። የአባቴ ሞት ሕይወቴን ቆም ብዬ እንድመረምርና ግቦቼን እንዳስተካክል አጋጣሚ ሰጥቶኛል።

 ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ በሕይወትህ የሚያጋጥምህ መከራ ግቦችህን ቆም ብለህ እንድትመረምር የሚረዳህ እንዴት ነው?—1 ዮሐንስ 2:17

a ክንድ የርዝመት መለኪያ ሲሆን መጠኑ 45 ሴንቲ ሜትር ገደማ ነው።