በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ብንለያይ ይሻል ይሆን? (ክፍል 2)

ብንለያይ ይሻል ይሆን? (ክፍል 2)

 በቅድሚያ፣ ለመነጋገር አመቺ የሆነ ሁኔታ መምረጥ አለብሽ። a ይህ ሲባል ምን ማለት ነው?

 አንቺ በወንድ ጓደኛሽ ቦታ ብትሆኚ ኖሮ ጉዳዩ እንዴት እንዲነገርሽ እንደምትፈልጊ አስቢ። (ማቴዎስ 7:12) በሌሎች ፊት ቢነገርሽ ደስ ይልሻል? ደስ እንደማይልሽ የታወቀ ነው።

 ከአንድ ሰው ጋር ግንኙነታችሁን ለማቋረጥ ከወሰንሽ፣ ተገናኝቶ መነጋገሩ ጥበብ እንዳልሆነ እስካልተሰማሽ ድረስ በስልክ የመልእክት መቀበያ ማሽን ላይ መልእክት በመተው አሊያም በሞባይል ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት የጽሑፍ መልእክት በመላክ ውሳኔሽን ባታሳውቂ የተሻለ ነው። ከዚህ ይልቅ ይህንን ከባድ ጉዳይ ለመወያየት አመቺ የሆነ ጊዜና ቦታ ምረጪ።

 ቀጣዩ ነገር፣ ‘ውሳኔሽን የምትናገሪው እንዴት ነው?’ የሚለው ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ እርስ በርሳቸው ‘እውነትን እንዲነጋገሩ’ ክርስቲያኖችን አሳስቧቸዋል።—ኤፌሶን 4:25

 ስለዚህ ከሁሉ የተሻለው መንገድ፣ ጥብቅ አቋም እንዳለሽ በሚያሳይ ሆኖም ስሜቱን በማይጎዳ መልኩ ውሳኔሽን ማሳወቅ ነው። ግንኙነታችሁ እንደማያዛልቅ ያሰብሽው ለምን እንደሆነ በግልጽ ንገሪው።

 ድክመቶቹን መዘክዘክ ወይም የትችት መዓት ማዥጎድጎድ አያስፈልግሽም። “አንተ በፍጹም . . . አታደርግም” ወይም “አንተ መቼም ቢሆን . . . አታውቅም” በማለት ጣትሽን እሱ ላይ ከመቀሰር ይልቅ የራስሽን ስሜት ብቻ መግለጹ የተሻለ ነው፤ ለምሳሌ “እኔ የምፈልገው . . . ሰው ነው” ወይም “ግንኙነታችንን ማቆም እንደሚገባን የሚሰማኝ . . . ምክንያት ነው” ማለት ትችያለሽ።

 ይህ የምትወላውዪበት ጊዜ አይደለም፤ ጓደኛሽ ሐሳብሽን እንዲያስቀይርሽ ልትፈቅጂ አይገባም። ግንኙነታችሁን ለማቆም የወሰንሽው አጥጋቢ ምክንያት ስላለሽ መሆኑን መዘንጋት የለብሽም። በመሆኑም ጓደኛሽ አሳማኝ የሚመስሉ ነጥቦችን በመደርደር ውሳኔሽን እንዳያስቀይርሽ ተጠንቀቂ። ሎሪ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ከቀድሞ የወንድ ጓደኛዬ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ካቆምኩ በኋላ፣ በነገሩ በጣም እንደተጎዳ ማስመሰል ጀመረ። እንዲህ የሚያደርገው እንዳዝንለት ብሎ እንደነበረ ይሰማኛል። በእርግጥም አዝኜለት ነበር። ሆኖም ይህ ድርጊቱ አቋሜን እንዳላላ አላደረገኝም።” አንቺም እንደ ሎሪ ምን እንደምትፈልጊ ማወቅ ይኖርብሻል። ከአቋምሽ ፍንክች አትበዪ። ቃልሽ አይደለም ከሆነ አይደለም ይሁን።—ያዕቆብ 5:12

a በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።