በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ከሰዎች ጋር የመጨዋወት ችሎታዬን ማሻሻል የምችለው እንዴት ነው?

ከሰዎች ጋር የመጨዋወት ችሎታዬን ማሻሻል የምችለው እንዴት ነው?

 በአካል ተገናኝቶ መጨዋወት ምን ጥቅም አለው?

 አንዳንዶች በአካል ተገናኝቶ መነጋገር፣ በተለይ የጽሑፍ መልእክት ከመላላክ አንጻር ሲታይ በጣም ከባድና ውጥረት የሚፈጥር ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል።

 “በአካል ተገናኝቶ መነጋገር ይበልጥ ይጨንቃል፤ ምክንያቱም የተናገርከውን ነገር ተመልሰህ ማስተካከል ወይም መሰረዝ አትችልም።”—አና

 “የጽሑፍ መልእክት አስቀድሞ እንደተቀዳ ፕሮግራም፣ በአካል ተገናኝቶ ማውራት ደግሞ እንደ ቀጥታ ስርጭት ነው ሊባል ይችላል። ከሰዎች ጋር ሳወራ ሁሌም የማስበው ከአሁን አሁን አጉል ነገር ተናገርኩ ብዬ ነው!”—ጂን

 ሆኖም ይዋል ይደር እንጂ ከሰዎች ጋር በአካል ተገናኝቶ የመነጋገር ችሎታ ማዳበር ይኖርብሃል። ለምሳሌ አዳዲስ ጓደኞችን ለማፍራት፣ ሥራ ለማግኘትና በዚያ ሥራ ለመቀጠል እንዲሁም ዝግጁ ስትሆን የፍቅር ጓደኝነት ለመጀመር ይህ ችሎታ የግድ ያስፈልግሃል።

 ደስ የሚለው፣ ከሰዎች ጋር በአካል ተገናኝቶ መጨዋወት የምታስበውን ያህል የሚያስፈራ ነገር አይደለም። ዓይናፋር ብትሆንም እንኳ ይህን ችሎታ ማዳበር ትችላለህ።

 “አልፎ አልፎ የተሳሳተ ነገር መናገርህና በተናገርከው ነገር ማፈርህ የማይቀር ነገር ነው። ‘እንዴት እሳሳታለሁ?’ የሚል አመለካከት ሊኖርህ አይገባም።”—ኒል

 ጭውውት መጀመር የሚቻለው እንዴት ነው?

 •   ጥያቄ ጠይቅ። የሰዎችን ትኩረት ስለሚስብ አንድ ርዕሰ ጉዳይ አስብ፤ ከዚያም ያን ርዕሰ ጉዳይ ተጠቅመህ ጭውውት ጀምር። ለምሳሌ፦

   “በቅርቡ የት የት አካባቢ ተጉዘሃል?”

   “ይሄ በጣም አሪፍ ድረ ገጽ ነው። አይተኸው ታውቃለህ?”

   [አንድ ጉዳይ ከጠቀስክ በኋላ] “ስለዚህ ጉዳይ ሰምተሃል?”

   ጭውውታችሁ ሰፋ ካለ ርዕሰ ጉዳይ ይልቅ በአንተና በምታነጋግረው ግለሰብ ላይ ያተኮረ እንዲሆን ከፈለግክ ሁለታችሁንም የሚመለከቷችሁን ጉዳዮች ለማሰብ ሞክር። ለምሳሌ የምትማሩት አንድ ትምህርት ቤት ነው? ወይም የምትሠሩት ሥራ ተመሳሳይ ነው? ሁለታችሁንም በሚያገናኟችሁ ጉዳዮች ላይ ተመሥርተህ ጥያቄዎችን ማንሳት ትችላለህ።

   “የእናንተን ትኩረት የሚስቡትንና የሰዎችን ምላሽ ለመስማት የምትጓጉላቸውን ጥያቄዎች ለማሰብ ሞክሩ።”—ማሪትሳ

   ማሳሰቢያ፦ በአንድ ጥያቄ ላይ ሌላ ጥያቄ በማከታተል እንደ መርማሪ ፖሊስ አትሁን። ግለሰቡን የሚያሸማቅቁ ጥያቄዎችንም እንዳትጠይቅ ተጠንቀቅ። “በሕይወትህ ውስጥ በጣም የምትፈራው ነገር ምንድን ነው?” ወይም “ሁሌ ሰማያዊ ልብስ የምትለብሰው ለምንድን ነው?” እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች ጥያቄው የቀረበለትን ግለሰብ ሊያስጨንቁ ይችላሉ። እንዲያውም ሁለተኛው ጥያቄ ትችት ያዘለም ሊመስል ይችላል!

   በተጨማሪም ግለሰቡ ላነሳኸው ጥያቄ መልስ ከመስጠቱ በፊት ወይም ከሰጠ በኋላ፣ አንተ ስለ ጉዳዩ ያለህን አመለካከት መግለጽህ ግለሰቡን በጥያቄ የምታፋጥጠው እንዳትመስል ይረዳሃል። በሌላ አባባል ውይይታችሁ ቃለ መጠይቅ ሳይሆን ጭውውት ይሁን።

  ጥያቄዎቻችሁ መርማሪ ፖሊስ ያስመስሏችኋል?

   የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በሰው ልብ ውስጥ ያለ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውኃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ቀድቶ ያወጣዋል።”​—ምሳሌ 20:5

 •   ጥሩ አድማጭ ሁን። ከሌሎች ጋር ጥሩ ጭውውት በማድረግ ረገድ ስኬታማ መሆንህ የተመካው ከመናገር ችሎታህ ይልቅ በማዳመጥ ችሎታህ ላይ ነው።

   “ስለማነጋግረው ሰው አንድ አዲስ ነገር ለማወቅ ጥረት አደርጋለሁ። በኋላም ግለሰቡ የነገረኝን ነገር በማስታወስ በቀጣዩ ጊዜ ስንገናኝ ስለ ምን ጉዳይ ልጠይቀው እንደምችል አስባለሁ።”—ታማራ

   ማሳሰቢያ፦ ‘ቀጥሎ ምን ልናገር?’ ብለህ አትጨነቅ። በደንብ ካዳመጥክ ግለሰቡ በተናገረው ነገር ላይ ተመሥርተህ ሐሳብ መስጠት ትችላለህ።

   የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ [ይሁን]።”​—ያዕቆብ 1:19

 •    ለግለሰቡ ከልብ እንደምታስብለት አሳይ። ለምታነጋግረው ሰው የምታስብለት ከሆነ ጭውውቱ ይበልጥ አስደሳች ይሆንልሃል።

   “ከአንድ ሰው ጋር ስትጨዋወት አልፎ አልፎ የምትናገረው ነገር ይጠፋህ ይሆናል፤ ሆኖም ግለሰቡ፣ የሚናገረው ነገር ከልብ እንደሚያሳስብህ ከተሰማው ጭውውታችሁ አስደሳች ይሆናል።”—ማሪ

   ማሳሰቢያ፦ ሊያስጨንቁ የሚችሉ ጥያቄዎችን አትጠይቅ። ለምሳሌ “ቆንጆ ኮት ነው የለበስከው። ስንት ገዛኸው?” እንደሚለው ያለ የአድናቆት መግለጫ ግለሰቡን ቅር ሊያሰኝ ይችላል።

   የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”​—ፊልጵስዩስ 2:4

 ጭውውቱን መደምደም የምትችለው እንዴት ነው? ጆርዳን የተባለ ወጣት “አዎንታዊ ነገር በመናገር ጭውውቱን ለመደምደም ጥረት አድርጉ” የሚል ምክር ሰጥቷል። አክሎም “‘በዚህ አጋጣሚ ስለተጨዋወትን ደስ ብሎኛል’ ወይም “መልካም ቀን ይሁንልህ’ እንደሚሉት ያሉ ሐሳቦችን መሰንዘር ግለሰቡን በቀጣዩ ጊዜ ስታገኙት ጥሩ ጭውውት ለማድረግ መሠረት ይጥላል” ብሏል።