በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ሌሎችን መርዳት ያለብኝ ለምንድን ነው?

ሌሎችን መርዳት ያለብኝ ለምንድን ነው?

 ብዙ ሰዎች የማያውቋቸው ሁለት ሚስጥሮች

 ሚስጥር 1፦ ለሌሎች የምትሰጥ ከሆነ ሰዎች በምላሹ ለአንተ እንደዚያ ያደርጉልሃል!

 ሰዎች ሰጪ እንደሆንክ ሲመለከቱ እነሱም ለአንተ ለመስጠት መፈለጋቸው አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ይላል፦

  •  “ሰጪዎች ሁኑ፤ ሰዎችም ይሰጧችኋል። . . . በምትሰፍሩበት መስፈሪያ መልሰው ይሰፍሩላችኋል።”​—ሉቃስ 6:38

  •  “ለሰዎች የምታደርጉላቸውን ያህል እነሱም ያደርጉላችኋል።”​—ሉቃስ 6:38 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርዥን

 ሚስጥር 2፦ ሌሎችን ስትረዳ ራስህንም ትጠቅማለህ!

 ለሌሎች ጥሩ ነገር ስታደርግ ለራስህ ያለህ አክብሮት ይጨምራል፤ እንዲሁም መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ ትቀምሳለህ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ይላል፦

  •  “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”​—የሐዋርያት ሥራ 20:35

  •  “ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችን፣ አካለ ስንኩላንን፣ አንካሶችንና ዓይነ ስውሮችን ጥራ፤ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ ደስተኛ ትሆናለህ።”​—ሉቃስ 14:13, 14

 አሳቢ የሆኑ ወጣቶች

 ለሌሎች የሚያስቡ ብዙ ወጣቶች አሉ። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከት።

 “አንዳንድ ጊዜ እንዲሁ ሶፋ ላይ ቁጭ ብሎ ቴሌቪዥን ማየት ያምረኛል፤ በዚህ ጊዜ ግን አባቴና እናቴ ወደ አእምሮዬ ይመጣሉ፤ ሲሠሩ ውለው ወደ ቤት ሲመለሱ ምን ያህል እንደሚደክማቸው አስባለሁ። ከዚያም ተነስቼ ዕቃ ማጠብና ቤት ማጽዳት እጀምራለሁ። ከዚህም ሌላ ወላጆቼ ቡና ስለሚወዱ ቡና አፍልቼ እጠብቃቸዋለሁ። እናቴ ቤት ስትገባ ‘ጎሽ! ቤቱ እንዴት ደስ ይላል! የቤቱ መዓዛ ራሱ ያውዳል። በጣም አመሰግናለሁ፣ የኔ ቆንጆ!’ ትለኛለች። ለወላጆቼ እንዲህ ዓይነት ጥሩ ነገሮችን ሳደርግ ሁልጊዜ ደስ ይለኛል።”​—ኬሲ

 “ወላጆቼ የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ በማሟላት ተንከባክበው አሳድገውኛል። ባለፈው ዓመት ወላጆቼ መኪናቸው ከባድ ብልሽት አጋጥሞት ነበር፤ መኪናውን ለማስጠገን የሚወስደው ወጪ ካጠራቀምኩት ገንዘብ ብዙውን የሚጠይቅ ቢሆንም ለጥገና የሚሆነውን ወጪ ሸፈንኩ። በእርግጥ መጀመሪያ ላይ እምቢ ብለውኝ ነበር፤ እኔ ግን በግድ አልኳቸው። ለወላጆቼ ከዚህ እጅግ የበለጠ ባደርግም እንኳ ይገባቸዋል። በዚያ ላይ ደግሞ ለእነሱ መስጠት በመቻሌ በጣም አስደሰተኝ።”​—ሆሊ

 ይህን ታውቅ ነበር? የይሖዋ ምሥክር የሆኑ በርካታ ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ሌሎችን መርዳት የሚያስገኘውን ደስታ ቀምሰዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች በጣም በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ሄደው ለማስተማር ሲሉ ወደ ሌላ አገር ተዛውረዋል።

 “ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሜክሲኮ ሄድኩ። ብዙ ገንዘብ ስለሌለኝ አንዳንድ ጊዜ ለሰዎች በገንዘብ ወይም በንብረት እርዳታ መስጠት ይከብደኛል። ይሁን እንጂ ጊዜዬንና ጉልበቴን ለአገልግሎት መስጠቴ ሰዎችን በገንዘብ ከመርዳት የበለጠ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ተገንዝቤያለሁ።”​—ኤቫን

 ሌሎችን መርዳት የምችለው እንዴት ነው?

 ሌሎችን መርዳት የሚያስገኘውን ደስታ መቅመስ ትፈልጋለህ? ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር።

 ቤተሰብህን ለመርዳት እንዲህ ማድረግ ትችላለህ፦

  •  ሳትጠየቅ ቤቱን ማጽዳትና ማስተካከል እንዲሁም ዕቃ ማጠብ

  •  ምግብ ማዘጋጀት

  •  ለወላጆችህ ያለህን አመስጋኝነት ካርድ ላይ ጽፈህ መስጠት

  •  ወንድምህን ወይም እህትህን የትምህርት ቤት ሥራቸውን ሲሠሩ መርዳት

 ከቤተሰብህ ውጭ ያሉ ሰዎችን መርዳት፦

  •  የታመመ ሰው ካለ ካርድ ጽፎ መላክ

  •  በዕድሜ የገፋ ሰው ግቢውን ሲያስተካክል መርዳት

  •  ከቤት መውጣት የማይችል ሰውን ሄዶ መጠየቅ

  •  አስቸጋሪ ሁኔታ ለገጠመው ሰው ስጦታ መስጠት

 ጠቃሚ ምክር፦ ልታደርጋቸው የምትችላቸው ሌሎች ነገሮች እንዳሉ ለማሰብ ሞክር። ከዚያም በዚህ ሳምንት አንድ ሰው ለመርዳት ግብ አውጣ። ሌሎችን መርዳት ምን ያህል እንደሚያስደስት ስትመለከት መገረምህ አይቀርም!

 “ሌሎችን ስትረዳ አንተም ደስተኛ ትሆናለህ። አንድ ትልቅ ነገር እንዳከናወንህ የሚሰማህ ከመሆኑም ሌላ ሌሎች የተደረገላቸውን ነገር ሲያደንቁ ትመለከታለህ። መጀመሪያ ላይ እንደዚያ ባይሰማህም እንኳ ሌሎችን መርዳት ምን ያህል እንደሚያስደስት ማየት ትችላለህ። አንተ ራስህ ብዙ ጥቅም ስለምታገኝ ሰዎችን ለመርዳት ብለህ የከፈልከው መሥዋዕትነት ራሱ ምንም መስሎ አይታይህም።”​—አላና