የወጣቶች ጥያቄ
ማኅበራዊ ሚዲያ ምን ዓይነት ተጽዕኖ እያሳደረብኝ ነው?
ወላጆችህ ማኅበራዊ ሚዲያ እንድትጠቀም ይፈቅዱልሃል? ከሆነ፣ ይህ ርዕስ በሦስት ወሳኝ አቅጣጫዎች ይረዳሃል።
በዚህ ርዕስ ውስጥ
ማኅበራዊ ሚዲያ በጊዜዬ ላይ ምን ተጽዕኖ እያሳደረ ነው?
ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም ፈረስ እንደመጋለብ ነው፤ አንተ ካልተቆጣጠርከው እሱ ይቆጣጠርሃል።
“‘ለጥቂት ደቂቃዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ልጠቀም’ ብዬ እጀምርና ሳላስበው ሰዓታት ያልፋሉ! ማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ ሊያስይዝና ጊዜ ሊያባክን ይችላል።”—ጆአና
ይህን ታውቅ ነበር? ማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ የሚያስይዝ የሆነው ሱስ እንዲያስይዝ ተደርጎ ስለተዘጋጀ ነው። አዘጋጆቹ አንድ ድረ ገጽ ይበልጥ ተወዳጅ በሆነና ሰዎች እሱን በመጠቀም ብዙ ሰዓት ባጠፉ ቁጥር ለማስታወቂያ ብዙ ገንዘብ እንደሚከፈላቸው ያውቃሉ።
ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ማኅበራዊ ሚዲያ ስጠቀም ጊዜው ሳላስበው ይሄድብኛል? ይህን ጊዜ ፍሬያማ ነገር ለማድረግ ልጠቀምበት እችል ይሆን?’
ምን ማድረግ ትችላለህ? ማኅበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ምን ያህል ጊዜ እንደምታሳልፍ ወስን፤ ካበጀኸው ገደብም አትለፍ።
“ስልኬ ላይ ያሉትን አንዳንድ አፕሊኬሽኖች ከሆነ ሰዓት በኋላ የሚዘጋ ፕሮግራም መጠቀም ጀመርኩ። ለተወሰነ ጊዜ ያህል ይህን ዘዴ ከተጠቀምኩ በኋላ ሚዛናዊ መሆን ቻልኩ፤ አሁን ማኅበራዊ ሚዲያ ብጠቀምም ብዙ ሰዓት አላባክንም።”—ቲና
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።”—ኤፌሶን 5:16
ማኅበራዊ ሚዲያ በእንቅልፌ ላይ ምን ተጽዕኖ እያሳደረ ነው?
አብዛኞቹ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት በአሥራዎቹ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች በቀን ቢያንስ ለስምንት ሰዓት መተኛት ያስፈልጋቸዋል፤ ሆኖም ብዙዎቹ ያን ያህል እንቅልፍ አያገኙም። ለዚህ ችግር አንዱ መንስኤ ማኅበራዊ ሚዲያ ነው።
“ከመተኛቴ በፊት መልእክት መጥቶልኝ እንደሆነ ለማየት ስልኬን እከፍታለሁ፤ ከዚያ ግን ሳላስበው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሰዓታት አጠፋለሁ። ይህን መጥፎ ልማድ ለማስወገድ እየታገልኩ ነው።”—ማሪያ
ይህን ታውቅ ነበር? በቂ እረፍት አለማድረግ ለጭንቀትና ለድባቴ ሊዳርግ ይችላል። የሥነ ልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት ጂን ትዌንጊ እንደተናገሩት ሰዎች እንዲደብራቸው ከሚያደርጉት ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ እንቅልፍ ማጣት ነው። አክለውም እንቅልፍ ማጣት “ውሎ አድሮ ለከባድ የአእምሮ ጤንነት ቀውስ” ሊዳርግ እንደሚችል ገልጸዋል። a
ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘በየቀኑ ለስንት ሰዓት እተኛለሁ?’ ‘ለእንቅልፍ መዘጋጀት ባለብኝ ሰዓት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እገኛለሁ?’
ምን ማድረግ ትችላለህ? ምሽት ላይ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችህን ከክፍልህ አውጣ። ከተቻለ፣ ከመተኛትህ ከሁለት ሰዓት በፊት የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ መጠቀም አቁም። ጠዋት ለመነሳት አላርም የሚያስፈልግህ ከሆነ ከስልክ ወይም ከታብሌት ይልቅ ሰዓት ለመጠቀም ሞክር።
“አንዳንድ ጊዜ ስልክ እየተጠቀምኩ በጣም አመሻለሁ፤ እርግጥ ለማስተካከል እየሞከርኩ ነው። የበሰለ እና ኃላፊነት የሚሰማው ሰው መሆን እፈልጋለሁ። በቀጣዩ ቀን በሙሉ ኃይሌ መሥራት እንድችል ቀደም ብዬ መተኛት አለብኝ።”—ጄረሚ
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵስዩስ 1:10
ማኅበራዊ ሚዲያ በስሜቴ ላይ ምን ተጽዕኖ እያሳደረ ነው?
አንድ ዘገባ እንደገለጸው በጥናቱ ከተካፈሉት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የሆኑ ሴቶች መካከል ግማሽ ገደማ የሚሆኑት “ሥር የሰደደ የሐዘንና የተስፋ ቢስነት ስሜት እንደሚሰማቸው” ተናግረዋል። ለዚህ አንዱ መንስኤ ማኅበራዊ ሚዲያ ሊሆን ይችላል። ዶክተር ሌነርድ ሳክስ እንዲህ ብለዋል፦ “ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ራሳችሁን ከሌሎች ጋር በማወዳደር ብዙ ጊዜ ባሳለፋችሁ መጠን በድባቴ የመዋጣችሁ አጋጣሚ ይጨምራል።” b
“ወጣቶች ራሳቸውን ከሌሎች ጋር የማወዳደር ዝንባሌ አላቸው፤ ማኅበራዊ ሚዲያ ደግሞ ይህን ዝንባሌ ይበልጥ ሊያባብሰው ይችላል። የማታውቋቸው ሰዎች የለጠፏቸውን ነገሮች ለሰዓታት ስታዩ ትቆዩና የእናንተን ሕይወት ከእነሱ ሕይወት ጋር ማወዳደር ትጀምራላችሁ፤ ወይም ደግሞ ጓደኞቻችሁ የሚያደርጓቸውን አስደሳች ነገሮች ስታዩ ብዙ ነገር እንደቀረባችሁ ሊሰማችሁ ይችላል።”—ፊቢ
ይህን ታውቅ ነበር? ማኅበራዊ ሚዲያ ከጓደኞችህ ጋር ለመገናኘት ሊረዳህ ቢችልም በአካል ተገናኝቶ ማውራትን አይተካም። ዶክተር ኒኮላስ ካርዳራስ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “በኤሌክትሮኒክ የመገናኛ ዘዴዎች መጠቀም ሰዎችን በአካል ለማግኘት ያለንን ውስጣዊ ፍላጎት ሊያረካ የሚችል አይመስልም። ምክንያቱም ሰዎች ከሌሎች ጋር ትርጉም ያለው ጊዜ የማሳለፍ መሠረታዊ ፍላጎት አላቸው።” c
ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ጓደኞቼ ምን እያደረጉ እንዳሉ ካየሁ በኋላ ብቸኝነት ይሰማኛል?’ ‘ጓደኞቼ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለጥፏቸውን ሲዝናኑ የሚያሳዩ ፎቶዎች ሳይ የእኔ ሕይወት ከእነሱ ጋር ሲወዳደር አሰልቺ እንደሆነ ይሰማኛል?’ ‘የለጠፍኩት ነገር ብዙ “ላይክ” ካላገኘ ይከፋኛል?’
ምን ማድረግ ትችላለህ? ለተወሰኑ ቀናት፣ ለሳምንት ወይም ለወር ያህል ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀምህን ሙሉ በሙሉ ለማቆም ሞክር። ከጓደኞችህ ጋር በአካል በመገናኘት ወይም በስልክ በማውራት የምታሳልፈውን ጊዜ አሳድግ። ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም ማቆምህ ውጥረትህ እንዲቀንስ ወይም ደስታህ እንዲጨምር እንዳደረገ ታስተውል ይሆናል።
“ማኅበራዊ ሚዲያ ስጠቀም በሌሎች ሰዎች ሕይወት ላይ ከልክ በላይ እንደማተኩር አስተዋልኩ። አካውንቶቼን ካጠፋሁ በኋላ ትልቅ ሸክም ከላዬ ላይ እንደወረደ ተሰማኝ፤ ይበልጥ ፍሬያማ የሆኑ ነገሮችን የማደርግበት ጊዜም አገኘሁ።”—ብሪያና
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያወዳድር ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል።”—ገላትያ 6:4