በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ብንለያይ ይሻል ይሆን? (ክፍል 1)

ብንለያይ ይሻል ይሆን? (ክፍል 1)

 መለያየት ጠቃሚ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ጂል የተባለች ወጣት ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “የወንድ ጓደኛዬ የት እንዳለሁ፣ ምን እያደረግሁ እንደሆነ እንዲሁም ከማን ጋር እንደሆንኩ ሁልጊዜ ሲጠይቀኝ እንደሚጨነቅልኝ ስለሚሰማኝ መጀመሪያ አካባቢ ደስ ይለኝ ነበር። በኋላ ላይ ግን ከእሱ ጋር ብቻ ካልሆነ በቀር ከሌላ ሰው ጋር ለደቂቃ እንኳ ጊዜ ማሳለፍ ችግር ሆነ። ሌላው ቀርቶ ከቤተሰቤ ጋር በተለይ ደግሞ ከአባቴ ጋር ስሆን ይቀና ጀመር። ከእሱ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ሳቆም አንዳች ነገር ከላዬ ላይ የወረደልኝ ያህል ቅልል አለኝ!”

 ሣራም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሟታል። የወንድ ጓደኛዋ የነበረው ጆን፣ ሥርዓት የጎደለውና ምንም ቢደረግለት የማይደሰት ሰው መሆኑን እያደር አስተዋለች፤ ከዚህም በላይ በአሽሙር ይናገራት ነበር። ሣራ ያጋጠማትን ስታስታውስ እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ ወቅት ከቀጠሯችን ሦስት ሰዓት አርፍዶ መጣ! እናቴ በሩን ስትከፍትለት ዝግት አድርጓት ገባ፤ ከዚያም ‘እንሂዳ፣ አርፍደናልኮ!’ አለኝ። የሚገርመው ‘አርፍጃለሁ’ ከማለት ይልቅ ‘አርፍደናል’ ነበር ያለው። ይቅርታ መጠየቅ ወይም ያረፈደበትን ምክንያት መግለጽ ነበረበት። ከሁሉ በላይ ደግሞ እናቴን ሊያከብራት ይገባ ነበር!”

 እርግጥ ነው፣ አንድ ግለሰብ በአንድ ወቅት ላይ መጥፎ ጠባይ ስላሳየ ወይም የሚያበሳጭ ነገር ስላደረገ ብቻ ግንኙነቱ መቆም አለበት ማለት አይደለም። (መዝሙር 130:3) ሆኖም ሣራ፣ ጓደኛዋ ከላይ የጠቀሰችው ዓይነት ሥርዓት የጎደለው ጠባይ ያሳየው በአጋጣሚ እንዳልሆነና እንዲህ ማድረግ ልማዱ እንደሆነ ስትገነዘብ ግንኙነታቸውን ለማቆም ወሰነች።

 እንደ ጂልና እንደ ሣራ አንቺም a የወንድ ጓደኛሽ ተስማሚ የትዳር አጋር እንደማይሆንሽ ብትገነዘቢስ? እንዲህ ከሆነ ውስጥሽ የሚነግርሽን ማዳመጥ አለብሽ! ነገሩ እንደሚከብድሽ ባይካድም ግንኙነቱን ማቆም ከሁሉ የተሻለ ውሳኔ ሊሆን ይችላል። ምሳሌ 22:3 “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል” ይላል።

 እውነት ነው፣ ከወንድ ጓደኛሽ ጋር መለያየት ቀላል ላይሆን ይችላል። ይሁንና ጋብቻ ዘላቂ ጥምረት እንደሆነ አስታውሺ። መለያየታችሁ ለተወሰነ ጊዜ ቢያሳዝንሽም ዕድሜ ልክሽን በጸጸት ስሜት ስትሠቃዪ ከመኖር ይሻልሻል!

a በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።