በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

የፆታ ግንኙነት እንድፈጽም የሚደረግብኝን ተጽዕኖ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

የፆታ ግንኙነት እንድፈጽም የሚደረግብኝን ተጽዕኖ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

 “ተማሪ ሳለሁ፣ አንድ ልጅ የፆታ ግንኙነት እንደፈጸመ ከተናገረ ሌሎቹ ልጆች ሁሉ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። ማንም ሰው ቢሆን ወጣ ያለ እንደሆነ ተደርጎ መታየት አይፈልግም።”—ኢሌን፣ 21

 ሁሉም ሰው የሚያደርገው ነገር እንደሆነ በማሰብ የፆታ ግንኙነት መፈጸም እንዳለብህ ተሰምቶህ ያውቃል?

 የምትወደው ሰው የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽም ጫና አድርጎብህ ያውቃል?

 ከሆነ ይህ ርዕስ የሌሎችን ጫናም ሆነ የራስህን ምኞት አሸንፈህ የተሻለ ምርጫ እንድታደርግ ይረዳሃል።

 የሚባለው እና እውነታው

 የሚባለው፦ ሁሉም ሰው የፆታ ግንኙነት ይፈጽማል።

 እውነታው፦ በ18 ዓመት ልጆች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት፣ ከሦስት ልጆች መካከል ሁለቱ የፆታ ግንኙነት ፈጽመው እንደሚያውቁ አሳይቷል። ሆኖም በዚህ ጥናት መሠረት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ልጆች ማለትም ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት የፆታ ግንኙነት ፈጽመው አያውቁም። ስለዚህ “ሁሉም ሰው የፆታ ግንኙነት ይፈጽማል” የሚለው ሐሳብ አያስኬድም።

 የሚባለው፦ የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይበልጥ ያቀራርባል።

 እውነታው፦ አንዳንድ ወንዶች ሴቶች ከእነሱ ጋር የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ጫና ለማድረግ ሲሉ እንዲህ ብለው የሚናገሩ ቢሆንም እውነታው ከዚህ የተለየ ነው። አብዛኛውን ጊዜ አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር የፆታ ግንኙነት ከፈጸመ በኋላ ከእሷ ጋር ያለውን ግንኙነት ያቋርጣል። እንዲህ ያለ ሁኔታ የደረሰባቸው ሴቶች መበሳጨታቸው አይቀርም፤ ምክንያቱም ጓደኛቸው እንደሚወዳቸው ሌላው ቢቀር ደግሞ የተወሰነ የኃላፊነት ስሜት እንደሚሰማው ይጠብቃሉ። a

 የሚባለው፦ መጽሐፍ ቅዱስ የፆታ ግንኙነትን ያወግዛል።

 እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ የፆታ ግንኙነትን አያወግዝም፤ ሆኖም የፆታ ግንኙነት ሊፈጸም የሚገባው ትዳር በመሠረቱ ወንድና ሴት መካከል ብቻ እንደሆነ ይገልጻል።—ዘፍጥረት 1:28፤ 1 ቆሮንቶስ 7:3

 የሚባለው፦ በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መመራት ደስታ ያሳጣል።

 እውነታው፦ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም መቆጠብህ ይበልጥ ደስተኛ ያደርግሃል፤ ምክንያቱም ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ሊያስከትል ከሚችለው ጭንቀት፣ ጸጸትና ስጋት ራስህን ትጠብቃለህ።

 ዋናው ነጥብ፦ ትዳር እስኪመሠርት ድረስ የፆታ ግንኙነት ባለመፈጸሙ የተጎዳ ሰው የለም። ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት በመፈጸማቸው ግን የተጎዱ በርካታ ሰዎች አሉ።

 የሚደርስብህን ጫና ማሸነፍ የምትችለው እንዴት ነው?

 •   ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ያለህን አቋም አጠናክር። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የጎለመሱ ሰዎች “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት [እንዳሠለጠኑ]” ይናገራል። (ዕብራውያን 5:14) ስለሚያምኑበት ነገር እርግጠኞች ስለሆኑ በሚደርስባቸው ተጽዕኖ የሚሸነፉበት አጋጣሚ አነስተኛ ነው።

   “ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ጠንክሬ እሠራለሁ፤ ደግሞም ጥሩ ስም አለኝ። ይህን ሊያበላሽብኝ የሚችል ምንም ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ አይደለሁም።”—አሊሺያ፣ 16

   ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ምን ዓይነት ስም ማትረፍ ትፈልጋለህ? በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስትል ያተረፍከውን ስም ማበላሸት ተገቢ ይመስልሃል?

 •   መዘዙን አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል” ይላል። (ገላትያ 6:7) የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽም ለሚደርስብህ ጫና እጅ መስጠትህ በአንተም ሆነ በሌላ ሰው ሕይወት ላይ የሚያስከትለውን መዘዝ አሻግረህ ለማሰብ ሞክር። b

   “ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ያልተፈለገ እርግዝና ወይም በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች ሊያመጣ ይችላል፤ በአብዛኛው ደግሞ የጥፋተኝነት ስሜት፣ ጸጸት አልፎ ተርፎም ያለመወደድ ስሜት ያስከትላል።”—ሲዬና፣ 16

   ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ሴክስ ስማርት የተባለው መጽሐፍ እንዲህ የሚል ጥያቄ ያቀርባል፦ “ጓደኞቻችሁ ሊጎዷችሁ የሚችሉ ነገሮችን እንድታደርጉ የሚገፋፏችሁ ከሆነ እንዲህ ካሉ ጓደኞች ጋር ጊዜ ማሳለፋችሁ ተገቢ ነው? አስፈላጊ ስለሆኑ ጉዳዮች የሚሰጧችሁን ምክሮችስ ልትሰሙ ይገባል?”

 •   ሚዛናዊ አመለካከት ይኑርህ። የፆታ ግንኙነት በራሱ መጥፎ ነገር አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ባለትዳሮች በዚህ ደስታ ሊያገኙ እንደሚገባ ይናገራል።—ምሳሌ 5:18, 19

   “የፆታ ግንኙነት ከአምላክ ያገኘነው አስደሳች ስጦታ ነው። ሆኖም አምላክ ይህን ስጦታ እንድንጠቀምበት የሚፈልገው እሱ ባሰበበት መንገድ ማለትም በጋብቻ ውስጥ ብቻ ነው።”—ጄረሚ፣ 17

   ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ወደፊት ትዳር ስትመሠርት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ትችላለህ። ቀደም ሲል የተጠቀሱት መዘዞች ይደርሱብኛል የሚል ስጋት አያድርብህም፤ ይህም የተሟላ ደስታ እንድታገኝ ያስችልሃል።

a እንዲህ ያለ ጫና የሚያሳድሩት ወንዶች ብቻ አይደሉም። ከእነሱ ጋር የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ወንዶችን ለማሳመን ጥረት የሚያደርጉ ብዙ ሴቶች አሉ።

b ከሚያስከትላቸው በርካታ መዘዞች መካከል ያልተፈለገ እርግዝና እንዲሁም ለአካለ መጠን ካልደረሱ ልጆች ጋር በተያያዘ የሕግ ተጠያቂነት ይገኙበታል።