በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

የፍቅር ጓደኝነት—ክፍል 3፦ ብንለያይ ይሻል ይሆን?

የፍቅር ጓደኝነት—ክፍል 3፦ ብንለያይ ይሻል ይሆን?

 የፍቅር ጓደኝነት ከጀመራችሁ ሰነባብታችኋል፤ ሰሞኑን ግን ጥርጣሬ እያደረባችሁ ነው። ግንኙነታችሁን ብትቀጥሉ ይሻላል ወይስ ብትለያዩ? ይህ ርዕስ የተዘጋጀው ጥሩ ውሳኔ እንድታደርጉ ለመርዳት ነው።

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 ጥርጣሬያችሁን መገምገም

 አንድ ወጣት ወንድና ሴት ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከተጠናኑ በኋላ መጀመሪያ ያሰቡትን ያህል የሚመሳሰሉ ሰዎች እንዳልሆኑ ይገነዘቡ ይሆናል። ለምሳሌ፦

  •   አንዳቸው ባሕር ዳርቻ መዝናናት ያስደስታቸዋል፤ አንዳቸው ደግሞ ተራራ መውጣት ይመርጣሉ።

  •   አንዳቸው ተግባቢ ናቸው፤ አንዳቸው ደግሞ ቁጥብ ናቸው።

  •   አንዳቸው መዋሸት ይቀናቸዋል፤ አንዳቸው ደግሞ ሁልጊዜ ሐቀኛ ናቸው።

 እነዚህ ሦስት ሁኔታዎች የተለያዩ እንደሆኑ ልብ በሉ። የመጀመሪያው የፍላጎት ልዩነት ነው፤ ሁለተኛው የባሕርይ ልዩነት ነው፤ ሦስተኛው ደግሞ የመሥፈርት ልዩነት ነው።

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ለመጋባት ብትወስኑ ከእነዚህ ሦስት ልዩነቶች መካከል ለማስተናገድ የሚከብዳችሁ የትኛው ነው? ማስማማት የምትችሉትስ የትኞቹን ልዩነቶች ነው?

 አንድ ባልና ሚስት የተለያየ ፍላጎት ወይም ባሕርይ ቢኖራቸውም አስደሳች ትዳር ሊመሠርቱ ይችላሉ። ደግሞም ሁለት ሰዎች ይጣጣማሉ ማለት በሁሉም ነገር አንድ ዓይነት ናቸው ማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ፣ አንድ ባልና ሚስት በጊዜ ሂደት ፍላጎታቸው ሊመሳሰል ወይም አንዳቸው ከሌላው ባሕርይ ሊጠቀሙ ይችላሉ። a

 በሌላ በኩል ግን የምታገቡት ሰው ከእናንተ ጋር ተመሳሳይ መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ መሥፈርት ያለው መሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ካልሆነ መለያየት ሊያስፈልጋችሁ ይችላል።

 ለምሳሌ ሁለት ሰዎች የተለያየ ሃይማኖት ቢኖራቸውስ? ፋይቲንግ ፎር ዩር ሜሬጅ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “በተደጋጋሚ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የተለያየ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች የሚመሠርቱት ጋብቻ በፍቺ የማክተሙ አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው።”

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ።”​—2 ቆሮንቶስ 6:14

 ውሳኔ ማድረግ

 መጽሐፍ ቅዱስ “የሚያገቡ ሰዎች በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) ስለዚህ በምትጠናኑበት ጊዜ በተወሰነ መጠን መከራ ቢያጋጥማችሁ ሊያስገርማችሁ አይገባም።

 ትናንሽ ግጭቶች ቢያጋጥሟችሁ ግንኙነታችሁ ተስፋ የለውም ማለት አይደለም። ዋናው ጥያቄ፣ ግጭቶችን በሰላም መፍታት ትችላላችሁ ወይ የሚለው ነው። ከተጋባችሁ በኋላ ሁለታችሁም ይህ ችሎታ ያስፈልጋችኋል።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ . . . እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ።”​—ኤፌሶን 4:32

 በሌላ በኩል ግን፣ ተደጋጋሚ ወይም ከባባድ ግጭቶች የሚያጋጥሟችሁ ከሆነ፣ ይህ ሁኔታ የማትጣጣሙ ሰዎች እንደሆናችሁ ሊጠቁም ይችላል። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ፣ ይህን ከወዲሁ ማወቃችሁ የተሻለ ነው!

ተደጋጋሚ ወይም ከባባድ ግጭቶች የሚያጋጥሟችሁ ከሆነ፣ ይህ ሁኔታ የማትጣጣሙ ሰዎች እንደሆናችሁ ሊጠቁም ይችላል

 ዋናው ነጥብ፦ የፍቅር ጓደኛችሁን ወይም ለትዳር ዝግጁ መሆናችሁን በተመለከተ ከበድ ያለ ጥርጣሬ ካደረባችሁ ጥርጣሬያችሁን በቸልታ አትለፉት!

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል፤ ተሞክሮ የሌለው ግን ዝም ብሎ ይሄዳል፤ መዘዙንም ይቀበላል።”​—ምሳሌ 22:3

 ለመለያየት ከወሰናችሁ

 መለያየት የስሜት ሥቃይ ሊያስከትል ይችላል። ሆኖም አንዳችሁ ወይም ሁለታችሁም ግንኙነታችሁን በተመለከተ በተደጋጋሚ የሚያሳስባችሁ ከሆነ መለያየታችሁ የተሻለ ሊሆን ይችላል።

 ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ለየት ያለ ምክንያት ካልኖራችሁ በቀር በጽሑፍ መልእክት ወይም በኢሜይል አማካኝነት ውሳኔያችሁን ከማሳወቅ መቆጠባችሁ የተሻለ ነው። ከዚህ ይልቅ ይህን ከባድ ጉዳይ በተመለከተ ተገናኝታችሁ መነጋገር የምትችሉበት ተገቢ ሰዓትና ቦታ ምረጡ።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ።”​—ዘካርያስ 8:16

 ተለያይታችኋል ማለት ሳይሳካላችሁ ቀረ ማለት ነው? በፍጹም። የመጠናናት ዓላማ ግለሰቡን ለማግባት ወይም ላለማግባት እንድትወስኑ መርዳት እንደሆነ አስታውሱ። ብትለያዩም እንኳ አብራችሁ ካሳለፋችሁት ጊዜ ጠቃሚ ትምህርቶችን ማግኘት ትችላላችሁ።

 ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘ከዚህ የፍቅር ጓደኝነት ራሴን በተመለከተ ምን ትምህርት አግኝቻለሁ? በአንዳንድ አቅጣጫዎች ረገድ እድገት ማድረግ እንደሚያስፈልገኝ አስገንዝቦኛል? ወደፊት የፍቅር ጓደኝነት ለመጀመር ብወስን የትኞቹን ነገሮች ማስተካከል ይኖርብኛል?’

a እነዚህ ልዩነቶች በባለትዳሮች ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይበልጥ ለመረዳት “ለቤተሰብ—የአመለካከት ልዩነቶችን ማስታረቅ” እና “ለቤተሰብ—የሚያበሳጫችሁን ጠባይ በአዎንታዊ መንገድ ማየት” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከቱ።